የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ቅድስት ሆይ !

በረከሰችው ከተማ በናዝሬት አንቺ ግን በቅድስና ትኖሪ ነበር ። በተቀደሰችው በገነት ሔዋን በደለች ። አብርሃም በከነዓን ፣ ሎጥ በሰዶም ፣ ሙሴ በግብፅ ፣ ዳንኤል በባቢሎን በቅድስና ይኖሩ ነበር ። ጥሩ ቦታ ብቻውን ጥሩ አያደርግም ። ጥሩ ልብም ከጥሩ ቦታ ጋር አስፈላጊ ነው ። በቤተ ክርስቲያን በዓለማዊነት ፣ በወንጌል መንደር በጨካኝነት የምንኖር ነን ። አንቺ ግን በጨለማው ዓለም ውስጥ እግዚአብሔርን ታከብሪ ነበር ። ብዙ መርዶ በተሰማበት ፣ ቅኝ ገዥ ፣ ኃጢአት ፣ ሰይጣን ባጎሳቆሉት ዓለም የምሥራቹን ለዓለሙ ሁሉ ጆሮ ሆነሽ ሰማሽ ። ክርስቶስን በማኅፀንሽ ስትፀንሺ ከምድር ወገን ማንም አያውቅም ነበር ። ስትወልጂው ግን ዓለሙ ሁሉ አወቀ ። የሮማው የሕዝብ መዝገብ ፣ የሩቅ ምሥራቅ ነገሥታት አወቁ ። ። ራእይም በእኛ ነፍስ ሲፀነስ ሰዎች አያውቁም ። አስቸጋሪው ሰዓት አልፎ የብቸኝነት ዘመን ወደ ኋላ ወድቆ ደስታው ሲወለድ ብዙዎች ይመጣሉ ።

ቅድስት ሆይ !

ራእይን ፀንሰው በብቸኝነት ለሚኖሩ አንቺ መጽናኛ ነሽ ። ፅንሱ ከማን ነው ብለው እንዳይቃወሙሽ ዮሴፍን መጋረጃ አደረገልሽ ። አንቺም ሞትን ሳትፈሪ በእምነት ኖርሽ ። እኛም የሚገልጥ ሳይሆን የሚሸፍን ዮሴፍን እንሻለን ። ቅድስት ሆይ ! ወልድን የመጽነስ ዜና እንደ ሰማሽ ኃይልን ተሞልተሸ ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ ገሰገስሽ ። እንደ ሥጋ ልማድ አልጸነሽምና መንፈስ ቅዱስ አቅም ሆነሽ ።

ቅድስት ሆይ !

አንቺና ኤልሳቤጥ ሳትነጋገሩ እርስዋ በእርጅናዋ ፣ አንቺ በድንግልና ፀነሳችሁ ። ላንቺ የገለጠ መልአኩ ፣ ለኤልሳቤጥ የገለጠም መንፈስ ቅዱስ ነው ። ኃጥአን ተነጋግረው አይግባቡም ። ጻድቃን ግን ሳይነጋገሩ ይግባባሉ ። በቅዱሳን መካከል የአሳብ ድንበር የለምና አንዱ ያንዱን ልብ ያውቃል ። የክርስቶስ ልብ ያላቸው አንድ አሳብ ያስባሉ ። ቅድስት ሆይ ይህን ተመኝተናል ። በረከትሽ ይድረሰን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 7 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ