የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ቅድስት ማርያም ሆይ !

የሚራዳሽን ጠራቢውን ዮሴፍን በዓይኖችሽ እያየሽ ፣ በማኅፀንሽ ያደረውን ፣ ዓለምን ያለ መዶሻ ያነጸውን ጌታ ባሰብሽ ጊዜ ድንግል ሆይ ምን አልሽ ! ሰማይና ምድር የማይችሉት አምላክ በጠባብ ማኅፀንሽ ባደረ ጊዜ ከስፋቱ ሳይሰበሰብ ፣ ከምልአቱ ሳይጎድል ሥጋን መዋሐዱ አልገረመሽም ወይ ? ከላይ ከመንበረ ሥላሴ ሳይቀንስ ወረደ ፣ ከታች ሳይጨምር ተወለደ ። ድንግል ሆይ እርሱ ሳይሰማ እርስ በርሳችን እስቲ እናውራ ። እግዚአብሔር ሰው የሆነው ፈርቶ ነው ወይ ? ሁሉ እያለው እንደሌለው የሆነው ድህነትን ልለማመድ ብሎ ነው ወይ? በጉልበት ማስገበር ሲችል እርሱ ግን የባሪያን መልክ ይዞ መምጣቱ ተጨንቆ ነው ወይ ? አብዝተው ሲርቁት አብዝቶ የሚቀርበው መላ አጥቶ ነው ወይ ? እኛ መንግሥቱን ካጣን ገሀነመ እሳት እንኳ የእኛ ባለመሆኑ የምንገባው በደባልነት ነው ። ሰይጣን ባልበላውም ጭሬ ልበትነው ብሎ በተነሣ ጊዜ ሰው ክብሩን አጣ ። ሰው እግዚአብሔርን ሲያጣ ገሀነመ እሳት እንኳ የእርሱ ያልሆነች የስቃይ ስፍራው ናት ። ድንግል ሆይ ሌላ ፍጥረት አይፈጥርም ወይ ? እርሱ ደክሞ ነቢያቱንም የሚያደክመው ለምንድነው ? ይህን ዓመፀኛ ዓለም መደምሰስ አቅቶት ነው ወይ ሰባኪዎችን የሚያደክመው ? ይህንን ያወራነው ዘመዳችን ስለሆንሽ ነው ።

እርሱ እንዳይሰማን አደራ !! ወዳጁን የማያውቅ ጠላቱንም አያውቅም ። ስለዚህ ሰው የሰይጣን አሽከር ለመሆን ወስኗል ። ታዲያ እንዲህ ከሆነ ለምን አይተወንም ። ሲጠሉት አያውቅም ወይ ? የሚወደን መጥላት ስለማይችል ነው ወይ ? እባክሽን ድንግልናዊ ሀሊብን/ወተትን ስትሰጪው ጠይቂው ። ዓለምን እያስተዳደረ ፣ ደግሞ ከሕፃናት መካከል ሲሯሯጥ ጠርተሽ “ለጠላት ይህ ሁሉ ይደረጋል ወይ ?” ብለሽ ጠይቂው ። እርሱ በሰው አንደበት ቃልን ያስቀመጠ ፣ በይሁን አዋጅም ዓለምን የፈጠረ ሳለ በክንዶችሽ አፍ ያልፈታ ዲዳ ሕፃን መሆኑ ይገርማል !! ይህን ሁሉ የመከርነው በዘመድነትሽ ነውና እርሱ እንዳይሰማን አደራ ። ድንግል ሆይ ተዪው ። እርሱ ለካ ሰው ሁኗል ። የእኛን ምሥጢር ለማወቅ ለካ ሰው ሆኗል ። በአምላክነቱ ሁሉን ማወቁ አይጠረጠርም ። ግን የእኛን ምሥጢር ለማወቅ ሰው ሆነ ። “ምን እያደረጉ ነው ?” የሚለውን ለማወቅ ሳይሆን ሁሉን ሊያደርግልን ሰው ሆነ ።

አዎ ትዝ አለኝ ሰው የሆነው የሰውን ምሥጢር ለማወቅ ነው ። ጠባዩ የታወቀ ነው ፣ ምሥጢራችንን አይቶ ለመሸፈን ሰው ሆነ ። የመበደል አቅማችን የመጽደቅ አቅም ሊሆነን አልቻለምና ምሥጢራችንን አውቆ ምሥጢሩን ሰጠን ። በጥምቀት ልጅነትን ፣ በሜሮን ማኅተመ መንፈስ ቅዱስን ፣ በንስሐ ስርየትን ፣ በክህነት አገልግሎትን ፣ በተክሊል አንድነትን የምናገኝበትን ምሥጢሩን አደለን ። ምሥጢር አውቆ ምሥጢር የሚሰጠውን ልጅሽን ወደድነው ። ሌላ ፍጡር ቢፈጥርስ ብለን ነበር ። እርሱ ግን ሰይጣንን እንኳ መደምሰስ አልፈለገም ። የስድስቱ ቀን ፍጥረት ረግቶ እንዲኖር መለኮት ወሰነ ። ተበላሸ ብሎ የማይጥል ፣ ወደቀ ብሎ የማይረሳ ፣ እልፍ አለኝ ብሎ በአንዲቱ መጥፋት የሚቆጭ መሆኑን ተረዳን ። በገሊላና በይሁዳ ከተሞች የፈረሰን አድሳለሁ ፣ የሞተን አድናለሁ እያለ ዞረ ። ሐኪሙም መድኃኒቱም እርሱ መሆኑ ተገለጠ ።

አዎ ምሥጢራችንን ለመሸፈን ምሥጢር ሰጠን ። ትዳሩ አውጥቶ የጣለውን ፣ ችግሩ አደባባይ ያወጣውን ፣ ዘመድ ምቀኛ የሆነበትን ፣ ወዳጆች የከሰሱትን ፣ ልጁ ያዋረደውን ሊሸፍን እርሱ ሰው ሆነ ። የእኛን ክፉ ዜና ወስዶ የእርሱን መልካም ዝና ሰጠን ። ዕራቁቱን የቆመውን ሊጋርድ ፣ ዘመን የካደውን ዘመን ሊሰጠው ሰው ሆነ ። በእንግዶች ማደሪያ ስፍራ ያልተገኘለት ፣ ገና በፅንስ የተገፋው ኢየሱስ ፣ በጠዋቱ ለተጠሉት ቤዛ ሆናቸው ። ቅድስት ማርያም ሆይ ነፍሳችን የተገፋውን ልጅሽን ባሰበች ጊዜ በመገፋትዋ ደስ አላት ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 29 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ