የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በልጅነቴ ያነበብኩት

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ                                                  አርብ  መስከረም 23 / 2007

       የሰው ልጅ ከሚኖርበት የአየር ጠባይ የተነሣ አሊያም በበሽታ ይጠቊራል። ድህነትም ሰውን እንደሚያጠቊር ያየሁት ያንን የቀድሞ ሻለቃ የዛሬ ደቃቃ፣ የድሮ ጌታ የዛሬ ከርታታ የነበረውን ሰው ባየሁ ጊዜ ነው፡፡ ከእኔ ጋር አብሮኝ የሚዞር ይመስለኛል፡፡ አውቶብስ በምጠቀምበት ዘመን 0.25 ሣንቲም እየከፈለ ከሾፌሩ ኋላ በመሆን ለተቀመጠው ጥቂት፣ ለቆመው ብዙ ተሳፋሪ “ወገኖቼ” በማለት ልመናውን ሳይሆን ምሬቱን ይናገራል፡፡ ሰው የንግግር ክህሎትን ሳያጠና ደንበኛ ተናጋሪ ከሚሆንባቸው ነገሮች አንዱ የመከራ ሕይወት መግፋት ነው፡፡ ድሀን የሚሰማው የለም እንጂ ያ ሰው ብዙ የጥበብ ቃላትን ያወርደዋል፡፡ የቱን ይዞ የቱን መጣል ይቻላል? በማስታወሻ ለማስፈር የምሳፈረው በአውቶብስ፣ ሰው እንደ ማገር በሚጠቀጠቅበት መኪና ነው፡፡ የሚቻለው እንደ ምርኮኛ እጆችን ወደ ላይ መዘርጋት ብቻ ነው፡፡ እጅ ከወረደ ማንም አይተማመንም፡፡ መገለማመጥ፣ በሳል አሳቦ ማጉረምረም ይጀመራል፡፡

                ከአውቶብስ ወደ ታክሲ ቀየርኩ፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! ያም ሰው ሥራው ያው ልመና ቢሆንም የሥራ ቦታውን ቀይሮ ከስንት ዓመት በኋላ የሣር ቤት ታክሲ ውስጥ ገብቼ ሜክሲኮ አየሁት፡፡ ከሩቅ ሲመጣ በሾፌሩ መስተዋት በኩል አሻግሬ አየሁት፡፡ ወይ ጉድ የመከራ ዕድሜ ረጅም ነው በሚል ስሜት እያሰብኩት እያለ እንደ እኔ አሻግሮ ያየው አጠገቤ ያለው ወጣት አንደበቱ በድንገት ባረቀ፡- “ውይ ይህ ሰውዬ መጣብን አሁንስ ሰለቸን” አለ፡፡ ወደ እኛ ታክሲ እንደሚመጣ እርግጠኛ ሆኖ ምሬቱን ገለጠ፡፡ ውስጤ ስቅቅ አለ፡፡ እኔው ያልኩ መስሎኝም ደነገጥኩ፡፡ ከውስጤ ጋር ስታገል ያ ሰው ደረሰና ገና፡- “ወገኖቼ” ሲል ሾፌሩ የቅድሙ ንግግር ጆሮው ላይ ነበርና “ምነው ሰለቸኸን” አለው፡፡ ይበልጥ ደነገጥኩ፡፡ ያ የቀድሞ ሻለቃ የዛሬው ደቃቃ፣ ያ የቀድሞ አዛዥ ዛሬ ግን ታዝዞ መኖር እንኳ የጠፋው ሰው በታላቅ ፀጥታ ቢያንስ ለሦስት ደቂቃ ያህል ሾፌሩን ትክ ብሎ ማየት ጀመረ፡፡ ዝምታው ሾፌሩን ሳይቀር አስደነገጠው፡፡ ሁሉም ሰው ደንግጧል፡፡

               የዝምታው ክፍለ ጊዜ አለቀና ያ የቀድሞ ሻለቃ “ወንድሜ” ብሎ ሾፌሩን ማናገር ጀመረ፡- “ወንድሜ እንዳንተ ያሉ ሰዎች ሲገጥሙኝ በልጅነቴ ያነበብኩት ፍካሬ ኢየሱስ ትዝ ይለኛል፤ እንዳንተ ያሉ ሰዎች እንደሚመጡ አስቀድሞ ተናግሯል” አለው፡፡ አሁንም ታላቅ ፀጥታ ሆነ፡፡ በመቀጠል ለመሄድ እየተሰናዳ፡- “እኔ የተሸከምኩት ሳይሰለቸኝ ምነው አንተን ሰለቸህ” በማለት በችግር በጠቆረ ፊት ላይ በሀዘን ጠቊሮ ወደፊት ገሰገሰ፡፡ ታክሲው ወዲያው ሞላና ጉዞ ጀመርን፡፡ ከሾፌሩ አንሥቶ እስከ ተሳፋሪው ሁሉም ሰው በጥፊ እንደ ተመታ ጭው አለ፡፡ ከታክሲው የሞተር ድምፅ በስተቀር የሚሰማ ምንም ድምፅ አልነበረም፡፡ እኔም የታክሲውን ግማሽ ጉዞ ከፍዬ ሆዴ እየተርገበገበ ወረድሁ፡፡ “እኔ የተሸከምኩት ሳይሰለቸኝ ምነው አንተን ሰለቸህ” የሚለው ቃል እየተከታተለ ይጮኽብኛል፡፡ ሾፌሩን አይቼዋለሁ መተኛት የሚችል አይመስለኝም፡፡ ይህን ሰውዬ ምነው ዛሬ አስታወስኩት ካየሁት ዐሥር ዓመት አልፎኛል፡፡ ንግግሩ ግን አላረጅ ብሎ በውስጤ ይታደሳል፣ የዕለትም ድምፅ ሆኗል፡፡


               ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ከመግባቴ በፊት የመጣሁበት ታክሲ ውስጥ፡- “መልካም ቃል ምጽዋት ነው” የሚል ጥቅስ አንብቤአለሁ፡፡ ወይ ታክሲ የሚያስለቅስ፣ የሚያጽናና መልእክት ይዞ ይዞራል፡፡ የተመረሩት በሰው ንግግር መሆኑን በጥቅስ ይገልጹልናል፡፡ ድሮ በቃላቸው ዛሬ በጽሑፍ ይናገራሉ፡፡ “የቤትሽን አመል እዚያው” የሚል ጽሑፍ በእንያንዳንዱ ታክሲ ውስጥ የመኪናው ሊብሬ እስኪመስል ይገኛል፡፡ የዛሬው ታክሲ ግን፡- “መልካም ቃል ምጽዋት ነው” ይላል፡፡ ገንዘብ መስጠት ባንችል መልካም ቃል መስጠት ከተሳነን መጸለይ አለብን፡፡ ለድሀ ሣንቲም ብቻ ሳይሆን መልካም ቃልም ምጽዋት ነው፡፡ ምን ለድሀ ብቻ ለባለጠጋው የምንመጸውተው የነፍስ ምጽዋት የሆነውን መልካም ቃል ነው፡፡
               ያ ሾፌር የተናገረውን ቃል አሁን ሳስበው በውጭ አገር የሚኖር አንድ የምወደው ወንድሜ አብርሃም ሊንከን የተናገሩት ነው ብሎ ከሰዓታት በፊት የነገረኝን ቃል አስታወሰኝ፡- “አውርተህ ሞኝነትህን ከማረጋገጥ፣ ሳታወራ ሞኝ መሆን ይሻላል፡፡ እንደ ተጠራጠሩህ ይኖራሉ፡፡”
               “መልክ ምስክር ያሻዋል” ይባላል፡፡ ቆንጆ ነበርኩ የሚሉ ሰዎች ቆንጆ እንደ ነበሩ ለማመን ይከብዳል፡፡ ውበት ቅሬታ እንኳ ሳይተው ጥሏቸው ሄዷል፡፡ ከባለቤቶቹ ንግግር ይልቅ ያን ጊዜ ቆንጆ እንደ ነበሩ የሚያውቋቸው ሰዎች ሲመሰክሩ ትንሽ ተአማኒነት ይኖረዋል፡፡ ሰው ማንን ይመስላል? ቢሉ ኑሮውን ይባላል፡፡ የጠቆሩ ሁሉ ጥቁር ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ጥቁረት ሁሉ የተፈጥሮ ቀለም ላይሆን ይችላል፡፡ በረሀብ የጠቆሩ፣ በችግር የከሰሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ እገሌ ዘንባባ ነው ብለን ስንናገርለት የነበረ በችግር አጥሮ አይተነዋል፡፡ እገሌት እንቡጥ አበባ ትመስላለች ስንል በኑሮ ትግል ጠውልጋና ረግፋ አይተናታል፡፡ መልክ ማንም አይነካብኝም ብለን የምንከራከርለት የእኛ ሐቅ አይደለም፡፡ መልክ ተመላላሽ ነው፡፡ አንዱ ሰው ስንት ጊዜ ፈርሶ ሲሠራ አይተናል፡፡ በምድራችን በኢትዮጵያ ካሳለፍነው ደስታ ያሳለፍነው መከራ ይበዛል፡፡ ችግር ካስቸገረን ይልቅ በችግር ቀን እኛ የተጨካከነው ይብሳል፡፡ ዛሬ ጧሪ ያጡ አረጋውያን፣ በሜዳ የተበተኑ ሕፃናት እኛ የቤት ሥራችንን ያለመሥራታችን፣ ቃሉን ያለመተግበራችን ውጤት ናቸው፡፡ ባሕላችን ለእኩዮች ብድር የሚመላለስ እንጂ ለድሀ ቸርነት የሚያደርግ አይደለም፡፡ ለድሆች ሣንቲም የሚቸረችር እንጂ አንድን ሰው ነፃ ስለ ማውጣት የሚያስብ አይደለም፡፡ የማንጠቀምበትን ልብስ እንኳ ለመስጠት የምንሰስት ልብስን በዕቃ የሚለውጥ “ልዋጭ” ጠባቂ ነው፡፡ የተረፈንን እንጀራ ለድሀ የማንሰጥ ድርቆሽ ይሆናል የምንል ነን፡፡ የጠገብነውን ሥጋ ለሌላቸው ከመስጠት እንደ ነብር አትልተን የምንበላ ነን፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ በዓለም ላይ እንደ እኛ ያለ ክርስቲያን የለም ብለን የምንናገር ደፋሮች ነን፡፡ ለነገሩ እንደ እኛ ያለ ክርስቲያን በዓለም ላይ የለም፡፡ ጠንቋይ ቤት አድሮ ማልዶ ለቅዳሴ የሚደርስ፣ ሦስት ሚስት ይዞ ልቁረብ የሚል፣ ላልኖረላት ሃይማኖት እሞታለሁ የሚል፣ ኢትዮጵያዊነትና ክርስቲያንነት የተምታታበት፣ ወኔና ወንጌልን ያለየ…፡፡
               ያ ሻለቃ ከመቀበል ይልቅ መስጠት ያስመረረውን ወይም ሰው ለሰጠ የሚበሳጨውን ሾፌር፣ ሾፌሩ የወከላቸውን ብዙዎችን ተቸ፡፡ በዓለም ላይ አራት መከራ አሉ ቢባል የመጀመሪያ የሚሆነው የሰው ፊት ነው፡፡ የሰው ፊት መራራ፣ ስጦታውም ዕዳ ነው፡፡ እኛስ ከባለቤቶቹ በላይ ሰልችቶን ይሆን? እያዘንን ያለነው ለወደቁት ነው ወይስ የወደቁትን ላየ ዓይናችን ነው? ድሆችን ለማየት የጠላነው አርቴፌሻል ደስታችንን ስላበላሹብን ነው ወይስ ቅምጥልነታችንን ስላጋለጡብን ነው? ድህነትን ነው የጠላነው ወይስ ድሆችን ነው? እነዚያ ባለ ትዳሮች ሁልጊዜ ሰላም ማጣታቸው ነው ያሳዘነን ወይስ ሽምግልና መጠራታችን? እነዚያ የተካሰሱት ወንድማማቾች የሰለቹን በደረቁ ስለሚያማክሩን ነው ወይስ ከፍቅር ገንዘብ ስለበለጠባቸው? ከእኛ ስሜት በላይ የተቸገሩት ሊያሳዝኑን፣ ካሉበት ማጥ እንዲወጡ ልንጨክን ይገባል፡፡ የእኛ ትርፍ ነገር ለሌሎች ዋናቸው ሊሆን ይችላል፡፡ የእኛ አንድ ቃል ለሌሎች ሰላም ሊሆን ይችላል፡፡ ከተሸከሙት በላይ አይክበደን፡፡ “የምጣዱ ሳለ የእንቅቡ ተንጣጣ” እንዲሉ፡፡
      እኛስ በልጅነታችን ያነበብነው ትዝ ይለን ይሆን? በልጅነታችን ያነበብነው ምንድነው?
               የሰው ልጅ ከትምህርት ቤት ይልቅ ከማኅበረሰቡ የሚማረው ይበዛል፡፡ የመጀመሪያዎቹ አስተማሪዎቻችንም ወላጆቻችን ናቸው፡፡ ወንድ ልጅ ከአባቱ ያየውን በሚስቱ ላይ፣ ሴት ልጅም ከእናቷ ያየችውን በባሏ ላይ ትፈጽማለች፡፡ አባቱ እናቱን ሲደበድብ ያየ ልጅ እርሱም ሲያድግ ሚስቱን ይደበድባል፡፡ እናቷ አባቷን በደብተራ ሥራ ሥር፣ በጠንቋይ ምክር ስትይዝ ያየች ሴት ልጅ እርሷም ስታድግ ባሏን በፍቅር ሳይሆን በሰይጣን መንገድ ለመያዝ ትሞክራለች፡፡ ዛሬ በብዙ ሽንገላ እውነትን ለማጥፋት እየሞከርን ነው፡፡ “እንደ ቀድሞ ያሉ ባሎች ዛሬ የሉም የዛሬ ባሎች እጅግ ጥሩ ናቸው” እያልን ነው፡፡ የዛሬው ባል ሽንኩርት በመክተፉ ብቻ ከቀድሞ የበለጠ መባሉ ወይም ለሚስቱ በኤፍ ኤም ሙዚቃ በመምረጡ ብቻ ትልቅ መባሉ ስህተት ነው፡፡ ባለፉት ዘመናት ያላየነውን ሚስታቸውን በአሲድ የሚገድሉ፣ ዓይን የሚያወጡ ባሎችስ የዛሬ ባሎች አይደሉም? አዎ ያ የቀድሞ ሻለቃ የዛሬው ደቃቃ እንደ ተናገረው በልጅነታችን ያነበብነው ነው፡፡ አባቶቻችን እናቶቻችንን ወጪ ከለከሉ፣ እኛ ፍቅር ከለከልን፡፡ አባቶቻችን እናቶቻችንን ደበደቡ እኛ ገደልን፡፡ በልጅነታችን ያነበብነውን እኛ እየተገበርነው፣ በትንሹ ያየነውን በትልቁ እየደገምነው ነው፡፡ ችግሩ ያለው ከወንዱ ችግሩ ያለው ከሴቷ አይደለም፡፡ ችግሩ ያለው ከእኛ ነው፡፡
               ከቆሎ ትምህርት ቤት ጀምሮ ከእነየኔታ እስከ መምህር እገሌ በልጅነታችን ያነበብነው መልካም አይደለም፡፡ ክፉን ግን ይቅር አላልነውም እኛም እየተረጎምነው እንገኛለን፡፡ እነርሱ አነበቡ እኛ ተረጎምን፡፡ እነዚያ ማወቃቸው ለራሳቸው ብቻ የሚታወቃቸው፣ እውቀታቸው ሌሎችን ያልለወጠ፣ በትዕቢት ተነፍተው እንደ አንበሳ ገዳይ የሚፎክሩ፣ በመንፈሳዊ ቦታ ተቀምጠው መንፈሳዊ ያልሆኑ፣ የሰውን ምክር ላለመስማት መጻሕፍትን እናውቃለን የሚሉ፣ ከአንደበታቸው ደንቆሮ የሚለው ስድብ የማያባራ፣ ሰውን ለማወቅ ካህን ነው ወይስ ጨዋ? የሚሉ እነዚያ ትላንት ላይ አልቀሩም፡፡ እውቀታቸው ቢቀርም ስድባቸው ግን ዛሬም ይገዛናል፡፡ ዘመናውያን መምህራንም ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ዩኒቨርስቲ ያሉት ማንነታችንን አሳጥተው ያሳደጉን፣ ከእነርሱ ዘመን ጋር እያነጻጸሩ እንደ እኔ ለምን በኩራዝ አላጠኑም? እንደ እኔ ለምን የስድስት ሰዓት መንገድ ተጉዘው አልተማሩም? እያሉ በፈተና ዱላ የሚበቀሉ፣ የማስረዳት ምኞት የሌላቸው አላዋቂነታችንን ለመንገር ግን ስል የሆኑት መምህራኖቻችንን እኛም እየተካናቸው ነው፡፡ ባደረጉብን ነገር ያዘንን ብንሆንም ነገር ግን ማስመረር ደስ ይለናል፡፡ በክፋት የሚወዳደር ወገን ነንና እግዚአብሔር ይቅር ይበለን፡፡ አዎ በልጅነታችን ያነበብነው ትዝ ብሎናል፡፡ ክፉ ገዢዎች ክፉ አሳዳጊ የገጠማቸው፣ ክፉ ገረዶች ክፉ እመቤት የገጠማቸው እንደሆኑ እናያለን፡፡ ዛሬስ የምናየው፣ ዛሬስ የምናደርገው በልጅነታችን ያነበብነውን እያስታወስን ይሆን?
               የሚጻፈውን፣ የሚሮጠውን፣ የሚባጀተውን ስናይ የአድዋ ጦርነት መሰናዶን ያስታውሰናል፡፡ እነዚያስ ለጣልያን እኛ ግን ለወገናችን፣ እነዚያስ ጥይት ለያዘ እኛ ግን ወንጌል ለያዙ ሕጻናት መሆኑ ያሳዝናል፡፡ መስበክ፣ መዘመር፣ መጻፍ ቀላል አለመሆኑን የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ በሰለጠነው አገር ያሸልም ነበር፡፡ እኛ አገር ግን ያስወግዛል፡፡ አዎ ዛሬ የምናየውና የምንሰማው በልጅነታችን ያነበብነውን ያስታውሰናል፡፡  
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ