የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በረከት በማክበር ይገኛል

መልካም ጎረቤትህን አክብረው ። “ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት” የተባለውን አትርሳ ። ክፉ ጎረቤትህንም ውደደው ፣ ዕቃ አያውስህምና ዕቃ ያስገዛሃል ። እጅግ የተዋበች ጽጌረዳ እጅግ የከፋ እሾህ አላት ። ዓለምም የሚያምርና የሚያደማ ነገር የያዘ ነው ። አበባውን ብቻ ስታይ እሾሁ ያነቃሃል ፣ እሾሁን ብቻ ስታይ አበባው ያጽናናሃል ። እንዳለ ያለ እግዚአብሔር ብቻ ነውና ፀጉሬ ሸበተ ፣ መልኬ ጠቆረ ፣ ቆዳዬ ተሸበሸበ ፣ እግሬ አነከሰ ፣ እጄ ዛለ ፣ ዓይኔ ደከመ ፣ ደሜ ከፍ አለ ብለህ አትጨነቅ ። ሞትን ብትሸሸውም ያለማቋረጥ የምትጓዘው ወደ እርሱ እንደሆነ እወቅ ። ዛሬ የሌሎችን ሞት ትሰማለህ ፣ ነገ ደግሞ ያንተን ሞት ሌሎች ይሰማሉ ። ከፍታህን ከፍ ባለ ቃል ሳይሆን ከፍ ባለ ኑሮ ግለጠው ። ሕያው መንፈስ አለህና በቁሳቁስ አትመካ ። ወርቁ ይዞ በነሐስ መመካት አለማወቅ ነውና ። አንተ ለእግዚአብሔር ስትኖር ፍጥረት ላንተ ይኖራል ። ጓዳህን ለሁሉ አታሳይ ፣ ምሥጢርህን በአደባባይ አትግለጥ። ድመት ክፉ ትመስላለች ፣ ነገር ግን ሐፍረቷን አታሳይም ። ውሻ ደግ ነው ነገር ግን ሐፍረቱን አይደብቅም ። ዝርክርክ ደግ አትሁን ።
ሁሉም የራሱ ጥያቄ አለውና አንተ ብቻ ሙግት እንዳለብህ አታስብ ። ለአገር የመጣ በአንድነት ቢያዝኑት ይቀላል ። የግልህን ችግር ከአገር ችግር ጋር እኩል አድርገህ አትመልከት ። ለአገርህ ኑር እንጂ አገርህ ላንተ እንድትኖር አትፍቀድ ። “ሰው ቢሞት በአገር ይለቀሳል ፣ አገር ቢሞት በማን ይለቀሳል?” የተባለውን አትርሳ ።
አንድ የሙዚቃ መሳሪያ ማወቅ ፣ አንድ የስፖርት ዓይነት መሥራት ፣ አንድ ማስታወሻ ለትውልድ መጣል ፣ አንድ ችግረኛን ነጻ ማውጣት ፣ አንድ ሃይማኖት መያዝ ፣ አንድ የትዳር ኪዳን ማጽናት አስፈላጊ መሆኑን እወቅ ። እየቻልህ ንፉግ ፣ እያወቅህ እውቀትህን ሰዋሪ አትሁን ። በዓለም ላይ ከዘራፊዎች ይልቅ እያላቸው የሚጨክኑ ቀማኞች ናቸው ። እውቀቱንም የሚሰውር ሌላ ነገር አያውቅም ። ሙሉ በሙሉ የማያውቅ ፣ ሙሉ በሙሉም የሚያውቅ የለም ። አድርጌአለሁ ለማለት ማንኛውንም ነገር ያለ ውስጣዊ ግፊት አታድርግ ። ሐሰት ከእውነት ትይዩ ጎጆ ትቀልሳለች ፣ መኮረጅ ትችላለች ፤ መሆንን ግን አትፈልግም ። “ሰይጣንም ላመሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል” ይባላል ። ሰይጣን ሙሉ እውነትንና ሙሉ ውሸትን አይወድም ።
“ሸንጋዮች ሲገናኙ ሰይጣን እራቱን ሊበላ ይሄዳል” ይላሉ ። በዚህ ዓለም ላይ የሰይጣን ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አስመሳዮች ናቸው ። ዓይናቸውን በጨው ካጠቡ ፣ የቀኑን ዘፈን ከሚዘፍኑ ፣ ማሊያ እየለወጡ መጫወት ከሚችሉ ተጠንቀቅ ። አሁን የአራዊት ሥጋት የለም ፣ ደኑ አልቋል ። በፎቅ ጫካ ውስጥ ያሉት አራዊቶች እነዚህ ናቸውና ተጠንቀቅ ። እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውንም አያፍርም ። አንተ ያዝረከረከውን ሌላው እንዲሰበስብልህ አትመኝ ። አንተ የጠላኸውን አገርም ማንም ሊወደው አይችልም ።
ክፋት መሥራት የነገ መንገድህን በእሾህ ማጠር ነው ። ኃላፊነትህን እግዚአብሔር ያየኛል ብለህ ተወጣ ። አደራ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝህ መሆኑን አትርሳ ። ነገርን አታጓትት ። ዛሬ ማድረግ ሲቻልህ ለነገ ሥራህን አታስቀምጥ ። አመጋገብህን ልከኛና ጤናህን የማይጎዳ አድርገው ። የሰውን ዕድሜ ከሚያሳጥሩ ነገሮች አንዱ ቅጥ የሌለው አመጋገብ ነው ። ትንንሽ አስተሳሰብ ካላቸው ጋር አትጣላ ፣ ጥሉ ለእነርሱ ክብር ሲሆን ላንተ ግን ውርደት ነው ። ያጋጣሚ ፍቅር መልካም ነው ፣ እስኪበስል መጠበቅ ግን ወሳኝ ነው ። ሰውን ደግም ክፉ ብለህ በአንድ ቀን አትለካው ። በመጀመሪያ ቀን በጣም ጥሩ የመሰሉህ ላይሆኑ ፣ በመጀመሪያው ቀን ክፉ የመሰሉህ ክፉ ላይሆኑ ይችላሉ ። በእርጋታ መጓዝ እርጋታ የሌላቸው የሚያመጡትን አደጋ መቀነስ ነው ። አደጋ ባይቀርም መቀነስ የሚቻለው በጥንቃቄ ነው ።
ግዴታቸውን የማያውቁ መብታቸውንም ማወቅ አይችሉም ። ሦስት ዓይነት ጠባይ ያላቸው ሰዎች አሉ ፡- የመጀመሪያዎቹ ሁሉም የጋራችን ነው ብለው የሚያምኑ ፣ ሁለተኛዎቹ ፡- የእኔ የግሌ የሌላው የጋራችን ነው ብለው የሚያምኑ ፣ ሦስተኛዎቹ፡- የእኔ የሌላው ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው ። ሁሉም የጋራችን ነው ብለው የሚያምኑ አብሮ መኖር የሚያውቁ ናቸው ። የእኔ የግሌ የሌላው የጋራችን ነው ብለው የሚያምኑ ያልሰለጡ ሰዎች ናቸው። የእኔ የሌላው ነው የሚሉ መንፈሳውያን ሰዎች ናቸው ።
ክብር በትግል አይገኝም ፣ መፈራትም እውነተኛ ክብርን አያመጣም ። ክብር ከእግዚአብሔር ነው ። ፍቅር የሌለው ክብር ደረቅ ነው ፣ ክብር የሌለው ፍቅርም ዕድሜው ያጠረ ነው ። መጣር መልካም ነው ፣ ቢሳካ ደስታ ባይሳካ ከጸጸት የሚያድን ነው ። እውነትህን እንጂ ስሜትህን አትግለጥ ። ቁጣህን ተቆጣው ። ስስትህን ሰስተው ። ፍቅርህን አፍቅረው ። ክብርህን ግን አታምልከው ። ግምትህን አትመነው ፣ ነገር ግን አትካደው ። ካልሾሙህ በቀር ሹመትን አትመኘው ። ሹመትን ሁለት ነገሮች በጽኑ ያዋርዱታልና ከእነርሱ ተጠንቀቅ ፡- ዝሙትና ፍቅረ ንዋይ ።
እውነተኛ ደስታ ያለው ስታደርግ እንጂ ሲደረግልህ አይደለም ። ደስታ እንደ ምንጭ ነው ፤ ምንጭ ወደ ውጭ ሲፈስስ ይስቃል ። ደስታም ሌላው ሲረካ በማየት የሚመጣ ነው ። እግዚአብሔር አቅምህን በጉልበትህ ውስጥ ሲያስቀምጥ ፣ ደስታህን ግን በሌሎች ጉድለት ውስጥ አስቀምጦታል ። ለወዳጅህ በቁሙ አበባ መስጠት ፍቅርህን መግለጥ ነው ፣ በሞተ ቀን መስጠት ግን ክብርህን መግለጥ ነው ። በሰው ሞት ላይ ክብርህን አታደራጅ። ይመጣል ብለህ የመጣውን አትግፋ ። አይመጣም ብለህ በጭንቀት አትከፋ ። ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር መርሐ ግብር በመጓዝ ላይ መሆኑን አትርሳ ። አንተ ስትቆም አምላክህ ይቀጥላል ። በችግርህ አንተ ታዝናለህ ፣ አምላክህ ግን ችግርህን መለወጥ ይችላል ። ራእይን ያለ ችግር ፣ ልጅንም ያለምጥ መውለድ አይቻልም ። ሳትኖር አትሙት ፤ ሳትሞትም ሥራህን ፈጽም ። እውነተኛ ኪዳን በጣት ቀለበት ሳይሆን በልብ ፍቅር የሚገለጥ ነው ። ሰርግ የሌለው ትዳር ሊኖር ይችላል ፣ ትዳር የሌለው ሰርግ ግን ሊኖር አይችልም ። እግዚአብሔር ጥረትህን እንጂ ምኞትህን አያግዝም ። የሰው ትልቅነት የሚለካው ደስታን ብቻ ሳይሆን መከራንም በጸጋ በመቀበሉ ነው ። በበረሃው ዓለም ላይ ለምን አተኮሰኝ ማለት የትንሽ አስተሳሰብ ውጤት ነው ።
ማግኘት የሚያስደስተው ከመከራ ቀን ወዳጅ ጋር ሲካፈሉት ነው ። ድልም የሚያረካው ለራስ ሳይሆን ለአገር ሲከፈል ነው ። ሃይማኖትም በረከት ያለው ስለሌሎች ማሰብ ሲችል ነው ። ከኪስ ብዙ ገንዘብ በአእምሮ ያለ ትንሽ እውቀት ይበልጣል ። እውቀት ማለት ያልተመነዘረ ሀብት ማለት ነውና ። ቀኑ በጨመረ ቁጥር ያወቅኸው እየጠፋህ ይመጣልና ያወቅኸውን ዛሬ ተርጉመው ። ከሚያንስህ ጋር ለመርዳት ፣ ከእኩያህ ጋር ለጨዋታ ፣ ከሚበልጡህ ጋር ለምክር ተገናኝ ።
ችግረኛን ስታይ የተጨነቅህበትን ቀን አስበው ። በዚያ ቀን ማንም እንዲያልፍህ አትፈልግም ነበር ። አንተም አትለፍ ። እግዚአብሔር ላንተ የሚበቃህን ብቻ ሳይሆን የምትሰጠውንም አስታቅፎ ልኮሃል ። ሁሉ ባለ ራእይ አይሆንም ፣ ባለ ራእዩንም መንከባከብ ባለ ራእይነት ነው ። ትላንትን በሽማግሌዎች ፣ ዛሬን በትዳር አጋርህ ፣ ነገን በልጆችህ ማየት ትችላለህ ። በቁጥጥር ሥር የዋለ ችግር አያስፈራም ፣ የተሸነፈን ጦር ሕጻን ይማርከዋል፤ ለእግዚአብሔር የነገርከው ችግርም እንዲሁ ነው ። የሌላውን ስህተት ሲያወሩ የሚውሉ ማሰብ የማይፈልጉት ትልቅ ወንጀል ስላላቸው ነው ። ሲተች የሚውልን ሥራ ስጠው ። ለምን ይህ አልተደረገም የሚለውን እንዲያደርግ ኃላፊነትን አስታቅፈው ። ተቀምጠን ስናየውና ቆመን ስናየው ሁሉም ነገር ልዩነት አለው ። ከሺህ ምኞት አንድ እርምጃ ወደ ግቡ የተደረገ ጥረት ነው።
ከሞተ ደግ የቆመ ክፉ ያሳዝናል ። የሞተ ሰው ደግ የመሥራት አጋጣሚ የለውም ፣ የቆመ ግን ንስሐ የመግባት ዕድል አለው ።
ቤተ ክርስቲያን እስከ ዛሬ ትገፋለች ፣ የገፉአት እየወደቁ እርስዋ ግን ትኖራለች ። ከነቢያት አሻግሮ ማየትን ፣ ከሐዋርያት እውነትን መግለጥን ፣ ከወንጌላውያን የምሥራቹን ማዳረስን ፣ ከአስተማሪዎች ተክሉን ማጠጣትን ፣ ከእረኞች መንከባከብን ፣ ከሰማዕታት ቆራጥነትን ፣ ከጻድቃን ዓለም መናቅን ፣ ከደናግል በተሰጠን መኖርን ፣ ከመነኮሳት በኪዳን መጽናትን ፣ ከካህናት ምሥጢር መሰወርን ፣ ከሊቃውንትን ቃለ አሚንን ፣ ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ትሕትናን ተማር ። እግዚአብሔር ያከበረውን ማክበር በረከት እንዳለው አትርሳ።
የደስታ ቋጠሮ/20
ተጻፈ አዲስ አበባ
ሐምሌ 30/2010 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ