መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » በርኅራኄ የሚቀሰቅሰው እጅህ

የትምህርቱ ርዕስ | በርኅራኄ የሚቀሰቅሰው እጅህ

በውስጤም በዙሪያዬም ካለው አየር ይልቅ ለእኔ የቀረብከው እግዚአብሔር አመሰግንሃለሁ ። በነፍስ ግስጋሴ የምትገኘው ፣ መድረሻን ውብ የምታደርገው ፣ ለደከመው አዲስ ኃይል የምትሰጠው ቡሩክ ተስፋ ሆይ አመሰግንሃለሁ ። የናቅሁት ስህተት ሲበረታብኝ ፣ ሰው እንዴት በዚህ ይወድቃል ያልሁበት ገዥ ሁኖ ሲመጣብኝ ፣ ራሴን በድካም ፣ አንተን በመምህርነትህ አለማወቄ ነውና ይቅር በለኝ ። የናቁት ያደርጋል ዕራቁት የተባለው ደርሶብኛልና አቤቱ አስበኝ ። ክፋትን አንድ ጊዜ ፣ ደግነትን ሁለት ጊዜ አይ ዘንድ ዓይኖቼን ክፈት ። ክፋትን አንድ ጊዜ ማየቴ ለመጠንቀቅ ፣ ደግነትን ሁለት ጊዜ ማየቴ ለመልካሙ ዋጋ ለመስጠት ይሁንልኝ ። እንደ መርማሪ ፖሊስ የሰውን ንስሐ የምቀበል ካህን ፣ አማክራለሁ እያልሁ ያለ ፈቃዱ የሰውን ውስጥ የምበረብር አካሚ እንዳልሆን ፣ ከሁሉ በላይ አድምጡኝ ለሚሉ ጆሮዬን እንዳውስ እባክህ እርዳኝ ።

ከሐሰት ይልቅ እውነት ፈታኝ ስትሆንብኝ ፣ ከመልካም ቃል ይልቅ የጥመት ቃል ሲቀለኝ እየሰጠምሁ ነውና እባክህ እንደ ጴጥሮስ አድነኝ ። በሚያወያየው ርእስ መጣላት ፣ በሚያከባብረው ጉዳይ መገዳደልን ከእኔ አርቅ ። እኔ ተጠቅሜበት ቀፎ ያደረግሁትን ፣ ሰዎች ተጠቅመውበት የጣሉትን ማንነቴን አንተ የክብር ዕቃ አድርገህ ተጠቀምበት ። ፍጡርን የሚያከብር ፈጣሪው ፣ ሥራን የሚያውቅ ሠሪው ነውና ካልፈጠሩኝ ክብርን መጠበቅ ከእኔ አርቅ ። ለክፋት የተነሣሡ አእምሮዎች ለሥራ እንዲነሣሡ ፣ በግድ የሚሠሩ እጆች ሐውልት እንዲሆንላቸው በውዴታ አንድ በጎ ነገር እንዲሠሩ አንቃን ። እውነት የደቦ ፍርድ ሳትሆን ያንተ ሚዛን እንድትሆን አግዘን ። ብዙኃን ከተስማሙበት ውሸት አድነን ።

ጌታ ሆይ ውዝግብ ውስጥ ስገባ የቀኙን አድራሽ መንገድ ፣ በነቀፌታ ውስጥ ሳልፍ “ኑ እናንተ የአባቴ ቡሩካን” የሚለውን ምስጋናህን እንዳስብ እለምንሃለሁ ። በዘለፋ ውስጥ “ልጄ” የሚለው ያንተ ድምፅ ፣ በሐሜት ውስጥ “አንተ ጎበዝ ተነሥ” የሚለው ሬሳን ጎበዝ ባይ አፍቃሪነትህ ፣ በማንቀላፋት ውስጥ በርኅራኄ የሚቀሰቅሰው እጅህ ከእኔ ጋር ይሁን ። አሜን ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 20 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም