የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በሰላም መሄድ

“አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ” ዘፍ. 15 ፡ 15 ።

ይህ ዓለም የርክክብ ዓለም ነው ። አረካካቢዎቹም ልደትና ሞት ናቸው ። ልደትና ሞት ወሳኝ ኩነት ናቸው ተብለዋል ። ሰው ላያገባ ፣ ላይመረቅ ይችላል ። ሰው ሁኖ ግን ያልተወለደና ሰው ሁኖ የማይሞት የለም ። ልደት ባይኖር ኖሮ ሞት ይህን ዓለም ባዶ ያደርገው ነበር ። ሞት ባይኖርም የሰው ልጅ እንደ ንብ ተነባብሮ ለመኖርም ይሳነው ነበር ። ወደ ትልቁ አዳራሽ ለመግባት ልደት መግቢያ በር ነው ። ሞትም የመውጫ በር ነው ። የተወለድንበት ቅርጽ በር ሲሆን ስንሞትም የሚጠብቀን መቃብር የበር ቅርጽ ያለው ነው ። በመግቢያ በር የሚገቡ ምንም ያልያዙ ሊሆኑ ይችላሉ ። ወደዚህ ዓለም ስንመጣም ባዶ እጃችንን ፣ ዕራቁት ገላችንን ይዘን መጥተናል ። ደግነትም ክፋትም ያልነበረን ፣ ባለማወቃችንና በእርዳታ ፈላጊነታችን ሁሉ የሚወደን ማሙሽ ነበርን ። በመውጫ በር የሚወጡ ብዙ ዓይነት መልክ አላቸው ። ባዶ እጃቸውን የሚወጡ አሉ ። የሚፈልጉትን ሳያውቁ ፣ የሚፈልጉትን ሳያገኙ ፣ ገንዘብ ሳይዙ ሰዎች ባዶ እጃቸውን ይወጣሉ ። በዚህ ዓለም ኑሮ ተስፋ ቆርጠው ፣ እንደ እርጉዝ በሚያቅበጠብጥ ምኞት ሲጎመዡ ኖረው ፣ ሁሉንም ነገር በዜሮ በሚያባዛ ፍልስፍና ተወጥረው ባዶ እጃቸውን የሚሰናበቱ አሉ ።

የሚያስፈልጋቸውን ይዘው የሚወጡ ሰዎችም አሉ ። እነዚህ ሰዎች የሚፈልጉትን ከሚያስፈልጋቸው ነገር የለዩ ናቸው ። ቀኑን የኖሩበት ቀኑ ያልኖረባቸው ብልሆች ናቸው ። በዓላማ እንደ ተፈጠሩ በዓላማ ኖረው ያለፉ ናቸው ። እነዚህ ሰዎች አስቀድመው የሚፈልጉትን ጽፈው የገቡ ሲሆኑ አቅማቸውን በትክክል የተጠቀሙ ፣ የሚፈልጉትን ብድግ ብድግ አድርገው ጊዜአቸውን ያተረፉ ፣ አላስፈላጊ ወጪዎችን ያስወገዱ ናቸው ። የሚያዩት ሁሉ ዓይን አዋጅ ሳይሆንባቸው ፣ ሁሉም የእኔ ይሁን የሚል ስግብግብነት ሳይጫናቸው ፣ የቱን ልምረጥ ብለው ሳይምታቱ በሥርዓት ኖረው የሚያልፉ ናቸው ።

ዛሬ እንደ ተወለዱ ሕፃናት እኛም ተወልደናል ። ትላንት እንደ ሞቱት አባቶች ደግሞ እንሞታለን ። በእርሻ ላይ የተዘራው ስንዴ በመኸር ይሰበሰባል ። እንዲሁም በዚህ ዓለም ላይ የተዘራን የእግዚአብሔር ስንዴ ነን ። የጀመርነው በስንዴነት ነው ፤ መኸር የተባለው ሞት ሲመጣ ወደ ጎተራው ወደ ሰማይ እንሰበሰባለን ። ምድር የዘር ፣ የመኸር ቦታ ናት ። ሰማይ ጎተራ ነው ። በምድር ያላፈራ ወደ ሰማይ ጎተራ አይገባም ። ይህችን ጊዜያዊ ምድር ውድ የሚያደርጋት ዘላለማዊ ውሳኔ የምናደርግባት መሆንዋ ነው ። ሞት ከዚህ ዓለም ካሉት ወዳጆች ጋር ሲለየን በሰማይ ካሉት ወዳጆች ጋር ያገናኘናል ። በሰማይ ያሉት ደግሞ አባቶቻችን ናቸው ። የሚታየው ዓለም መንፈስ ሲሆን የማይታየው ዓለም ደግሞ የሚታይ ይሆናል ። በምድር ላይ አካላችን ሲታጣ መንፈሳዊ ተግባራችን ሲናገር ይኖራል ። በሰማይ ደግሞ አካላችን ይገኛል ፣ ሥራችንም ይከተለናል ።

የዚህ ዓለም ጉዞአችንን ስንፈጽም ለትውልድ ጥለን ስለምንሄደው ነገር ማሰብ አለብን ። ያን ጊዜ በሰላም መሞት ይቻላል ። ወደ ኋላ ያሳለፍነውን ጊዜ እያሰብን ፣ በባከነው ዘመን እንዳናዝን እያንዳንዱን ቀን ልንኖርበት ይገባል ። መወለዱን የሚጠራጠር እንደሌለ መሞቱንም የሚጠራጠር የለም ። መቼ እንደምንሞት እንጠራጠር ይሆናል ። መሞታችንን ግን አንጠራጠርም ። እርግጥ ስለሆነው ነገር ችላ ብለን እርግጥ ስላልሆኑ ነገሮች እንተጋለን ። ሞት ያለው በጦር ሜዳ ወይም በሆስፒታል ሳይሆን ሞት ይዘነው የምንዞረው ነው ። ሞት ከታላላቅ ጥሪዎች አንዱ ነው ። ልደት ጥሪ ነው ፣ ክህነት ጥሪ ነው ፣ ሹመት ጥሪ ነው ፣ ሞትም ጥሪ ነው ። ጥሪ ነውና ሰው በዕድሜ ፣ በበሽታ ላይሞት ይችላል ። አረጋዊው ተቀምጦ ሕፃኑ ፣ በሽተኛው ሳለ ጤነኛው ይሞታሉ ። ሞት አንዱ ላንዱ የማይከፍለው ባለቤቱ ራሱ የሚወራረደው ዕዳ ነው ። የማይቀረውን የሞት ዕዳ ከመክፈላችን በፊት በክርስቶስ መንገድነት መጓዝ ፣ በእውነትነቱ ነጻ መውጣት ፣ በሕይወትነቱ መዳን ያስፈልገናል ።

“አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ” ዘፍ. 15፡15 ።

በሰላም መሄድን ምን አመጣው ? ጠጥቶ የሰከረ ሰው ሰላምታ እየሰጠ ገብቶ እየተሳደበ ይወጣል ። በኃጢአት አረቄ የሰከረ ሰውም አሟሟቱን ያበላሻል ። በመጨረሻ ሰዓት ለእግዚአብሔር ክብር ፣ ለሰው ጥቅም የማይበጅ ሥራ ይሠራል ። በሰላም መሄድ ራሱን ለሚገዛ ፣ አገኘሁ ብሎ ለማይሻማ ሰው የተመደበ ዕድል ነው ። በሰላም መሄድን ካነሣን ዓለሙ ነገረኛ ነው ማለት ነው ። ነገር ይፈልገናል ፣ ይተነኳኮለናል ። በሽታው ፣ አግኝቶ ማጣቱ ፣ ከብሮ መዋረዱ ፣ ነግቶ መጨለሙ እነዚህ ሁሉ ነገረኞች ናቸው ። በሰላም መሄድ በረከት ነው ። በሰላም መሄድ የከፈቱትን ዘግቶ ፣ ያስቀየሙትን ይቅርታ ጠይቆ ፣ የበደሉትን ክሶ ፣ የቀሙትን መልሶ ነው ። ወደ አባቶችህ ትሄዳለህ ማለቱም ሞትህ አድራሻ አለው ሲለው ነው ። የአብርሃም አባቶቹ እነ አዳም ፣ አቤል ፣ ሄኖክ ፣ ኖኅ … ነበሩ ።

እግዚአብሔር አምላክ ሆይ በሰላም መሄድን አድለን ! የነፍሳችንን አድራሻ አንተው አሳውቀን! ሠርቶ አፍራሽ ፣ ለግሞ ፈራሽ ከመሆን ጠብቀን ! አሜን !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ