የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ሰኞ ነሐሴ 12/2006 ዓ.ም.
ከብዙ መባዘን በኋላ ወደ እግዚአብሔር ቤት የመጣ አንድ ወንድም ያን ቀን ተንበርክኮ ጸለየ፡፡ ኋላ ላይ እንዲህ አለ፡- “ስንበረከክ የትምህርት ቤት ጊዜዬ ትዝ አለኝ፣ ትምህርት ካቆምኩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ተንበረከክሁ፤ ያን ጊዜ ለቅጣት፣ ዛሬ ግን ለበረከት ተንበረከክሁ” በማለት አስደናቂ ምሥጢር ተናገረ፡፡ የትም አንበረከክም የምንበረከከው በመምህሩ ፊት ቅጣትን ለመቀበል፣ በወዳጅ ፊት ይቅርታ ለማግኘት፣ በእግዚአብሔር ፊት ባርኮትን ለማፈስ ነው፡፡ መንበርከክ መልካም ነው፡፡ ችግራችን የሚንበረከከው ስንበረከክ ብቻ ነው፡፡ ሸክም የተሸከመ ሲንበረከክ ሸክሙ ጉልበቱ መሬት ሳይነካ እንደሚወድቅ፣ ስንበረከክም ሸክማችን ፈጥኖ ይቀላል፡፡ በመንበርከክ ማንበርከክ ይቻላል፡፡ በየዕለቱ ተንበርክከን የምንለምነው እግዚአብሔርን ብቻ ነው፡፡ መንበርከክ ወይም ስግደት አምልኮ ነው የምንለው ለዚህ ነው፡፡ በእኛና በሰማይ መካከል ያለው ርቀት ከጉልበት እስከ መሬት ነው፡፡ ሰማይን በዝላይ መንካት አይቻልም፡፡ በመንበርከክ ግን ሰማይን እንነካለን፡፡ መንበርከክ በተንበረከከ ልብ ሲሆን የሰማይን ደጅ ያስከፍታል፤ እግዚአብሔር ለሚሸነፉለት ይሸነፋልና፡፡
መንበርከክ ብቻ ሳይሆን ወደ ሰማይ አንጋጠን፣ ወደ ላይ አትኩረን ከእግዚአብሔር በቀር የምንለምነው ማንም የለም፡፡ ይህም ለእግዚአብሔር የሚሰጥ የብቻው አምልኮ ነው፡፡ አዎ መምህሩ ሲያንበረክከን ያለ ፈቃዳችን፣ የበለጠውን ቅጣት በማሰብ እንበረከካለን፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ግን በፈቃዳችን ቀጣዩን በረከት በማሰብ እንበረከካለን፡፡ በወዳጅ ፊት ስንበረከክ ብዙ ጊዜ ጥለውን ይሄዳሉ፤ መሸነፍን ሰው ዋጋ አይሰጠውምና፡፡ እግዚአብሔር ፊት ስንበረከክ ግን አልፎን አይሄድም፡፡ እንኳን ፈልገነው ሳንፈልገው የፈለገን ነውና፡፡ ተንበርክከን የምናወራው፣ አንጋጠን የምንለምነው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
እግዚአብሔር በሰማይና በምድር የሞላ ነው፡፡ ዓይኖቹ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ያያሉ፡፡ ከእርሱ ውጭ የሆነ ግዛትም የለም፡፡ ከግዛት ውጭም ከሰማይና ከምድር ተርፎ ያለው እጅግ ሰፊ የሆነ አምላክ ነው፡፡ ዳርቻዎች በእርሱ ውስጥ ናቸው፡፡ ዘላለም ብለን የምንጠራው ቁጥር አልባ ዘመንም በእርሱ ውስጥ ነው፡፡ ግን ይህ አምላክ በሰማይ የምትኖር ይባላል፡፡ አዎ በሰማይና በምድር ምሉዕ ቢሆንም ስለ ክብሩ ግን በሰማይ ይኖራል ተብሎ ይታመናል፡፡
ጌታችን ያስተማረው ታላቁ ጸሎት “አቡነ ዘበሰማያት- በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ” በማለት ይጀምራል /ማቴ. 6፤9/፡፡ በሰማያት የምትኖር የሚለው ቃል እግዚአብሔር በአንድ ስፍራ ሳይሆን በትልቅ ግዛት መኖሩን ይገልጣል፡፡ ምድር ብለን ስንጠራ እንኳ ዓለመ- ምድር ኘላኔቶችን ሁሉ ጥልቆችንም ያካትታል፡፡ የምድር አካል እጅግ ሰፊ ነው፡፡ እነ ኤልያስ በአካለ ሥጋ የሚኖሩበት ብሔረ ሕያዋንን ሳይቀር የሚጨምር አዳም ቀድሞ የነበረበትን ገነት የሚያካትት ሰፊ ግዛት ነው፡፡ ሰማያትን ስናነሳ ደግሞ በጣም ሰፊና ውብ ነው፡፡ አይሁዳውያንና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያምኑት ሰማያት ሰባት ናቸው፡፡ የሚጠፋው ምድር እንዲህ ባለ ጥበብና ውበት ከተሠራ ዘላለማዊ ሰማያት ደግሞ በበለጠ ውበት እንደ ተሠሩ እናምናለን፡፡ እግዚአብሔር በሰማያት የሚኖር አባታችን ነው፡፡ ሦስት ክንድ ከስንዝር ቦታ የምትችለውን ሰው አባት ብለን ስንጠራ ካላፈርን በሰማያት የሚኖረው፣ ፈጥሮ የሚገዛው ልዑለ ባሕርይን አባት ብለን መጥራት እጅግ የሚያኮራ ነው፡፡ ይህ አምላክ በሰማያት የምትኖር ተባለ፡፡
1. ስለ ልዕልናው በሰማይ ይኖራል፡- ግዛቶች ሲያልፉ መንግሥታት ሲለዋወጡ ታሪክ ሲቀመር፣ ወቅት ሲገሰግስ እርሱ ሁሉን እየታዘበ በዙፋኑ ይኖራል፡፡ በንጉሡ ፊት ሕዝብና ሠራዊት እጅ እየነሡ እንደሚያልፉ በእግዚአብሔር ፊትም ታሪክና ዘመን እጅ እየነሡ ያልፋሉ፡፡
2. በሰማያት የምትኖር መባሉ ከምድራውያን አማልክትና አባቶች የተለየ ስለሆነ ነው፡- እርሱ አምልኮ ተገብቶት የሚመለክ፣ አምላክ ስለሆነም የሚመለክ ነው፡፡ አባትነቱም ወደር የለውም፡፡ ምሳሌም አይገኝለትም፡፡ ፈጣሪ አባት፣ ፈጣሪ አምላክ ብለን በአጭሩ ከመግለጥ በቀር ምንም ማለት አንችልም፤እንደ ምድራዊ አባት ወልዶ የሚክድ፣ የሚጨክን፣ በትኖ የሚሞት አይደለም፡፡ ልዩ አባት ነውና ከምድራውያን አባቶች ሲለየው ሰማያዊ አባት ይለዋል፡፡
3. በሰማያት ሳለ ከምድራውያን ጋር ኅብረት ያደርጋል፡- እኛ ከሰለጠነ አገር መጥተን ያልሰጠነ አገር እንጠየፋለን፣ ከመኪና ወርደን መሬት መርገጥ እንሰቀቃለን፡፡ እግዚአብሔር ግን በሰማያት ሳለ ከእኛ ከትቢያዎቹ፣ ታጥበን ከማንጠራ አፈሮች ጋር ኅብረት በማድረጉ ልንደነቅ ይገባል፡፡
በሰማያት የምትኖር የሚለው የውዳሴ ቃል በብሉይም በአዲስ የተለመደ ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት፡- “በሰማይ የምትኖር ሆይ÷ ዓይኖቼን ወደ አንተ አነሣሁ÷ እነሆ÷ የባሪያዎች ዓይኖች ወደ ጌታቸው እጅ እንደሆነ÷ የባሪያይቱም ዓይን ወደ እመቤትዋ እጅ እንደሆነ÷ እንዲሁ እስኪምረን ድረስ ዓይናችን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ነው፡፡ ማረን÷ አቤቱ÷ ማረን፤ ንቀትን እጅግ ጠግበናልና፤ የባለጠጎችን ስድብና የትዕቢተኞችን ንቀት ነፍሳችን እጅግ ጠገበች” ብሏል (መዝ. 122)፡፡
ባሪያው የጌታውን፣ባሪያይቱ የእመቤቷንእጅ የሚያዩት ለራሳቸውናለቤቱ አንድ ነገርን ፈልገው ነው፡፡ አማኝም የእግዚአብሔር ባሪያ ነው፡፡ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ የሚያንጋጥጠው ለሕይወቱ በረከት፣ ለእግዚአብሔር ክብር የሚሆን ነገርን ለመቀበል ነው፡፡ ባሪያ አማራጭ እንደማይጠቀም እንዲሁ አማኙ እግዚአብሔርን ይጠብቃል እንጂ አቋራጭ አምላክ አይፈልግም፡፡ የእግዚአብሔር ምሕረቱ ከንቀትና ከስድብ ያድናል፡፡እግዚአብሔር ሲምረን የሚቀርብን ጸጋ የለምና፡፡ “ማረኝ” የሚለው ጸሎት ትልቅ ጸሎት ነው፡፡ ባለጠጎች የሚሳደቡበት፣ ትዕቢተኞች በንቀት የሚያንጓጥጡበት ዘመን እንዲያበቃ፣ ክብር እንዲመለስ ዳዊት ይጸልያል፡፡
ዛሬም በመናቃችን፣በመሰደባችን የእግዚአብሔርን ምሕረት ልንለምን ይገባል፡፡ ምሕረቱ ባለጠጎችንባዶ እጃቸውን የሚሰድ፣ ምስኪኖችን የሚያጠግብ፤ ትዕቢተኞችንየሚያዋርድ ትሑታንን የሚያከብር ነው፡፡ እግዚአብሔር ሲነሣ ቦታ ያለዋውጣል፡፡
“በሰማይ የምትኖር ሆይ ዓይኖቼን
ወደ አንተ አነሣሁ”