ሐሙስ፣ የካቲት 29 2004 ዓ.ም.
ዛሬ የሴቶች ቀን ነው! አንዳንድ የታሪክ መዛግብቶች እንደሚስረዱት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መከበር የጀመረው እ.ኤ.አ መጋቢት 8/ 1909 ዓ.ም ጀምሮ በአሜሪካ ሀገር ነው፡፡ ይሄም ቀን እንዲከበር ያስፈለገበት ምክንያት ለሴቶች ክብርን፣ አድናቆትንና ፍቅርን ለመግለጽና እንዲሁም ሴቶች በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ ያስመዘገቧቸውን ስኬቶች ለመዘከርና በዓለማችን በማንኛውም መስክ ያላቸውን ጉልህ ተሳትፎ ቦታ ለመስጠት ጭምር እንደሆነ እነዚሁ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡
ባለፈው ዓመት የሴቶች ቀን መከበር የጀመረበት 100ኛ ዓመት በአሜሪካ ሲከበር የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ባደረጉት ንግግር የ2011 ዓ.ም የመጋቢት ወር ‹‹የሴቶች ታሪክ ወር›› እንዲሆን መግለፃቸው በወቅቱ ተዘግቦ ነበር፤ Secretary of State የሆኑት ሄላሪ ክሊንተንም ሴቶችና ልጃገረዶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ብቃትና ተሳትፎ የሚያሳድጉበት መርሐ ግብር እና ኢንሼቲቭ አቋቁመው እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበር በወቅቱ ተገልጧል፡፡
የዘንድሮው የ2012ቱ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የተባበሩት መንግሥታት ‹‹Empowering Women- End Hunger and Poverty!›› በሴቶች ተሳትፎ ረሀብና ድህነት ያብቃ! በሚል መርሕ እንዲከበር ወስኗል፡፡ በማንኛውም የዓለማችን ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ስኬት ያለ ሴቶች ትርጉም የለሽ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በሀገራችንም ታሪክ በአመራር ብስለታቸው፣ በአርቆ አሳቢነታቸው፣ በብልሃታቸው በእጅጉ ስማቸው የሚነሡ ሴቶች አሉን፡፡ እንደ ንግሥት እሌኒ፣ እቴጌ ምንትዋብ፣ እቴጌ መነን፣ እማሆይ ገላነሽ… በጥቂቱ የምንጠቅሳቸው ናቸው፡፡ ባለፈው ሳምንት በዚህ ብሎጋችን ላይ የዘገብንበት የዐድዋው ድልም ያለ እቴጌ ጣይቱ ጀግንነት፣ ምክርና የጦር ስልት ፍሬያማ ሊሆን የማይችል እንደነበር የተለያዩ የታሪክ ጸሐፍት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሴቶችን ማክበር፣ መውደድ ለልፋታቸውና ለድካማቸው ቦታ መስጠት ከቃላት ጋጋታና ከመፈክር ያለፈ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ሴት ልጅ እህት፣ ሴት ልጅ እናት፣ ሴት ልጅ ሚስት ሴት ልጅ ሀገር ናት! ሴት የኑሮ ምሥጢረኛ፣ የፍቅር ማዕከል ናት፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ እንኳን ቅድስት ሥላሴ ተብለው የሚጠሩት በሴት አንቀጽ ነው፡፡ አባቶቻችን የዚህን ምክንያት ሲያብራሩም ሴት የርኅራኄ፣ የፍቅር ምንጭና የሕይወት ምሥጢር በመሆኗ የፈጣሪ ተምሳሌት እንደሆነች ይገልፃሉ፡፡ ፍቅር የሆነው እግዚአብሔር በፍቅር ስለ ፍቅር ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር ሲያመጣው ፍጥረት የሚኖርበትና የሚገዛበት ደግሞም የሚንቀሳቀስበት ኃይሉ ፍቅር እንዲሆንለት በፍጥረተ ዓለሙ ሁሉ ላይ ይሄን ፍቅሩን ያለ ገደብ አፍሶታል፡፡
የአበቦች ውበት፣ የውቅያኖሶችና የባሕሩ መዘርጋት፣ ስፋትና ግርማ፣ የፀሐይ ብርሃን ሙቀትና ኃይል፣ የሌሊት ጨረቃ ውበት፣ ሰማዩን ያስጌጡት የከዋክብቱ ድምቀት፣ የደመናው የሰማይ ላይ ትእይንት፣ የተራሮች ግርማ፣ የአእዋፋትና የሸንተረሩ ምንጮቹ ልዩ ዜማ… እነዚህ ሁሉ ፍቅርን የሚተርኩ፣ የፍቅር የአምላክ ድርሰቶች ናቸው፡፡
ከነዚህም ሁሉ በላይ ደግሞ ፈጣሪ ምሳሌና አርአያ የሆነው በመላ እሱነቱ ፍቅር የተተረከበት የሰው ልጅ ድንቅ የሆነ የፍቅር ዓለም ነው፡፡ ይሄ የፍቅር ዓለም ያድግና ይበዛ ደግሞም ለፍጥረት ሁሉም ይትረፈረፍ ዘንድ የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ የሆነ፣ በፈጣሪ የፍቅር ድርሰት ውስጥ ዋና ተዋናይ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር የሰው ልጅን ከምድር አፈር አበጀው፣ የሕይወትንም እስትንፋስ እፍ አለበት፡፡ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያን አባቶቻችንም ገለጻ፡- ‹‹እግዚአብሔር በአምሳሉና በአርያው የፈጠረውን አዳምን አየው፣ ወደደው፣ ሳመውም›› ይሉናል፡፡ ድንቅ ገለፃ፣ ግሩም እይታ፣ ነፍስና አጥንት ድረስ ዘልቃ የአምላክን ፍቅር ብርታትና ኃይል የምትገልጽ ጥበብ ይሏል ይሄ ነው!
እግዚአብሔር ዘላለማዊ ፍቅሩን ያለ ገደብ ያካፈለውን አዳምን በዚህ ምድር ላይ ከገለጸው በኋላ የፍቅርን ብርቱ ኃይልና ጥበብ ለአዳምና ለፍጥረት ሁሉ የምትተርክ የፍቅር አርበኛ፣ የሕይወት ምሥጢርና የመኖር ጥበብ የሆነች፣ ረዳት የምትሆነው ብቸኝነቱን የምታስረሳው የአምላክ ሕያው ፍቅር ድንቅ ጥበብ የሆነችው ሴት የአዳምን/የወንዶችን ዓለም ተቀላቀለች፡፡ በዛን ጊዜ ፍቅር ምሉዕ፣ ሕይወትም ጣፋጭና ትርጉም ያላት ሆነች፡፡ አዳም የሕይወቱን ክፋይ ሴትን ከጎኑ ባገኛት ጊዜ ከፍጥረት ጋር በአንድነት ሆኖ ልዩ የሆነ የፍቅርን ዜማንና ቅኔና እንደተቀኘላት እንገምታለን፣ መላእክቱም ይህን ልዩ ፍቅር ጥዑም ዜማ ለማዳመጥና ለመሳተፍ በአንድነት የታደሙ ይመስለናል፡፡ አይ ድምቀቱ፣ አይ ውበቱ…! አንድ የጥንት የቻይናዎች አባባል አለ እንዲህ የሚል፡-
‹‹አንድ ወንድና ሴት በተፋቀሩ ጊዜ መላእክት ከሰማይ ሰማያት ወርደው በጎጆአቸው ዙሪያ ከበው ልዩ የሆነ የፍቅርን ዜማ በደስታ ያዜማሉ›› በእውነትም ትክክል ነው! በዔደን ገነት የተሰማው የፍቅር ዜማም ሰማዩን፣ አየራቱን፣ ተራሮችን፣ አድማሳትን፣ ውቅያኖሱንና ባሕሩን፣ እጽዋቱን፣ አእዋፋቱን፣ የባሕር ዓሦችንና አራዊቱን ሁሉ በፍቅር ዜማ ያዘለለ ነበር፡፡ አዳምም እግዚአብሔር ወደ እቅፉ ያመጣትን ሴት ባያት ጊዜ ይህችን ድንቅ የፈጣሪ የፍቅር ጥበብ እንዲህ ሲል በጥበብ ቃል አሞካሻት፡-
‹‹ይህች አጥንት ከአጥንቴ፣ ሥጋዋም ከሥጋዬ ነውና ሴት ትባል… አንቺ የሕይወቴ ምሥጢር የፍቅርን ማዕድ በሐሴትና በፍስሐ የምትሞይልኝ ነሽና ሕይወቴ ነሽ ሲላት ስሟን ሔዋን አለው፡፡›› በፍጥረት ማግሥት በእባብ የተንኮል ምክር ተሳስታ የፈጣሪን ትእዛዝ የተላለፈችው ሔዋን ስህተቷ በእሷ ሳይገታ ወደ አዳምም እንዲተላለፍ ሆነ፡፡ በዚህም ምክንያት ሞት ተፈረደባቸው፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲናችን አባቶች መተርጉማን ሕይወቴ ብሎ የጠራት ሔዋን በኋለኛው ዘመን የሰው ልጅ ፍቅር አገብሮት ከሰማየ ሰማያት የወረደው ወልድ ከእመቤታችንና ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆኖ በፍቅሩ ካሣ የሰውን በደል ሁሉ ተሸክሞ በመስቀል ላይ በዋለ ጊዜ የሔዋን ስህተት በእመቤታችን በድንግል ማርያም እንደተካሰ ያመሰጥራሉ፡፡ የሴት ልጅ ሕይወት የመሆን ምሥጢር ውሉ የሚመዘዘው ከዚሁ እመቤታችን በእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ውስጥ የተመረጠችና ብፅዕት ሴት ከመሆኗ ነው፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከጽንስቱ እስከ ውልደቱና እድገቱ፣ በምድራዊው አገልግሎቱና እስከ ፍጻሜው የመስቀል ሞት ድረስ ያልተለየችው እናቱ ድንግል ማርያም የሴትነትን ብርታትና ልዩ ምሥጢር፣ የእናትን ፍጹም ፍቅር፣ ትሕትና እና ርኅራኄ ያሳየችን ምሳሌያችን ናት፡፡ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጭምት፣ ነገሩን ሁሉ በጊዜው ይሆን ዘንድ በልቧ የምትጠብቅ ጥበብንና ማስተዋልን የተሞላች ‹‹ብፅዕትና የተመሰገነች ሴት›› እንደሆነች በመንፈስ ቅዱስ በኤልሳቤጥ አንደበት የተመሰከረላት እንዲሁም ፍጥረት ሁሉ በአንድ ቃል እስከ ለዘላለም ድረስ ብፅዕት መሆኗን የሚመሰክሩላት ከሴቶች ሁሉ የተለየች ክብር የሚገባት ሴትና የጌታችን እናት መሆኗን ወንጌላውያኑ ጽፈውልናል፡፡
ዛሬ ዛሬ በሀገራችን በተለይም ደግሞ በሥልጣኔ አየር ታውዳለች በምትባለው አዲስ አበባችን ሴቶችን በሚመለከት ያለው እውነታ ልብን በሐዘን ጦር የሚወጋ ነው፡፡ የሚወራውና በተግባር እያየነው ያለው እውነታ አራምባና ቆቦ እየሆነብን ነው፡፡ ሴቶችን ከቃልና ከመፈክር ባለፈ ልባዊ የሆነ ፍቅርና አክብሮት እንሰጣቸው ዘንድ ይገባናል፡፡ የክርስቲያን ምድር በምትባል ሀገራችን በሴት እህቶቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ጭካኔና ውርደት ቃላት ከሚገልጹት በላይ ለአእምሮ በእጅጉ የሚከብድ ነው፡፡ በሚስቶቻቸው፣ በእህቶቻቸውና በእናቶቻቸው ፊት ላይ መርዝ የሚደፉ፣ ዓይን የሚያወጡ፣ አሰቃቂ በሆነ መንገድ የሚገድሉ ወንዶች በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዙ ነው፡፡ ሴት እህት፣ ሴት ሚስት፣ ሴት እናት፣ ሴት ሀገር ናት ልትከበር ልትፈቀር የሚገባት እንጂ እንዲህ ዓይነት ጭካኔና ውርደት ልናሰቃያት አይገባም፡፡
በዘመናችን እንደምንታዘበው የወንድነትና የሴትነት ክብር ትርጉም የተደባለቀበት እየሆነ ነው፡፡ ያለ ፍቅር በሆነ መንፈስ ስለ ሴቶች መብት የሚነገሩትና የሚፎከሩ ፉከራዎች ወደባሰ ጥላቻን መናናቅ እየወሰዱን ነውና ቆም ብለን ልናስብ ይገባናል፡፡ ሴቶቻችንም ለወንድሞቻቸው፣ ለአባቶቻቸው እና ለባሎቻቸው የሚገባውን ክብርና ፍቅር ሊቸሯቸው ይገባል፣ በመብት ስም የምንታዘባቸው ያልተገሩ ባሕርያት ወዴት እየወሰዱን እንደሆነ እያየን ነው፡፡ ለሴቶችም ሆነ ለወንዶች ከፍቅር የበለጠ መብት፣ ከፍቅርም የሚልቅ ነጻነት የለምና በፍቅር እርስ በርሳችን እንከባበር፣ እንዋደድ፡፡ የሴቶች ቀን የወንዶች ቀን ነው! ወንድ ልጅ ወደኋላው ሲዞር እናቱ፣ ወደ ቀኙ ሲዞር እህቱ፣ ወደ ግራው ሲዞር ሚስቱ ሴት ናት፡፡ ወደፊትም በክርስቶስ በማመን መዳንን በእኩልነት አብሮ የሚካፈለው ከሴት ልጅ ጋር ነውና ሴትና ወንድ በፍቅርና በመተሳሰብ የሰማዩን ርስት በማሰብ ሊኖሩ ይገባል፡፡ የወንድና የሴት ኅብረት ምክንያቱ ኃላፊ የሆነው ፍላጎት ሳይሆን ሁሉን በሞቱ እኩል ካደረገው ከክርስቶስ የተነሣ በዘላለማዊ አሳብ ሊተሳሰሩ ይገባል!