የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በቃልህ ይባረኩ

“አቤቱ ቃልህ በሰማይ ለዘላለም ይኖራል” መዝ. 118፡89 ።

ቃል ያለህ እግዚአብሔር ሆይ ፣ ወዳጅነትህ ብርቱ ነው ። ወዳጅ ለወዳጁ ቃል አለው ። ቃል የልብ መልእክተኛ ነው ። ልብህን ያየንበት ቃልህ ቡሩክ ነው ። ራሳችንን ያገኘንበት ቃልህ ድንቅ ነው ። ለቃላችን ቃል ስትሆነው አፈ ማር እንባላለን ። ቃላችንን ቃልህ ሲቃኘው ከአንደበት ዳኅፅ እንተርፋለን ። አቤቱ ቃልህ በምድር ላይ ክብር ባያገኝ ቃልህ በሰማይ ለዘላለም ይኖራል ። ቃልህን መስማት የሚናፍቁ ቅዱሳን መላእክት በርግጥ አሉ ። ቃላችን በሚያዝበት ምድር ላይ ሁከት በዝቷል ፣ ቃልህ በጸናበት ሰማይ ግን ሰላም ጸንቷል ። በምድር ላይ ለሁልጊዜው አንቆይም ፣ በሰማይ ግን በዘላለማዊ ቃልህ እየጸናን ለዘላለም እንኖራለን ።

የካብነውን ስንንድ ፣ የሾምነውን ስናወርድ ፣ ቋሚ ወዳጅ ቋሚ ጠላት የለም ስንል ቃላችን በምድር ላይ ለዕለት አይቆይም ። ፖለቲካን ስንኖረው ፣ ኑሮን ፖለቲካ ስናደርገው በገዛ ቃላችን ደክመናል ። ቃልህ አገር አለው ። ቃልህ የቅዱሳን ምግብ ነው ። ቃልህ ነዋሪና የሚያኖር ነው ። ቃልህ የጊዜ ድንበርን የሚሻገር ነው ። በክንፍህ መዘርጋት ከጥፋት ቀን የጋረድከን አማኑኤል ሆይ ፣ ቃልህ ይድረሰን ! ሰማይን ያለ ባላ ፣ ምድርን ያለ ካስማ ያቆመ ቃልህ ያጽናን ! ሰማይን ከነግሡ ምድርን ከነልብሱ የፈጠረ ቃልህ እንደገና ይሥራን ። የልጅ ልጆቻችን በቃልህ ይባረኩ ። አሜን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 15 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ