የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በበጎ ፈቃዱ

“በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን ።” ኤፌ. 1 ፡ 5 ።

ቫላንታይን ዴይ /የፍቅረኞች ቀን/ እየተባለ የሚጠራው የጣኦት አምልኮ ፣ ዘመናዊ ስያሜና ልምምድ አግኝቶ በወጣቶች ዘንድ እየተከበረ ይገኛል ። ወጣቶችም የሚያከብሩት ራሳቸውን በማዋረድ በመሆኑ በዓሉ መንፈሳዊ ክብር የሌለው ነው ። በዚህ ቀን ወጣቶች ቀይ ለብሰው ፣ ቀኑን ሲውሉ ምሽቱን ደግሞ ደማቸው ፈስሶ ፣ ድንግልናቸውን አጥተው ያድራሉ ። በቀይ ባንዲራ የዋለው ተረፈ ጣኦት ፣ ቀይ መስመር ውስጥ በማስገባት የወጣቶችን ሕይወት ይቀጫል ። በዚህ ቀን ዘላቂ ሕይወታቸው የሚበላሽባቸው ወጣቶች የትየለሌ ናቸው ። የጥንት የጣኦት አምልኮዎች ከዝሙት ጋር ጥብቅ ግንኙነት አላቸው ። ዝሙት ሥጋን ፣ ነፍስንና መንፈስን የሚያረክስ በመሆኑ የአጋንንት ትልቅ መሥዋዕት ነው ።

ወደ መንፈሳዊው ዓለም ስንመጣ የፍቅር ቀን የሚባል የለም ። ፍቅር ቀን የለውም ፣ ዘላለማዊ ነው ። ያ ፍቅርም እግዚአብሔር ነው ። መንፈሳዊው ፍቅር ቀይ በመልበስ የተገለጠ ሳይሆን ደሙን ባፈሰሰልን በክርስቶስ ሞት ላይ ያበበ ነው ። ይህ ፍቅርም ወደ ንጽሕና የሚጠራ ፣ ዝሙትን የሚረታ ነው ። ወጣቶችንም እንኳን የሚጎዳውን ኃጢአት ለመተው ይቅርና ሕይወታቸውን ለሰማዕትነት ለመስጠት የሚያስጨክን ፣ እነ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለሰማዕትነት ያበቃ ነው ።

ባሕል የሚመስሉ ጎጂ ነገሮች ፣ በዓል የሚመስሉ ውድቀቶች ፣ ከሌላው ዓለም የተቀዱ የሚመስሉ ዘመናዊነት የተላበሱ የደፈረሱ ውኃዎች ሊታሰብባቸው ይገባል ። በዚህ በፍቅረኞች ቀን የመገናኛ ብዙኃን ሳይቀሩ አልጋ ቀረሽ ወሬ እያወሩ ፣ ስለተላላፊ በሽታዎች በሚነገርበት ዘመን ሞራልና ጤናው የወደቀ ትውልድ እያተረፉ ናቸው ። ይልቁንም ስሜት እንጂ እውቀት የሌላቸውን ወጣቶች በጭድ አጠገብ ያለ እሳት እየሆኑባቸው ያሉ ሚዲያዎች በሕግ ሊጠየቁ ፣ በሃይማኖት ሊወገዙ ይገባቸዋል ።

እኛ የምናከብረው የፍቅር ቀን የለንም ። ያከበረን ፍቅር ግን አለ ። ይህንንም ፍቅር የምናከብረው ዘወትር ለሌሎች መሥዋዕት በመሆንና በተለወጠ ሕይወት ነው ።

የእግዚአብሔር ፍቅር በጎ ፈቃድ ያለው ነው ። የዓለም ፍቅር ግን ክፉ ምርጫ ያለበት ነው ። ፍቅር እግዚአብሔር ነውና እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ግብር ሁሉ የፍቅር ስም የተሰጠው ውድቀት ነው ።

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /8

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 10 ቀን 2014 ዓ.ም.

እባካችሁ ለሌሎች አካፍሉት

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ