የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በተዘጋው የሚመጣ/2

 “ያም ቀን እርሱም ከሳምንቱ ፊተኛው በመሸ ጊዜ ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት ፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ፡- ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው ።”/ዮሐ. 20፡19 ።/
የጌታችንን መነሣት ቀድመው ያወቁ የሮማ ወታደሮች ናቸው ። ወዳጆቹ ሳያውቁ ጠላቶቹ አወቁ ። ሲሰቅሉት ከትሕትናውና ከፍቅሩ አልተማሩም ። መግደል እየቻለ መሞቱ ትሕትና ፣ ስለ ኃጢአተኞች ራሱን አሳልፎ መስጠቱ ፍቅር ነው ። ሲነሣ ታላቅ ብርሃንና ኃይልን አዩ ። በትሕትና ያልተሳቡ በግርማው  ፣ በፍቅሩ ያልተማረኩ በኃይሉ ቢማረኩ መልካም ነበር ። ሰው ወይ ትሕትና ወይም ግርማዊነት ፤ ወይ ፍቅር ወይም ኃይል ይማርከዋል ። ጌታችን ሰዎች ሁሉ በሚማረኩበት መንገድ ቢገለጽም አላመኑበትም ። ለማመን እንዲችሉ ራሱን አሳያቸው ። ለማመን ካልፈቀዱ ለፍርድ እንዲመቻቹ ምክንያት ያሳጣቸዋል ። ሰዎች በከተማ የተቀመጠውን አገልጋይ “የከተማ ቅዱስ አለ ወይ?” ይሉታል ። በበረሃ ያለውን መናኝ ሰባኪ ደግሞ “የምንኖረውን ኑሮ ፣ የምናልፍበትን ፈተና ሳያውቅ በእኛ የሚፈርድ እርሱ ማነው?” እያሉ ችላ ይሉታል ። ጌታችን በከተማ እየበላና እየጠጣ ፣ መጥምቁ ዮሐንስ በበረሃ እያጠመቀ ማገልገላቸው ተናባቢነት ያለው ፣ የሰዎችን ተቺነት ዝም ለማሰኘትና ለንስሐ ለማብቃት የተደረገ ነው ። ወደ ክርስቶስ ሲመጡ በዘላለም እቅፉ ይሰውራቸዋል ፣ ወደ ዮሐንስ ሲሄዱም ወደ ክርስቶስ ያመለክታቸዋል ። የሮማ ወታደሮች መነሣቱን ቢያረጋግጡም አላመኑበትም ። ማረጋገጥ ማለት ማመን አይደለም ። አረጋግጠው ያላመኑ አሉ ። ክርስትናን እንደ ምርምር ጣቢያ ቆጥረው የትምህርት ማዕረግ የሚደረድሩ የአምልኮ ልብ ግን የሌላቸው አያሌ ናቸው ። ክርስቶስን ማወቅ አስፈላጊ ቢሆንም ማወቅ ግን ከእርሱ ጋር ላለን ግንኙነት መጨረሻው አይደለም ። ክርስትና ከማወቅ ቀጥሎ ማመን ፣ ከማመን ቀጥሎ መኖር ፣ እንደ ገና ታውቆ ወደማይጨረሰው ክብሩ መገስገስ ነው ።

ወታደሮቹ ትንሣኤው እርግጥ መሆኑ ሪፖርት አድርገዋል ፣ የምሥራቹንም በቤተ መንግሥት በማለዳ አድርሰዋል ። በወታደራዊ ሙያቸው መሞቱን አረጋግጠው እንዲቀበር ፈቅደዋል ፣ አሁን ደግሞ መነሣቱን ሪፖርት አደረጉ ። ይህ ለእነርሱ መደበኛ ሥራቸው ነው ። የሃይማኖት ሰዎች ግን አንድ ነገር አስተማሯቸው ። ገንዘብ ተቀብለው ያዩትን እንዲክዱ ፣ ተሰረቀ ብለው እንዲያወሩ አግባቡአቸው ። የሃይማኖት ሰዎች ጋር ያለው ክፋት ረቂቅ ነው ። የዓለም ሰዎች ቢጣሉ ይፈነካከታሉ ፣ የሃይማኖት ሰዎች ውስጡን እንዴት እንስበረው ፣ ዘላቂ ሕመም እንዴት እናስታቅፈው ? ይላሉ ። ሰማያዊውንና ረቂቁን ነገር ያመኑ ሰዎች ካልኖሩበት እንዳመኑት መጠን ይክዳሉ ። ሰው የሚወድቀው በወጣበት ልክ ነው ።
መግደላዊት ማርያም ከወታደሮቹ ቀጥሎ ትንሣኤውን አየች ። ጴጥሮስና ዮሐንስም መቃብሩ ባዶ መሆኑን አረጋገጡ ። ጌታችንም ለመግደላዊት ማርያም ተገለጠ ። ቀጥሎ ለሴቶቹ ሁሉ ተገለጠ ። ለኤማሁስ መንገደኞች ተገለጠ ። የኤማሁስ መንገደኞችም እንደገና ወደ ኢየሩሳሌም ተሰብስበው ወደ ነበሩት ደቀ መዛሙርት መጡ ። እነርሱ ሲመጡ ጊዜው ምሽት ነበረ ። የኤማሁስ መንገደኞችም የክርስቶስን መነሣትና እንደ ተገለጠላቸው ሲተርኩ ሳለ ክርስቶስ ተገለጠላቸው ። ምስክርነታቸውን ሊያትም ተገለጠ ። ስለ እርሱ እያወሩ ሲሄዱ አብሯቸው በኤማሁስ መንገድ የተጓዘ ጌታ ስለ እርሱ ሲመሰክሩ በሰገነቱ ተገለጠ ። እርሱ ስሙ በተጠራበት አለ ። እርሱ የመሰከርነውን ሊያትም ይገለጣል ። ጌታችን ሕይወት ያዛላትን የመከራ ቋጥኝ ስትገፋ የኖረችውን መግደላዊት ማርያምን አስቀደመ ። እርሱ የደካሞችን ድካም ያውቃል ። ትንሣኤውንም ለእርስዋ ቀድሞ ባይገልጥ ኑሮ ትጎዳ ነበር ። ጌታ ቀብራ ለማረፍ ለመጣችው ፣ ለመሰናበትም ሽቱ ለያዘችው  አዲስ ምዕራፍ ከፈተላት ። ሰዓቱን የሚያውቅ አምላክ በሰዓቱ ይደርስልናል ። የኤማሁስ መንገደኞችም ተስፋ ቆርጠው ወደ ፀሐይ መጥለቂያ ይጓዙ ነበር ። እነርሱም በተሰበረ ልብ ፣ ተስፋ በቆረጠ መንፈስ እንዳያድሩ  ደረሰላቸው ። ምሽቱን ግን ለደቀ መዛሙርቱ ተገለጠ ። “አጥብቀው ያሰሩትን ዘቅዝቀው ይሸከሙታል” እንዲሉ ደቀ መዛሙርቱን ስለ ተማመነባቸው እስከ ምሽት ዝም አላቸው ። ቢሆንም እስከዚያው የምሥራቹን ይልክላቸው ነበር ። በቃሉ ቀኑን አውሎ በመገለጡ አሳደራቸው ። ነቢዩ፡- በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም አቤቱ ፥ አንተ ብቻህን በእምነት አሳድረኸኛልና ይላል ። /መዝ. 4፡8 ።/ በሰላም እንዲያንቀላፉ ፣ በእምነት እንዲያድሩ ተገለጠላቸው ።
ቀኑ የሁከት ፣ የመጠራጠር ነበርና ። ሞቶአል የሚለው ኀዘን ነው ፣ ተነሥቷል የሚለው ግን ጥርጣሬ ነው ። ሞት ቁርጥ ነው ፣ ጥርጣሬ ግን ሲወዘወዙ መኖር ነው ። ከካዱት በላይ የሚጠራጠሩት ሲታወኩ ይታያሉ ። ጎረቤት የሚረብሽ ጸሎት የሚጸልዩት ለዚህ ነው ። ያዩት ሰው ሁሉ ላይ መንፈስ አለበት እያሉ የሚገሥጹት ለዚህ ነው ። ምግቡ ላይ ጋኔን አርፏል እያሉ ሲባርሩ የሚውሉት ለዚህ ነው ። አንዱን እግዜር ማመን ትተው የዛርና የቃልቻ ስም እየዘረዘሩ ሲቃወሙ ፣ ያንን የደርግ መፈክር “ይውደም” ሲሉ የሚውሉት ለዚህ ነው ። በግብራችን የምንስመውን ዲያብሎስ ፣ በቃላችን መርገም ከንቱ ጨዋታ ነው ።
በአትክልቱ ስፍራ ለመግደላዊት ማርያም ፣ በመቃብሩ ቦታ ለሴቶች ፣ በኤማሁስ ለመንገደኞች ፣ በሰገነቱ ላይ ለሐዋርያት ተገለጠ ። ቀኑን በሙሉ ሰዎች ሲያደክሙት ዋሉ ። ዓርብ ሙሉ ቀን ለማስታረቅ የደከመው አሁን ደግሞ እንዲያምኑት ደከመ ። እርሱ ወደ ሰው ካልመጣ በኃጢአት ዓይኑ የጨለመው የሰው ልጅ ወደ እርሱ መምጣት አይችልም ። እኛስ ከልጅነት እስከ እውቀት ብዙ እንዳደከምነው ተስምቶን ይሆን ? ስንክድም ስናምንም አላምርብን እያለ አስቸግረነዋል ። ስንክድ ሰዎችን መንቀፍ ፣ አምነን ደግሞ ስንወጋገዝ መኖር እርሱን ያደክመዋል ።
አንዳንዴ ቀትሩ ይጨልማል ። ሙሉ ብርሃን ነው ሲሉት ድቅድቅ ጨለማ ይሆናል ። ምድርም ትከዳለች ። የሚረገጥ እስኪጠፋ እግር መደላደያ ያጣል ። ሰማይ ጠቁሮ ያስፈራል ። እግዚአብሔርም ዝም ያለ ፣ ከቀኑ ጋር ያደመ ይመስላል ። ባል በጫጉላ ቤት ሲሞት ፣ ልጅ ፊት ለፊታችን የጥይት እራት ሲሆን ፣ ጠዋት ጤነኛ የነበርነው ከሰዓት የአልጋ ቁራኝ ስንሆን ፣ ኬክ ይዘው ይመጡልን የነበሩ መርዝ ጋግረው የት ነው ? እያሉ ሲፈልጉን ፣ የቅጥር ተሳዳቢዎች የተሞሉትን ሳንቲም እስኪጨርሱ ሲሰድቡን ፣ አለሁ ያሉን አርባ ክንድ ሲርቁን ፣ እንኳን ሰውን ልባችንን ማመን ሲከብደን የሚያድነንን እንፈልጋለን ። ሁሉም ነገር ዘላለማዊ ጸጥታን የተላበሰ የሚመስልበት የተዘጋ ቀን አለ ። “አምላኬ ሆይ ለምን ተውኸኝ ?” የሚል ጥያቄ አዘል ልመና ፣ ከመጉዳት ስሜታችን የሚወጣ ጩኸት በውስጣችን ያስተጋባል ። የወዳጅ ፊት ቅጭም ቢል ሰማይ ግን አይጠቁርም እንል ነበር ፣ መኖሪያ ቤት እንጂ መርገጫ ምድር አጣሁ እንደማንል እርግጠኛ ነበርን ። ነገር ግን ሰማይም የሚጠቁርበት ፣ ምድርም የሚከዳበት ዘመን አለ ። ሁላችንም ዓርብ አለንና በዚያ ቀን ከተማውን እንዳልሞላን ከከተማ ውጭ እንደ ጉድፍ እንጣላለን ። ስንደሰት ዝም ያሉ ስንሰቀል ሊያዩ ይወጣሉ ። በምድም በሰማይም የተገፋን መስሎ ይሰማናል ። ትልልቅ ተስፋዎች ወደ ትልልቅ ፍርሃቶች ይለወጣሉ ። ዕድሎቻችን ሁሉ የክሳችን አንቀጽ ይሆናሉ ። ምድር ከድታን ስንጠለጠል ፣ ሰማይ ተቀይሞን ፊቱን ሲያጠቁርብን ። ቀትሩ ጨልሞ ሁሉ ሲተወን ፣ እግዚአብሔርም እንደ ሰው የሆነ ሲመስለን ፣ የጸለይነው ጸሎት እንደ ገደል ማሚቱ ለራሳችን መልሶ ሲሰማን ፣ ካህናት ከሳሽ ፣ ንጉሥ ወቃሽ ሲሆንብን ፣ ሚሊየኖች ለአንድ እኛነታችን ሲያድሙብን ያን ቀን የዓርቡን ባለ ጽዋ ፣ ክርስቶስን እናስብ ። በቀደመበት በድል ያስከትለናል ። ለቀኑና ለስሜታችን አሳልፎ አይሰጠንም ። ዓርብ ቀትሩ እንደ ጨለመ ፣ እሑድ እኩለ ሌሊቱ ይበራልናል ። ያን ቀን የምስጋና ደቦ ጠርተንም ውለታውን ለመዝለቅ ፣ ክብሩን ለመዘመር አንችልም ።
አቤቱ ሕዝብህ ነንና አድነን ፣ ርስትህ ነንና ጠብቀን ።
ይቀጥላል
የመስቀሉ ገጽ 9/ለ
ግንቦት 15 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ