የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በተዘጋው የሚመጣ /3/

 “ያም ቀን እርሱም ከሳምንቱ ፊተኛው በመሸ ጊዜ ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት ፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ፡- ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው ።”/ዮሐ. 20፡19 ።/
እርሱ አስቀድሞ፡- “ያከበሩኝን አከብራለሁ” ብሏል ። /1ሳሙ. 2፡30 ።/ ቅዱሳን ሴቶች ማልደው ወደ መቃብሩ ስለገሰገሱ እርሱም ማልዶ የምሥራቹን አሰማቸው ። “ለገቢህ ተንገብገብለት” ይባላል ። ገቢህ የተባለው ስትጠራው አቤት ለሚልህ ፣ ስትጮህ ለሚደርስልህ ፣ እሳት ውስጥ ስትገባ እሳት ገብቶ ለሚያወጣህ ፣ ሲከፋህ አብሮ ለሚከፋ ፣ ስትታመም ለሚያገላብጥህ ለእርሱ ተንገብገብለት ፣ ኑርለት ፣ አልቅስለት ፣ ራራለት ፣ ሁለመናህን ስጠው ማለት ነው ።  ጌታም ለገቢዎቹ ይንገበገባል  ። እግዚአብሔር ማለዳ የገቡትንና ሠርክ የገቡትን በፍቅር ቢቀበልም ማለዳ መግባት ቢያንስ የቀኑ ሐሩርና የት ልሄድ የሚለው ሥቃይ ፣ ሥራ ፈትነት የሚያመጣውን የልብ ውዝዋዜ እንዲቀር ያደርጋል ። ደግሞም ከነትጥቁ የተማረከና ትጥቁን አራግፎ የተማረከ እኩል አይደለም ። በማለዳ የገቡ ቆስለው የተማረኩ አይደሉም ፣ ትጥቃቸውን ወይም ጉልበታቸውን አባክነው የመጡም አይደሉም ። እኩል በክርስቶስ ብንድንም እኩል አንሸለምም ። ማልደው የገቡ ክብራቸው ከፍ ይላል ። ቅዱሳን ሴቶችና መግደላዊት ማርያም ማልደው ቢሄዱ ትንሣኤን ሰሙ ። ማልደው ወደ እግዚአብሔር በጸሎት የሚገሰግሱ የሚያቆምና የሚያጸና መንፈስን ያገኛሉ ።

ቀኑን ብቻ ሳይሆን ቀኑን የሚያውል ቃል እግዚአብሔር ሰጥቶናል ። ያንን  የሚያገኙ ማልደው ቃለ እግዚአብሔርን የሚያነቡ ናቸው ። ቀኑን ያለ ኃይል መዋል ከባድ ነው ። ከእንቅልፍ እንደ ነቃን እንቅልፍ ሲሰማን ፣ ተኝተን አድረን ድካም መልሶ ሲጫጫነን ፣ ተስፋችን ተሟጦ ፊታችን ሲጨማደድ ፣ የትዳር ጓደኞቻችንንና ልጆቻችንን በጠዋቱ በቍጣ ስናስደነብር ይህ ኃይልን ያለ መሞላት ችግር ነው ። ሰው ሁሉ ማልዶ ተነሥቶ ውኃ መኖሩን ያረጋግጣል ፣ ለቁርስ የሚሆኑ ነገሮች በቤት እንዳሉ ይፈትሻል ፣ ቆሞ ያደረው መኪናው ዘይት አፍስሶ እንደሆነ ያጣራል  ። ሰው ግን ስለ መኪናውና ስለ ቁርሱ የሚያስበውን ያህል ስለ ነፍሱ አያስብም ። የሥጋ ጥጋቦቻችን ሁሉ እርካታ ያልሰጡን የነፍስ ጠኔ ስላለብን ነው ።
እነ ጴጥሮስ የመነሣቱን ዜና በመግደላዊት ማርያም ሰሙ ፣ ሮጠው ወደ መቃብሩ በመገስገስ አረጋገጡ ። ነገር ግን ዝምታን መርጠው ዋሉ ። እስቀድመው የሰሙት ወንዶች ቢሆኑ ኑሮ ሰብአዊ ኩራታቸው የምሥራቹን ታግሠው እንዲውሉ ያደርጋቸው ነበር ። ደስታቸውን ሊያጋሩ ሁልጊዜም ፈቃደኛ ለሆኑ ሴቶች ጌታ ትንሣኤውን ገለጠ ። እርሱ ለማን ምን መንገር እንዳለበት ያውቃል ።
መግደላዊት ማርያም ከመቃብሩ ባዶ መሆን ፣ ከመላእክት ምስክርነት በላይ ራሱን ጌታን አግኝታ ትንሣኤውን አረጋግጣለች ። ያ ቀን የዓርብ ዕለት ተቃራኒ ነበር ። ዓርብ ከማለዳው እስከ ምሽት የኀዘን ቀን ነበር ። እሑድ ደግሞ ከማለዳው እስከ ምሽት የምሥራች ነበር ። የዓርብን መከራ ያመኑ የእሑድን ደስታና ክብር ማመን አልቻሉም ። ጭንቅን የሚቀበል ደስታን የማይቀበል ፣ የሰይጣንን ሀልወት የሚያምን የእግዚአብሔርን መኖር የሚክድ ፣ በአዳም መኰነኑን የሚቀበል በክርስቶስ መዳኑን ችላ የሚል ፣ የምድርን አታካችነት የሚናገር የሰማይን ደስታ የማይቋደስ አእምሮ የሚደንቅ ነው ። ክፉ ነገር አገሩ እዚህ ነውና ይፈጥናል ። መልካም ነገር ደግሞ ይዘገያል ። በሰዎች ተጎዳሁ እያለ በክርስቶስ የማይጠቀም ፣ በምድር ተገፋሁ እያለ የሰማይን ምሰሶ የማይጨብጥ ፣ አጋንንት ተሰለፉብኝ እያለ የመላእክትን ተራዳኢነት የማይቀበል ፣ የሚጠሉትን እየተከተለ ለወዳጆቹ ጀርባው የሚሰጥ ፣ ቀሙኝ ብሎ እያለቀሰ ሲሰጡት የሚጠራጠር ፣ የክፋት ዜና መረረኝ እያለ የልማት ዜናን የማይወድ … የሚደንቅ ፍጡር ነው ። ሰው ሊጸልየው ከሚገባ ጸሎት አንዱ፡- “መከራዬን አስረሳኝ” ብሎ ነው ። አስተዳደጋቸው አኗኗራቸውን የሚዋጋባቸው ብዙ ናቸው ። የማጣት ዘመናቸው ዛሬ ወርቅ እንዳይለምዱና እንዲያግበሰብሱ ያደረጋቸው አያሌ ናቸው ። አንድ ወንድ ጎዳኝ ብለው ሺህ ወንድ የሚበቀሉ ፣ አንድ ሴት አታለለችኝ ብለው ሺህ ሴት የሚጠራጠሩ ብዙ ናቸው ። የዛሬው ኑሮ የሚበጠበጠው የትላንቱን መርሳት ባለ መቻላችን ነው ። ዓርብን ስላልረሱ እሑድን ሲተክዙ ዋሉ ። እግዚአብሔር ሲክስ ከተጎዳነው በላይ ነው ።
የትላንቱን መዘባበቻ መሆን ፣ የትላንቱን ከፀጉር የበዙ ጠላቶች ማስተናገድ ፣ የትላንቱን በአደባባይ መራቆት ፣ የትላንቱን የወደዱትን ማጣት ፣ የትላንቱን የአስገባሪዎች ክፋት ፣ የአስጨናቂዎችን ዘንግ ፣ የጫንቃውን በትር ፣ የጀርባውን ሰንበር መርሳት የዛሬን ትንሣኤ ለመቀበል አስፈላጊ ነው ። ደርግ አሥራ ሰባት ዓመት ጃንሆይን አልረሳም ፣ ሲራገም ነበር ። ሬሳ መደብደብ ጀግና አያሰኝም ። ያንን በደል ማውራት ጥቅም የለውም ። መካስ ግን ጥቅም አለው ። ደርግንም እስካሁን እንራገማለን ። አካሉ ሂዶ መንፈሱ አልሄድ ብሎን እንጨነቃለን ። የትላንቱን ተምረንበት መርሳት ያስፈልጋል ። ዛሬ ላይ ትላንትን መኖር አለማወቅ ነው ። እገሌ ጎዳን ከማለት እኔስ ምን ጠቀምኩኝ ? ማለት እውነተኛ ጥቄ ነው ። ሁለት ነገሮች ለሕክምና አስቸጋሪ ናቸው፡- ራስን አለመቀበልና ትላንትን አለመርሳት ። ክረምትና በጋ ፣ ደስታና ኀዘን የሕይወት ዑደት እንጂ አደጋ አይደሉም ።
ደቀ መዛሙርቱ የጌታን መነሣት ጠብቀዋል ። ሲነሣ ግን ማመን አቃታቸው ። ትልቅ ደስታ ማመን ይከለክላል ። ይህ ቅዱስ አለማመን ነው ። እየጠበቁም አለማመን አለ ። እየጠበቁ አይሁድ ክርስቶስን ሰቀሉ ። እግዚአብሔርን የማንቀበለው በእኛ ሥዕል ስለምንጠብቀው ነው ። እግዚአብሔር በእግዚአብሔር ብቻ የታወቀ ፣ እግዚአብሔር በራሱ መንገድ የሚሠራ አምላክ ነው ። ሲሆንና ሲፈጸም ለመቀበል አቅም የሚጠይቅ ደስታ አለ ። ደስታንም ለመሸከም አቅም ያስፈልጋል ። በዓለም ላይ እውነትን ለመሸከም አቅም ስለሚያስፈልግ መመጠን ያስፈልጋል ። የጋኑን በገንቦ እየገለበጡ ማፍሰስ ብክነት ነው ። እንዲህ ያለ የትንሣኤ ደስታ የዘመናትን ትካዜ ጠራርጎ የሚወስድ የብርሃን ጎርፍ ነው ። እሑድ ምሽት ላይ ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው እንዳልተሰረቀ አረጋግጠዋል ። በሥፍራው ማለት በመቃብሩ እናገኘዋለን ብለው ጠብቀው ስላጡት በስፍራቸው ሁነው ጠበቁት ። በስፍራው የተሰወረብንን ነገር በስፍራችን ሁነን መጠበቅ ግድ ነው ። መፈላለግ ያጠፋፋልና ።
የክርስቶስን መነሣት በግማሽ ልብ ቢቀበሉም ጠላቶቹ እስካላለቁ ደስታችን ሙሉ አይሆንም ብለው ያሰቡ ይመስላል ። በዚህም የነቢዩን ጸሎት ዘነጉ፡- “በጠላቶቼ ፊት ለፊት ራሴን በዘይት ቀባህ ” ይላል ። ጠላቶቼ እያዩ ፣ አለ እንጂ ጠላቶቼ ሬሳ ላይ ራሴን በዘይት ቀባህ አይልም ። የምንለምነው የጠላቶችን ሬሳ እንጂ የእግዚአብሔርን ዘይት አይደለም ። ሙት ግን ይዞ ይሞታልና ቅባቱ ይሻለናል ። የጠላት ድርብ ሞቱ የእኛን መቀባት ማየቱ ነው ። ጠላት ቅባታችንን ሊያጥብ ፣ ጸጋችንን ሊያራቁት ይነሣል ። እግዚአብሔር ግን በክብር ላይ ክብር ይጨምራል ። ሞት አንድ ጊዜ ነው ። ጠላት ደጋግሞ የሚሞተው ግን ቀበርሁት ያለው አደባባዩን ሲሞላው ነው ። ክርስቶስ ሲሰቀል ደቀ መዛሙርቱ በሕሊና ሙተው ነበር ። ክርስቶስ ሲነሣ ጠላቶቹ በሕሊና ሞቱ ።
አቤቱ ቅዱስ ዘይትህ አይለፈን ።
ይቀጥላል
የመስቀሉ ገጽ/ሐ
ግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቀን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ