የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በተዘጋው የሚመጣ

“ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ።” ዮሐ. 20፡26  ።
በጫካ ውስጥ በምሽት የሚገኝ መንገድ የጠፋው ነው ። በጫካ ውስጥ የሚደበቅ ወንበዴ የሚያሳድደው ነው ። በጫካ ውስጥ የጨለመበት ቀኑን ያባከነ ነው ። በጫካ ውስጥ ጨለማ ድርብ ነው ። ሌሊቱም መንታ ነው ። ግርማ ሌሊቱ ፣ ፀብአ አራዊቱ የሚያስፈራ ነው ። አዳም ስለ መሄጃው መንገድ እንጂ ስለ መመለሻው አላሰበም ። በገነት መጥፋት በጣም የሚደንቅ ነው ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁነው ለጠፉት ምሳሌ ነው ። በምድር የጠፋ ይታዘንለታል ፣ በገነት የጠፋ ምን እንደሚባል ቃላት የሚያውስ ሰው ያስፈልጋል ። አዳም መንገድ እንደ ሳተ ወዴት ነህ ? የሚለው አምላካዊ ድምፅ አመልካች ነው ። አዳም የጠፋው መንገድ የዱሩ ሳይሆን የሕይወት መንገድ ነው ። የዱሩም የሕይወትም መንገድ ሲጠፋ ሁለቱም ጊዜ ያባክናሉ ፣ መንፈስን ያስጨንቃሉ ። መንገድ የሚጠፋው በሚያውቀው ነገር ውስጥ የማያውቀው ነገር እንዳለ ያሳያል ። አዳም አውቆ በመጥፋቱ ፍርድን ተቀበለ ፣ በማወቁ ውስጥ አለማወቅ ስለ ነበረ የመዳን ተስፋን ሰማ ።

“አዳምና ሔዋን ጠፍቷቸው መንገዱ ፣
ለሰው ልጅ መከራን ትተውለት ሄዱ፤” ተብሏል ። ይደብቃሉ የተባሉ ነገሮች ሁሉ አዳምን መሸሸግ አልቻሉም ። ከእግዚአብሔር መደበቅ አይቻልም ፣ በእግዚአብሔር መደበቅ ግን ይቻላል ። ከእግዚአብሔር መደበቅ ምክንያታዊነት ፣ በእግዚአብሔር መደበቅ ንስሐ ነው ። አዳም የተዘጋ ደጅ ባይታየውም መውጣት አልቻለምና ደጁ ተዘግቶበታል ። እውቀት ሲሰወርም የደጅ መዘጋት ነው ። አዳም ደጁን የዘጋው ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰይጣንን ፣ ሚስቱንና ምኞቱን በመስማቱ ነው ። ከዚህ በፊት ባያውቀውም የኃጢአት እውቀትን ተለማመደ ፣ ከዚህ በፊት ባያውቀውም የንስሐን መድኃኒት ግን እንቢ አለ ። ለኃጢአት ፈጣን ፣ ለንስሐ ዳተኛ ሆነ ። በተዘጋው ደጅ ኢየሱስ መጣ ። በገነት ውስጥ የሰው ሕሊና ተዘግቶ ፣ በአዳምና በሔዋን መካከልም ግድግዳ ተገንብቶ ነበር ። መንገድ የጠፋው የዓለሙ ንጉሥ የሆነው አዳም ምሽት ደርሶበት ፣ ፀብአ አጋንንት በክስ ያስጨንቁት ነበር ። ምንም ያህል ጥፋት እንሥራ ከሳሽ ሰይጣን ነው ። ወቃሽ ሕሊና ግን የመንፈስ ቅዱስ መቅረብ ምስክር ነው ። አዳም ከእግዚአብሔር ሲጣላ አጋንንት ደፈሩት ። አራዊት ጠላት ሆኑበት ። የገዛ ሕሊናውም ከዳው ። እግዚአብሔር ለመንግሥተ ሰማያት ብቻ ሳይሆን ለሕሊና ሰላምም ያስፈልጋል ። ምኞታችንን የሚያረኩ ፣ እልህአችንን የሚያደምቁ ግፎች የሕሊና ሰላምን ያሳጡናል ። አዳም ተራቁቷል ፣ ነገር ግን ተራቁቻለሁ ማለት አልፈለገም ። ሰብአዊ ውድቀት ወደ ሰብአዊ ኩራት ወሰደው ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጆች መንገዱ ጣለን እንጂ እኛ አልወደቅንም ይላሉ ። ገዥዎችም ከያዢዎቻችን ድክመት እንጂ እኛ አልወደቅንም በማለት ይናገራሉ ። ወድቆ መፎከር በንስሐ ፣ ወድቆ መሸለል በአምላክ ምሕረት ይቻላል ። ነቢዩ፡- ጠላቴ ሆይ ፥ ብወድቅ እነሣለሁና ፥ በጨለማም ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሃን ይሆንልኛልና በእኔ ላይ ደስ አይበልሽ ብሏል ። /ሚክ. 7 ፡ 8 ።/
አዳምን ለምን ወደቅህ ? አላለውም ። እንዴት ወደቅህም አልተባለም ። አዳም ግን በማን ምክንያት እንደ ወደቀ ለመናገር ቸኮለ ። ለምሕረት ተጠርቶ ሌላውን ከሰሰ ። የእግዚአብሔር ምሕረት የእርሱንም የሌላውንም በደል መሸፈን ይችላል ። የራሱ የጸጸት ድምፅ የሸሸገው አዳም አሁን ወዴት ነህ? በሚለው የእግዚአብሔር የፍለጋ ድምፅ ብቅ አለ ። ወዴት ነህ ? ሲባል እዚህ ነኝ ማለትም አልቻለም ። የወደቀ ሰው እዚህ ነኝ ለማለትም እውቀት ያስፈልገዋል ። በደሉን አልተናዘዘም ፣ በደሉ ያመጣበትን ዕራቁትነት ግን ተናገረ ። ቀድሞ ደስ የሚለው የእግዚአብሔር ድምፅ አሁን ፍርሃት ሆነበት ። የእግዚአብሔርን ቃል መሸሽ ስንጀምር በጣም ወድቀናል ማለት ነው ። ሰው የሚወደው ምግብ እያስጠላው ሲመጣ ታሟል ማለት ነው ። አዳም ለበደሉ ምክንያት እስኪያገኝለት ተጨነቀ ። እግዚአብሔር ያን በደለኛውን ይጠይቃል እንጂ ምክንያቱ እንደማይጠየቅለት አላወቀም ።
እግዚአብሔር ሰውን በመውቀስ አልጀመረም ። ውስጡ የሚናገረውን መናገር ተገቢ አይደለም ። አስፈቅዶ ማዳን ግን መለኮታዊ ግብር ነው ። ወዴት ነህ ? በማለት ያለበትን ሁኔታ እንዲያይ አደረገው ። ያለበትን ሁኔታ አይቶ አውጣኝ ካለ እንደ ጴጥሮስ ሰጥሞ ሳያልቅ እጁን ይዘረጋለታል ። ሰው በመለኮታዊ ርኅራኄ ካልተወቀሰ ወድቆ ሊቀር ይችላል ። የሕክምና ስህተት የሚባለው በሽታው ሳይሆን በሽታውን ለማዳን በተደረገ ሥራ የተፈጠረ አደጋ ነው ። አጽናናለሁ እያሉ ማቍሰል ፣ አተርፋለሁ እያሉ የበለጠ በእሳት ውስጥ መማገድ ሊኖር ይችላልና ጥንቃቄ ያስፈልጋል ። የአንዳንድ ሰዎች አቀራረብና አሰባበክ የበለጠ ሊያስክድ ይችላል ። የንስሐ ድምፆች በሰው ኃጢአተኝነት ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ማተኮር አለባቸው ። የንስሐንና የማማከርን ሥራ የሚሠሩ አባቶችም እንደ መርማሪ ፖሊስ ሊሆኑ በርግጥ አይገባቸውም ። ሰውዬው እስከዚህ ድረስ ነው የሚሸከመኝ ብሎ ያመነውን ያህል ቢያማክራቸው የተሻለ ነው ።
ወዴት ነህ ? የሚለው ድምፅ የሕይወት ደጃፍ ለተዘጋበት ለአዳም የተነገረ ነው ። በኋለኛው ዘመን ወዴት ነህ ? ብዬ እፈልግሃለሁ ፣ ዛሬ በቃል በኋለኛው ዘመን ግን ሥጋ ለብሼ አድንሃለሁ ማለቱ ነው ። ፍለጋው በገነት ጫካዎች ጀመረ ፣ በቀራንዮ ፈጸመ ። ልብ አድርጉ እንጨት በልቶ የጠፋውን አዳምን ጌታችን እንጨት ተሸክሞ አዳነው ። ጸጋን ተራቁቶ ነበርና አምላካችን ዕርቃኑን ተሰቅሎ ክብር አለበሰው ። የዓለሙ ደጃፍ ሁሉ ተዘግቶ ፣ የገነት በርም ተቆልፎ ሳለ ኢየሱስ ክርስቶስ መጣ ።
ዓለም ሁሉ ግራ ተጋብቶ ነበር ። የነቢያት ትንቢት ፣ የሱባዔ ቆጠራ ፣ የጠቢባን የጥበብ ፍለጋ ሕዝብና አሕዛብ መሢሑን እንደ ጠበቁ ያሳያል ። በቤተ ልሔም የተገኙት መላውን ዓለም የወከሉ ናቸው  ። እረኞችና ነገሥታት ተገኝተዋል ። ሕዝብና አሕዛብም ሰግደዋል ። ደጆች ተዘግተው ሳለ ክርስቶስ መጣ   ። በዝግ ማኅጸን ተፀነሰ ። በዝግ ማኅጸንም ተወለደ ።
ዘመናችንን ልዩ የሚያደርገው ሁሉም እንደ ተቆለፈበት ግራ ሲጋባ ስናይ ነው ። በገዛ ቤቱም የተቆለፈበት በእስር ቤትም የተቆለፈበት ሁለቱም ስሜታቸው አንድ ዓይነት ነው ። ቤት ከእስር ቤት የማይሻልበት የስሜት እስራት ያለበት እየሆነ ነው ። የአዋቂዎች እውቀት አለማወቅ ለመሆን እየቸኮለ ነው ። አንዱን ቀዳዳ የሚደፍነው ሥልጣኔ ዘጠና ዘጠኝ ቀዳዳ የሚከፍት ነው ። ከአድማስ አድማስ በደቂቃ መገናኘትና ማውራት ይቻላል ፣ እንደዚህ ዘመን የሰው ልብ አልተራራቀም ። ሰዎች በሚመለከታቸው ርእስ ጠበኛ ናቸው ፣ የማውራት ትዕግሥት የላቸውም ። በማይመለከታቸው ርእስ ግን ቀኑን ሙሉ ያወራሉ ። ብዙ ደጆች ተዘግተው ሊሆን ይችላል ። የዓለሙ ፣ የአገሩ ፣ የቤቱ ፣ የሥራው ፣ የአገልግሎቱ ፣ … ደጆች ቢዘጉም ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታችን ይመጣል ። በስሜታችን ሳይፈርድ የሚረዳን ጌታ ይመጣል ። በንስሐ በእምነት ሁነን እንጠብቀው ። የተበዳደልን ይቅርታ እንጠያየቅ ፤ ዘመኑ እንኳን ክፉ ሠርቶ ፣ ደግ ሠርቶም የሚያስጨንቅ ነው ።
ይቀጥላል
የመስቀሉ ገጽ 9/ሀ
ግንቦት 14 ቀን 2012 ዓ. ም.
ዲያቆን መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ