“ከራስ እስከ ጢም እንደሚፈስስ፥ እስከ አሮን ጢም፥ በልብሱ መደረቢያ እንደሚወርድ ሽቱ ነው።”
መዝ. 132 ፡ 2 ።
ነቢዩ ዳዊት በእግዚአብሔር መንፈስ ሆኖ ከዛሬ ሦስት ሺህ ዓመት በፊት የሰጠው ምክር አጭርና ሦስት ቍጥሮች ያሉት መዝሙር ነው ። ይህን የኅብረት ምክር ለመኖር ግን እስካሁን አልተቻለም ። የጥንት ግሪካውያን “አንድነት ኃይል ነው” ይሉ ነበር ። ደካማ አገርና ትውልድ የሚወለደው አንድነትን በማጣት ነው ። በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ዘመን የእስራኤል መንግሥት ለሁለት ተከፈለ ። ሰሜኑ በአሦራውያን ጠፋ ፣ ደቡቡ በባቢሎናውያን ተደመሰሰ ። መለያየት ጥፋትን ይጠራል ። አንድ ሳሉ የተለያዩ አገራት እስካሁን ሰላም አላገኙም ። ኢትዮጵያና ኤርትራ ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ፣ ሕንድና ፓኪስታን ፣ ሰሜን ኮሪያና ደቡብ ኮሪያ ተጠቃሽ ናቸው ። በመለያየት ውስጥ ማነስ ፣ ደካማነት ፣ ሁከት ጸንቶ ይኖራል ። ኅብረት አስፈላጊ ነው ያለን እግዚአብሔር ነው ። ምክንያቱም የፈጠረን ለኅብረት ስለሆነ ነው ። ትእዛዛቱም ከሰው ጋር ስላለን ግንኙነት የሚናገሩ ናቸው ። የመጨረሻው ቀን ጥያቄም ሰው ለሰው ስላሳየው ፍቅር የሚሸልም ነው ። (ማቴ. 25 ፡ 35) ። መለኮት በባሕርይው አይራብም ፣ በረሀብተኞች ውስጥ ሆኖ ግን ተርቧል ። ሰው የሆነ ለሰው ይገደዋል ፣ ያዝናል ።
ነቢዩ በመንፈሰ እግዚአብሔር ሁኖ የኅብረትን ውበት አሁንም እየገለጠ ነው ። የአሮን ጢም ኅብረትን ገላጭ ነበር ። ካህናት ጢማቸውን ያሳድጋሉ ። “ጢም የሌለው መምህር ፣ አጸድ የሌለው ደብር” ይባላል ። አይከብድም ማለት ነው ። ካህናት ጢማቸውን ያሳድጋሉ ። ይህ እርጅናን አባትነትን የሚያመለክት ነው ። ኅብረት በአሮን ጢም ከተመሰለ አንድ ስንሆን ለትውልድ አባት መሆን እንችላለን ማለት ነው ። ጢም ወንድነትን የሚገልጥ ነው ። የካህናት ጢምም ራስነትን ፣ መሪነትንና ሥልጣንን የሚገልጥ ነው ። ኅብረት ሲኖረን ሥልጣን አለን ማለት ነው ። ጸሎታችንም ሥልጣን ያለው ጸሎት ይሆናል ። “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።” (ማቴ. 18 ፡ 20) ።
ጢም ሊቆጠር አይችልም ። ብዙ ነው ። ካህናትም አበ ብዙኃን የብዙዎች አባት ናቸው ። ወይም የብዙኃን አባትነት ሊሰማቸው ይገባል ። ኅብረት ሲኖረንም ለድሆች አባት ፣ ለምስኪኖች መጠጊያ እንሆናለን ። ብዙ የእርዳታ ተቋማት የተመሠረቱትና የሚቀጥሉት በተባበሩ እጆች ነው ። “ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክም ፣ ለሃምሳ ሰው ጌጡ ነው” ይባላል ። ስንከፋፈለው ትልቁ ችግር ትንሽ ይሆናል ማለት ነው ። አንድ ሎሚ ወደ ላይ እየወረወሩ ይጫወቱበታል ፣ እያሸተቱ መዓዛዋን ይደሰቱበታል ። እየመጠጡ ይመገቡታል ። በኅብረት የየራሳችንን ድርሻ ስንወጣ የምንወስደው ግዳጅ መዝናኛ ፣ ደስታና ጥጋብ ይሆናል ፣ መልካም ራእይም ከሚመርዝ ክፉ አሳብ የሚያድነን ነው ። “የአንድ አሳቢ ፣ የአንድ በሬ ሳቢ” እንዲሉ አገርም ቤትም በአንድ ሰው አሳብ አይቆምም ። አንዱ ላይ ስንጥለው በሌላው ሞት ለመኖር አቅደናል ማለት ነው ።
በአንገት ተጠልቆ ከትከሻ እስከ ጉልበት በሚደርሰው የካህኑ ኤፉድ ላይ በደረቱ ሁለት አቅጣጫ የዐሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ስም አለበት ። በዚህ ኤፉድ ላይ ሽቱውን ሲረጭ መዓዛ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ይሁን ማለት ነው ። ካህን የእግዚአብሔር ወኪል ነውና ንጽሕና በጎ መዓዛ ያለው ሊሆን ይገባዋል ። እጆቹ ደም ሳይሆን ዕጣን ይሸትታሉ ፣ በልብሱም መደረቢያ ሽቱ ያውዳል ። የእግዚአብሔር አገልጋይ ሥጋውም ነፍሱም ንጹሕና ምዑዝ ሊሆኑ ይገባቸዋል ። ኅብረት በካህኑ ልብስ ላይ እንደ ተረጨው ሽቱ ጣፋጭ ነው ። ካህኑ ሲባርክ ምእመናን ሽቱው ያውዳቸዋል፣ ደስ ያሰኛቸዋል ። ኅብረትም ሽቱ ነውና የራቁትን ያቀርባል ። ፍቅር ያጣው ዓለም ወደ እኛ የሚመጣው ፍቅራችንን ሲያይ ነው ። ለመባላትማ ዓለሙ መች አነሰው ! ኅብረታችን ምስክርነታችንም ነው ።
ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! እባክህ አንድ አድርገን!
ይቀጥላል ዕለተ ብርሃን 14
#ዲያቆን #አሸናፊ #መኰንን
መስከረም 25 ቀን 2016 ዓ.ም.