የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በኅብረት ተቀመጡ (4)

“በጽዮን ተራሮች እንደሚወርድ እንደ አርሞንዔም ጠል ነው በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና።” መዝ. 132 ፡ 3 ።

ኅብረት ማለት ያበረ ፣ የተባበረ ፣ አንድ የሆነ ፣ በቃል ኪዳን የተሳሰረ ፣ ዓላማን ለመነሻ መልካም ፍጻሜን ለመድረሻ አድርጎ ለፍቅር የዘመተ ማለት ነው ። የሚተባበር ሁሉ የተለያየ ቀለምና መልክ ያለው ነው ። አንድ ዓይነት ሊተባበር አይችልም ። የሚተባበር የተለያየ ቅርጽና ይዘት ያለው ነው ። የተለያየ ነገር ሲያብር ውበት አለው ። አበባ ውብ ነው ግን አንድ ዓይነት መልክ ያለው አይደለም ። በአንዱ ግንድ ላይ እንኳ ቢያንስ አረንጓዴና ሌላ ቀለም አለ ። ውበት የትብብር ውጤት ነው ። ነቢዩ፡- “በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?” ይላል ። (ኤር. 13 ፡ 23 ።) ነብር በአንድ ቆዳ ላይ ብዙ ዓይነት ቀለም አለው ። ኢትዮጵያዊ የሚባለውም የተለያየ መልክና ቋንቋ ያለው ነው ። ይህ መልክ ከዛሬ 2600 ዓመታት በፊት እንደ ነበረ ነቢዩ ጠቁሞናል ። ለእውነቱ ስናየው በቅርብ ቀን የመጣ ቋንቋና ጎሣ የለም ። ለምን እንግዳ እንደሆንን ፣ የዓይናችንን በጆሮአችን እንዳመንን ግራ ያጋባል ። የተንኮለኞች ማሽን ሆነን ሲያስሩንና ሲበትኑን መኖራችን ይደንቃል ።

ኅብረት የሥላሴ መገለጫ ነው ። እግዚአብሔር በሦስት አካላት ፣ በአንድ ሥልጣን የሚኖር ነው ። ሦስት ስሞች አንድ አምላክነት አለው ። ሦስት ግብራት አንድ ህልውና ይነገርለታል ። ሦስት ኩነታት አንድ መለኮታዊ አሠራር አለው ። አካላችን የተለያየ መሆኑ በአንድ ቤተ ክርስቲያን መጠራታችንን አይገድበውም ። ስሞቻችን መለያየታቸው በአንድ ሰንደቅ ለማደር እንቅፋት አይሆኑም ። አባት ልጅ ብንባልም ሁላችንም አንድ ሰውነት ያዋሕደናል ። አንዳችን በአንዳችን ውስጥ በአሳብ ፣ በቃል ፣ በእንቅስቃሴ አለን ። ድርሻችን ቢለያይም የመገፋፋት ሳይሆን የመፈላለግ ምክንያት ነው ። እግዚአብሔር ኅብረትን የፈለገው የእርሱ መገለጫ ስለሆነም ነው ። በእግዚአብሔር መልክ መፈጠር ማለት በኅብረት መኖር ማለት ነው ። አንድ ዓይነትነት የምንፈልግ ከሆነ ከገዛ አካላችን ጋርም መኖር አንችልም። ፀጉራችን ከቆዳችን ፣ አጥንታችን ከጅማታችን ልዩ ነው ። በአንድ አካል ግን ተባብሮ ይኖራል ። የመልካችን መብዛት በረከት እንጂ ርግማን አይደለም ።

የአርሞንየም ጠል ለኅብረት ትልቅ ምሳሌ ሁኗል ። አርሞንየም አናቱ በበረዶ የተሸፈነ ነው ። በረዶውም ሲቀልጥ ከተራራው ሥር ምንጭ ይገኛል ። በአርሞንየም ተራራ ሥር ያሉ መንደሮች ሁልጊዜ ለምለም ፣ በበጋም ቀዝቃዛ ውኃ የሚያገኙ ናቸው ። በኅብረት የሚኖሩም ልምላሜ ደስታ ይኖራቸዋል ። ቤተሰባዊና ማኅበራዊ ኑሮ ያላቸው በጭንቀት አይጠቁም ። አንዱ ለአንዱ የጭንቀት መድኃኒት ነው ።

እግዚአብሔር ላዘዘው ነገር ሽልማት አለው ። ምንም እንኳ ጥቅሙ ለራሳችን ቢሆንም እርሱ ግን ቸር ነውና ይሸልመናል ። በኅብረት ውስጥ ያለው ሽልማት እንዲህ ተገልጧል ። “በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዝዞአልና።” እግዚአብሔር በረከትንና ሕይወትን ጠራቸው ። እንዲህም አላቸው፡- ስሙ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ኅብረት ባለበት ኑሩ።

በረከት ባለን ነገር መደሰት ነው ። በረከት የሚኖረን ነገር ሳይሆን ባለን ነገር መስፋት ነው ። ሕይወትም መቆምና መጽናት ነው ። ግለኝነትን ስንመርጥ መርገምና ሞት ያጠቃናል ። እግዚአብሔር ባዘዘን ነገር ውስጥ ምንም የሚያጸጽት ነገር የለም ። በኅብረት ውስጥ በረከትና ሕይወት ለዘላለም ይኖራሉ ።

ተፈጸመ
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ