የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን

ኤፌ. 1፡1

አማኒ በክርስቶስ የፍቅር ባሕር ውስጥ ጠልቆ የሚኖር ነው ። ዓሣ ከውኃ ከተለየ ሕይወት እንደሌለው ክርስቲያንም ከክርስቶስ ተለይቶ መኖር አይችልም ። አማኝ በክርስቶስ ግንድነት ላይ የበቀለ ቅርንጫፍ ነው ። ቅርንጫፍ ከግንዱ ከተለየበት ቅጽበት ጀምሮ ይጠወልጋል ። አማኝም ከክርስቶስ ከተለየበት ሰዓት ጀምሮ ይሞታል ። ክንድ በአካል ላይ ይኖራል ። ከአካል ከተለየ ወዲያው መበላሸት ይጀምራል ። አማኝም አካል በሆነው በክርስቶስ ላይ በእምነት የተገጠመ ብልት/የአካል ክፍል/ ነው ። ከክርስቶስ ከተለየ ሕይወት ወዲያው ይለየዋል ።

እነዚህ ኤፌሶናውያን አካላዊ አድራሻቸው ኤፌሶን ሲሆን መንፈሳዊ አድራሻቸው ግን ክርስቶስ ነው ። በኤፌሶንም በክርስቶስም ላሉት ይላል ። በኤፌሶን ያሉ በክርስቶስ የሌሉ አሉ ። በክርስቶስ ያሉ በኤፌሶን የሌሉ አሉ ። በኤፌሶን ያሉ በክርስቶስ የሌሉ የእምነት ልብ ፣ የምስጋና ቃል የሌላቸው ሲሆኑ በክርስቶስ ያሉ በኤፌሶን የሌሉ ለአገራቸው ለወገናቸው ግድ የሌላቸው ቸልተኛ አማኞች ናቸው ። ኤፌሶናውያን እንደ ዜግነታቸው ምድራዊ አድራሻ አላቸው ። እንደ አማኝነታቸው ደግሞ አድራሻቸው ክርስቶስ ነው ። ስለዚህ በኤፌሶንም በክርስቶስም ላሉት ተባለ ።

በኤፌሶን ናቸውና መንግሥታቸውን ማክበር ፣ ግብር መክፈል ፣ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በሰላም መኖር ፣ የሌሎችን ደስታና ኀዘን መካፈል አለባቸው ። በክርስቶስ ናቸውና ለእግዚአብሔር መንግሥት አሥራት በኵራቱን ማውጣት ፣ ክርስቶሳውያንን መውደድ ፣ የአማኞችን መከራ እንደ ራስ መከራ ማየት ይገባቸዋል ። ይልቁንም አማንያን አንድ አካል ናቸውና ደስታቸውም ኀዘናቸውም የጋራ ነው ።

ለሚኖሩበት ኤፌሶን ብርሃንና ጨው መሆን ይገባቸዋል ። የመልካምነት ምሳሌ ፣ ለተጨነቁት አጽናኝ ፣ ለወደቁት የትንሣኤ ምክንያት መሆን ያስፈልጋቸዋል ። በክርስቶስ ያመነ ለሚኖርበት አገር አስተዋጽኦ አለው ። ሰማይን የሰጠው እግዚአብሔር የምድር አገሩንም ሰጥቶታል ፤ የሰማይ አገሩንም የተቀበለው በምድራዊት አገሩ ላይ ሁኖ ነው ። ምድራዊት አገሩ በክርስቶስ ምክንያት ብታሳድደው እንኳ እርሱ ግን ለአገሩ ብርሃንና ጨው መሆን አለበት ። ከዚህ ዓለም እንዳይጠብቅ ዓለሙ ጨለማና ምንም ጣዕም የሌለው አልጫ ነው ተባለ ። ስለዚህም ክርስቶስ ምእመንን ብርሃንና ጨው አድርጎ ሾሞታል ። ብርሃን ጨለማን ፣ ጨው አልጫን ይለውጣል ፤ ብርሃንና ጨው ተጽእኖና ለውጥ አምጪ ናቸው ። ትንሽ ብርሃን ጨለማን ታሸንፋለች ፣ ትንሹ ጨውም ያጣፍጣል ። ቤት ብንሠራ ፣ ወርቅ ብንደረድር ያለ ብርሃን ዋጋ የለውም ። ሥጋውን ቅቤውን ብንጨምር ጨው ከሌለው ጣዕም የለውም ። ፍትሕ ያለበት ዓለም ፣ ተስፋ ያለው ኑሮ እንዲመጣ ክርስቲያኖች ተሹመዋል ። በአገር ላይ የምናያቸው ብዙ ችግሮች ክርስቲያኖች ግዴታቸውን ባለመወጣታቸው የመጡ ናቸው ። በኤፌሶን ላሉ ፣ በክርስቶስ ላሉ የሚለው “የቄሣርን ለቄሣር ፣ የእገዚአብሔርን ለእግዚአብሔር” የሚለውን ያስተውሰናል ። የቄሣርን ለቄሣር ለመስጠት መማር ፣ መሥራትና ማትረፍ ይገባል ። የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር የምንሰጠውም በሮጥነው ምድራዊ ሩጫ ነው ። ቄሣር የምድሩ ገዥ ነውና ሃይማኖትን ካዱ እስካላለ ድረስ መታዘዝ ፣ እግዚአብሔርም የነፍስና የሥጋ ገዥ ነውና ያለ ገደብ ልንገዛለት ይገባናል ።

ኤፌሶን ሥጋዊ ፈንጠዝያ የሞላባት ፣ ዓለም አቀፍ ጣዖት የሚመለክባት ፣ ዝሙት ተራ ወግ የሆነባት ፣ ሰዎች በግፍ የሚወዳዱሩባት ከተማ ናት ። በኤፌሶን ግን ቅዱሳን ነበሩ ። በዓመፀኛው ዓለም መካከል ኖኅ ፣ በከነዓን ጣዖታውያን መካከል አብርሃም ፣ በሰዶም ሎጥ በቅድስና ነበሩ ። የቤተ ክህነቶቹ ሐናና ቀያፋ ክርስቶስ ላይ መስቀል ሲጭኑ ፣ የቀሬናው ስምዖን ደግሞ መስቀሉን ያግዘው ነበር ። ሔዋን በገነት ስትበድል ፣ ሙሴ በግብጽ ለእግዚአብሔር ይገዛ ነበር ። ቅዱሳን ሲል ክርስቲያኖች እያለ ነው ። ክርስቲያን ማለት ክርስቶሳውያን ማለት ነው ። ቅዱሳን ማለትም ለክርስቶስ የተለዩ ፣ በመሥዋዕትነት ፍቅር ሊከተሉት የጨከኑ ማለት ነው ። በቸርነቱ ክርስቲያን እንደ ተባልን ፣ በቸርነቱ ቅዱሳን እንባላለን ። ቅዱሳን የሚለው መጠሪያ በቅድስና ኑሮ መደገም አለበት ። በሰማይ ያሉት ቅዱሳን መላእክትና አባቶች ተጋድሎአቸውን ፈጽመው በክብር ያሉ ናቸው ። የእኛ ቅዱሳን መባላችን ግን በቅድስና ኑሮ ተደግፎ በሰማይ ማኅተም የሚያገኝ ነው ።

የኤፌሶን ትርጓሜ /3

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ