የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በእንተ ስማ ለማርያም

አገሬ ስማ ፣ ወገኔ አድምጥ ፣ ሕዝቤ ተለመን ። ቍራሽ ሳይሆን ልብህን ስጥ ፣ ጭላጭ ሳይሆን ፈቃድህን ገብር ። በልብህ ደጃፍ ላይ ቆሜ እለምናለሁ ። ከገረገራህ ላይ ተጠግቼ እማጸናለሁ ። በእንተ ስማ ለማርያም ፣ የእግዚአብሔር ተማሪ ነኝ ። በነፍስህ ላገለግልህ በጸሎት ፣ በቃለ እግዚአብሔር የምተጋ ነኝ ። ያካለልሁት አገርህ ፣ የበላሁበት ቤትህ ዛሬ ተዘግቷል ። ማነው ሳትል ትሰጥ የነበርህ አንተ ደግ ኢትዮጵያዊ ማነኝ ማነው የሚል ጥያቄ ውስጥ ገብተሃል ። ተማሪን ታሳድር የነበርህ የተማሪን ጎጆ አፍርሰሃል ። ትሰንቅ የነበርከው ለራስህ ርቦሃል ። በጨረቃ ትጓዝ የነበርከው በቀን መውጣት አቅቶሃል ። ማኅተም ያለው ባለማኅተምን አይነካም ትል የነበርህ ዛሬ ግን ተጠፋፍተሃል ። ገላጋይ አጥተህ ጠብህ አድክሞሃል ። በእንተ ስማ ለማርያም ዛሬ ቍራሽ ሳይሆን ልብህን እለምናለሁ ። አገሬ ታረቅ እማጸንሃለሁ ።

ፀሐይ ወጥቶልህ መልሶ ይጨልምብሃል ። ጨበጥኩ ስትል ይከዳሃል ። መልካም ሁሉ ስታሳድደው እንደ ጥላ አልያዝ ይልሃል ። የምትጠላው ክፉ ተጣብቆህ ይኖራል ። የምትለው አታጣ ፣ የሚሉህ አያጡም ። በነገረ እገዚአብሔር ሳይሆን በነገረ ሰብእ ተጠምደህ ትውላለህ ። እገሌ ከፋ እንጂ እኔ ከፋሁ መች ትላለህ ! ካምላክ የሚያገናኝህ ጸሎተኛ ፣ የሚሰብክህ የሰማይ ምንደኛ አጥተሃል ። ወገኔ ኪስህ እንጂ አንተ ተጠልተሃል ። በእንተ ስማ ለማርያም ብዬ እለምንሃለሁ ፣ ሰውን ትተህ ከእግዚአብሔር እንድትመክር እማጸናለሁ ። ወዳጆችህ መቼ እንደሚነሡብህ በጥርጣሬ ታያቸዋለህ ፣ የሞተው ውሻ ለእኔ ሲሆን ይነቃል ብለህ ትደመድማለህ ፣ ሰማይን ስፈልግ ምድራውያን ያሳስቱኛል ፣ ተናግሮ አናጋሪ ከመንገድ ያወጣኛል ትላለህ ። በእንተ ስማ ለማርያም ይህን ቀን እንድታልፍ አቤት አቤት በል ።

አንዱን ሳትዘልቀው አንዱ ይይዝሃል ። አንድ መከራ ሳይሆን የተቀላቀለ መጠጥ አስክሮሃል ። ቀን እህ ትላለህ ፣ በሕልም ስትታገል ታድራለህ ። ቸርነትህን በቸር ልብ የሚቀበል ትከጅላለህ ፣ እንቢ ሲሉህ ሞትን ትከፍላለህ ። አህያ ረገጠኝ ብለህ ፈረስ ትሆናለህ ። አፈር ልብላ ብለህ እንዳላበላህ ስትጠላ አፈር ታስገባለህ ። ደመና እያታለለህ ፣ ይዘንባል ብለህ ዘርህን አውጥተህ ትበትናለህ ። ሰማይ የከዳህ ያህል ታለቅሳለህ ። ልጅን ለስደት ትወልዳለህ ። የምትኖርበትን ከተማ ማግኘት ትናፍቃለህ ። ኑሮህም ቀብርህም ያጠራጥርሃል ። በእንተ ስማ ለማርያም ብዬ እለምንሃለሁ ፣ የገበታህን ንጉሥ እግዚአብሔርን ለምን እልሃለሁ ።

ነፍስህ ከሥጋ እንዳትለይ ትሳሳለህ ። ባልተካሰ ኑሮ መሞት ትሰጋለህ ። ሥጋህ ከነነፍስህ ብትነጠቅ ትሻለህ ። መቆያ እንጂ ዓለም መኖሪያ አለመሆኑን ትረሳለህ ። ትንሣኤ ሙታንን ዘንግተህ ለሞተው ፀጉርህን ትነጫለህ ። ተው ስማኝ አገሬ ሁሉን እንዲሠራልህ ሁሉን ለአምላክህ ተውለት ። በእንተ ስማ ለማርያም ስለ ቸሩ እግዚአብሔር ሲሉህ ሆድህ የማይጠናው ዛሬ ቍራሽ ሳይሆን የተቆረሰ ልብህን ለአምላክ ስጠው ። እንግዳውን ስታይ እንግድነትህ እየተሰማህ አልጋህን ለቀህ የምታሳድረው ፣ ባይተዋር ተደርጎ ሰው ሲጠቃ የምትታመመው ፣ እንኳን ቤተ ክርስቲያን ግንድ የተማጸነን የምትምረው አንተ የዋህ ኢትዮጵያዊ ልጅህ ሚስትህ የዋሹህ ፣ ሰማይ ምድር የከዳህ ይመስልሃል ። እግዚአብሔርን ለምነው አለሁ ይልሃል ። አባት ነኝ ለሙት ልጅ ፣ ወንድም ነኝ ለሌጣ ፣ ባል ነኝ ለቤቴ የምትል ፤ አባት ያጣህ አባት ፣ ወንድም ጋሻ ያጣህ ወንድም መስሎ ራስህ ቢሰማህ እግዚአብሔር እኔ አባትህ እሆንሃለሁ ይልሃል ። በእንተ ስማ ለማርያም ወገኔ ቃሉን ስማ እልሃለሁ ። አንተ እንጀራ ሰጠኸኝ ፣ እኔ ወንጌሉን እሰጥሃለሁ ። ያንተ ተቀብያለሁ ባለ ዕዳ እንዳልሆን የእኔን ተቀበለኝ ብዬ እማጸናለሁ ።

የተጠመቀ ከክርስቶስ ጋር ሞቷል ። የቆረበ ሲመሰክር ይኖራል ። ቤተ እግዚአብሔር የሚሄድ ወንድሙን ይቅር ይላል ። ቀኝ እጅህ ግራ እጅህን ተቀይማለችና ፣ ከመቍጠሪያህ ጋር የማይቆጠር አሳብ ጸሎትህን ያውካልና ፣ ሺህ ዓመት ላትኖር ጭንቀት ይቀጠቅጥሃልና ፣ ተርጉመህ በማዳመጥ ወተቱን አጥቁረሃልና ፣ አይሆንልኝም ብለህ ሁሉን አጨልመህ አይተሃልና ፣ ኪዳንህን አፍርሰህ ኪዳን ትሻለህና ፣ የተዘጋጀውን ትተህ አዲስ ትናፍቃለህና ፣ ያመሰገኑህን ተጠራጥረህ የረገሙህን ቃል ታምናለህና በእንተ ስማ ለማርያም ወገኔ ወደ እምነት ተመለስ ። ባሰብከው ባትኖርም ባሰበው ትኖራለህ ። ሐኪም ቢሳነው በደሙ ትድናለህ ። ቤትህ ቢያፈስስ በሰማይ ትሾማለህ ። ትዳርህ ረመጥ ቢሆን የክርስቶስ ሙሽራ ሆነህ ትሄዳለህ ። ከምድር ሞተ ተብሎ ሲለቀስልህ ፣ ከሰማይ ተወለደ ተብሎ ዝማሬ ትሰማለህ ። ዋሾ ዓለም ገድሎህ ያለቅሳል ። በእውነተኛው ዓለም አሳብህ ይሞላል ። በእንተ ስማ ለማርያም ስለ ቸሩ እግዚአብሔር ወገኔ ልብህን ለእግዚአብሔር ስጥ ! ከክርስቶስ ጋር ታረቁ ብለን የምንለምን ሽማግሌዎች ነን ። መምህር እያለህ አላዋቂ ፣ መካሪ እያለህ ነገ ጨለማ አይሁንብህ ። የተናገረውን የማያጥፍ እግዚአብሔር ካንተ ጋር ነው ። በእንተ ስማ ለማርያም ስለ ቸሩ እግዚአብሔር ተጽናና እልሃለሁ ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 2 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ