እገሌ
ቤተ ጳውሎስ፤ ሐሙስ፣ ሚያዚያ 4 2004 ዓ.ም.
የሲናን በረሀ የቃዴስ
በእሳትና መብረቅ በማረስ
እልፍ ነፍሳትን በቁጣ አቅልጦ
ምርጡን ለራሱ አብልጦ መርጦ
በእንቅጥቅጥ ፍርሀት
በህግ ስርዓት
ልብን እያራደ
ብርቱን እየናደ
የጊዜው ፍትሀት
በአንድ ማንነቱ በውል ባልታወቀ
(እ)ገሌ በተባለ
ያ አስፈሪው ሥርዓት በድንገት አለፈ፡፡
ለኃጢአተኞች እረፍት
መጽናናትና ህይወት
አንዴ ተሰውቶ የዘለዓለም ፈውስ
መንፃትና ስርየት ፍጹሙን መቀደስ
በእምነት ህይወትን ዘወትር እያደለ
በምሴተ-ሀሙስ በእገሌ ቤት ውስጥ የኪዳኑ መስዋዕት እንዲህ ተቋቋመ።
ትንሹን አክባሪ
ያልታወቀን ጠሪ
በምሴተ-ሀሙስ ድግሱን ደግሶ
ፍጥረትን ጋበዘ ሥጋ ደሙን ቆርሶ፡፡