“በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን ፤” ኤፌ. 1 ፡ 1 ።
ክርስቶስ ኢየሱስ እውነተኛው የወይን ግንድ ነው ። የወይን ግንድ ስስ የሚመስል በቀላሉ ግን የማይበጠስ ነው ። ክርስቶስ ኢየሱስም ትሑት ነው ፣ ነገር ግን ሞት በፊቱ የሰገደለት ነው ። የወይን ግንድ በተገረዘ ጊዜ ብዙ ያፈራል ፣ ክርስቶስ ኢየሱስም በመስቀል መከራው ብዙዎችን ገንዘብ አድርጓል ። የወይን ግንድ ማረፊያ ይፈልጋል ፣ ክርስቶስ ኢየሱስም በሰዎች አድሮ ይሠራል ። የወይን ግንድ ጥላ ይሆናል ፣ ክርስቶስ ኢየሱስም ብዙዎችን ከቃጠሎ ያሳርፋል ። የወይን ግንድ ፍሬውን ከላይ ወደ ታች ይሰጣል ፣ ክርስቶስ ኢየሱስም ሰማያዊ ጸጋውን አፍስሷል ። የወይን ግንድ ልምላሜው ይማርካል ፣ ክርስቶስ ኢየሱስም ብዙዎችን በፍቅር ይቀበላል ። የወይን ግንድ መልክ የለሽ ሲሆን ቅጠሉ ማራኪ ፍሬው ጣፋጭ ነው ፣ ክርስቶስ ኢየሱስም ስለ እኛ ደም ግባቱን አጥቶ ምእመናንን ውብ ፣ አገልጋዮቹን ጣፋጭ ፍሬ ያደረገ ነው ። የወይን ግንድ መንገድ ከሰጡት ርቆ ይሄዳል ፣ ክርስቶስ ኢየሱስም ፍቅሩ ለሁሉ ይበቃል ። የወይን ግንድ በፍሬው ይከበራል ፣ ክርስቶስ ኢየሱስም በአማኞቹ ደግነት ሲመሰገን ይኖራል ። የወይን ግንድ መልኩ አፈር ፣ ቅጠሉ አረንጓዴ ፣ ፍሬው ቀይና ነጭ ነው ። መልኩ አፈር የመሰለው ግንድ ሰው መሆኑን ፣ አረንጓዴው ቅጠል በእርሱ ደስ የተሰኙ ምእመናን ፣ ቀይና ነጭ ፍሬው መሥዋዕትነትና ቅድስና ያለበት የምእመናን ሕይወት ነው ። የወይን ግንድ ባይንከባከቡትም ለመድረቅ አይቸኩልም ፣ ክርስቶስ ኢየሱስም የጠሉትን ቶሎ አይቀየምም ። የወይን ግንድ የለም ሲባል ይኖራል ፣ ክርስቶስ ኢየሱስም ገደልነው ሲሉ ተነሥቷል ።
“እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ ፤ ገበሬውም አባቴ ነው” ይላል ። ዮሐ. 15 ፡ 1 ። ገበሬን እንንቅ ይሆናል ፣ እግዚአብሔር አብ ግን ገበሬ ተብሏል ። አናጢን መቀበል ያቅተን ይሆናል ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ ግን የመረጠው ሙያ ነው ። ውኃን ከቀለብ አንቆጥረው ይሆናል ፣ መንፈስ ቅዱስ ግን የሕይወት ውኃ ተብሏል ። አህያ እያልን እንሳደባለን ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ ግን ንጉሠ ሰላም ሁኖ የገባው በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ ነው ። ገበሬ ወይንን ቢተክለው እንጂ አይፈጥረውም ፤ መትከልም መውለድ ነው ። ተካይ ገበሬ የልጅ ልጁ ፍሬው ነው ። እግዚአብሔር አብም ወልድን ቢወልደው እንጂ አይፈጥረውም ። ገበሬ ስለ ተክሉ ይናገራል ፣ እግዚአብሔር አብም የምወደውና የምመለክበትን ልጄን ስሙት ብሏል ። ገበሬ ፍሬውን ይለቅማል ፣ እግዚአብሔር አብም የልጁ የደሙ ፍሬዎችን ይሰበስባል ። ገበሬ በፍሬው ይመሰገናል ። እግዚአብሔር አብም በምእመናን አንደበት “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ይመስገን” ይባላል ። ገበሬው አብ ፣ ግንዱ ክርስቶስ ፣ ውኃው መንፈስ ቅዱስ ፣ ቅርንጫፍ ምእመናን ፣ ፍሬው ሥነ ምግባር ነው ። ወይን የዕለተ ሠሉስ/የማክሰኞ ተፈጥሮ ነው ፣ ሰው የዕለተ ዓርብ የስድስተኛው ቀን ተፈጥሮ ነው ። ወይኑ በዕድሜ ሰውን ይበልጣል ። ሰው ግን የወይኑ ጌታ ሁኗል ። ይህ ምሥጢር ግሩም ነው ። እግዚአብሔር አብ ግን ዘመን ሳይቆጠርለት አባት የተባለው ዘመን የማይቆጠርለት ልጅ ስላለው ነው ። ዘላለማዊ አባትነት ዘላለማዊ ልጅ ይፈልጋል ። ልጅ በሌለበት አባት መባል የለምና ። አብም ያለ ወልድ የኖረበት ቅጽበት የለም ። ከአባቱ ጋር በዘመን እኩል የሆነው ልጅ ምስጋና ይገባዋል ።
ቅርንጫፍ ምእመናን ከወይኑ ግንድ ጋር መጣበቅ አለባቸው ። ቅርንጫፉ በወይኑ ላይ አለ ። ወይን ብዙ ቅርንጫፎች እንዳሉት ክርስቶስም ብዙ ልጆች አሉት ። ቅርንጫፍ በራሱ ሕይወትም ፍሬም የለውም ፣ ምእመንም ያለ ክርስቶስ ሕይወትም ቅድስናም የለውም ። ከፍሬ ሕይወት ይቀድማል ። ከሥነ መግባርም በፊት ሃይማኖት ያስፈልጋል ። እውነተኛው የወይን ግንድ እውነተኛ የወይን ቅርንጫፍ ያሰኘናል ። አቡሀ ለሐሰት የተባለውን የሰይጣንን ምክር የሰማው አዳም ሐሰተኛ የወይን ግንድ ሆነ ። የጸጋ ልጅነትን ከእግዚአብሔር የተቀበለው አዳም ስቶ ሁላችንን ሐሳውያን አደረገን ። የባሕርይ ልጅ በሆነው በክርስቶስ እውነተኛነትን ጻድቃን መባልን አተረፍን ።
በዚህ ዓለም ላይ እስረኞች አመክሮ እንዲታሰብላቸው ጨዋ ይሆናሉ ። ፈላስፎች ራሳቸውን አምላክ አድርገዋልና መቅደሳቸው እንዳይሰደብ ሥነ ምግባርን ይለማመዳሉ ። ወታደር ቅጣትን በመፍራት ዲሲፕሊን ውስጥ ይገባል ። ራስን በማስለመድም ሥጋቸውን የገሩ ሕዝቦች አሉ ። የክርስቲያን ሥነ ምግባር ግን ከዚህ ሁሉ የተለየና ከእውነተኛው የወይን ግንድ ከክርስቶስ በሚመጣ ሕይወት የሚገኝ ፍሬ ነው ። ትልቁ ጥያቄ ቅርንጫፍ በግንዱ ላይ እንዳለ እኛስ በክርስቶስ ኢየሱስ ነን ወይ? የሚለው ነው ። የኤፌሶን ምእመናን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉ ፣ በሰማያዊ ስፍራ የተቀመጡ ነበሩ ።
አንተን አብን ሳትታይ የምትወደደውን ፣ አንተን ወልድን ታይተህ የማትጠገበውን ፣ አንተን መንፈስ ቅዱስን አብና ወልድን ለማየት ዓይን የሆንከንን ለማመስገን ስለበቃን ደስ ይለናል ። ለዘላለሙ አሜን ።
የኤፌሶን ትርጓሜ /4
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 26 ቀን 2014 ዓ.ም.