ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 14 2004
ለኃጢአት ከተሰጠ ሰውነት
ሞት ሞት ከሚሸት ማንነት
አልጋ ሲሉት ከሚል ቀጋ
ሁሌ ከሚቃትት ሁሌ ከሚሰጋ
ጥላን ከሚከተል ንፋስ ከሚጎስም
ህማም ደዌ ሀሳር ከበዛበት ዓለም
ማን ነው የሚያድነኝ? ሀይሉን ክንዱን ሰብሮ
ከንቱ ከተባለ ከአለማማን ኑሮ፡፡
የሞት ዕልልታ ከነገሰበት
ሰይጣን በክፋት ከአጊያጌጠበት
ኃጢአት ድር ቤቷን ከሰራችበት
ስር መሠረቷን ካፀናችበት
ማን ያድነኛል? ከመቃተቴ
ማን ይሰማኛል? ይህን ጩኸቴ
ፅድቅ ከሚሠለች ከድካም መንፈስ
ማለዳ ቀድሶ አመሻሽ ከሚረክስ
የመርገም ዕጭ አብቅሎ
የፅድቅ ጫጩት ገድሎ
ከድንግዝግዝ ጉዞ ካልጠራ ዕይታ
ከሰካራም ጠባይ ከዚይ ክፉ ጌታ
ማነው የሚያድነኝ? ብዬ አልታወክም
ልቤን አላደክምም አቅሌን አልበትንም
አለልኝ መከታ የተዘረጋ ክንድ
ቀራንዮ ጎልጎታ ውዴ እኔን በወውደድ
ሸክሜን ተሸክሞ ርስቴን ያሰፋልኝ
ወዶ በፈቃዱ ሞቴን የሞተልኝ
ጌታ ኢየሱስ ነው በክንዱ ያዳነኝ፡፡