የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

“በዚህች ዓመት ተዋት”

እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አደረሳችሁ!
የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ፤ ዘመነ ማቴዎስ እሑድ መስከረም 1/ 2009 ..

ሰዎች ዘግናኝ አደጋዎችን እንደ አስደናቂ ዜናዎች መመልከት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ ማንም ሳይቀድማቸው ለማርዳት ይፈልጋሉ፡፡ በልባቸው ግን እነዚህ የሞቱት እግዚአብሔር ባወቀው ስህተት እንደሆነ ይሰማቸዋል፡፡ በመቀጠልም እግዚአብሔር ምን ያህል እንደሚወደኝ አወቅሁ ይላሉ፡፡ እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ፍቅር በሌሎች ጥፋት ውስጥ ለማየት ይሞክራሉ፡፡ የእግዚአብሔር የፍቅሩ መለኪያ ግን ሌሎች መቀጣታቸውና እኛ በነጻ መለቀቃችን አይደለም፡፡ የፍቅሩ መለኪያ በቀራንዮ የዋለው አንድ ልጁ ነው፡፡ እኛ ደህና ብለን ከምንጠራው ሞት ከደቀመዛሙርቱ የሞተ ያለ አይመስልም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በስቅላት፣ ቅዱስ ጳውሎስ በሰይፍ፣ ቅዱስ ቶማስ ቆዳው ተገፎ፣… ሞተዋል፡፡

የእግዚአብሔር የፍቅሩ መለኪያ የአሟሟት ሁኔታ ሳይሆን ቀራንዮ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ምን ያህል ትወደኛለህ? ብንለው ዕለት ዕለት እያበላኋችሁ አይለንም፡፡ ምን ያህል ትወደኛለህ? ስንለው የተቸነከረ እጁን እያሳየ ይህን ያህል ይለናል፡፡ ሰማዕታት ሁሉ ያመኑትን እውነት አልክድም ብለው ሞቱ፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ግን ኃጢአተኛ ተብሎ የሁላችንን ኃጢአት ተሸክሞ፣ በእኛ ፈንታ ተተክቶ ሞተ፡፡ የፍቅሩ መግለጫ ቀራንዮ ነው፡

አረመኔ መንግሥታት ሁሉ ለፈጸሙት የግፍ ግድያ የድጋፍ ፊርማና ሰልፍ ይፈልጋሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን ስለ ሰዶምና ገሞራ ቅጣቱ አድናቆት ልናቀርብለት ሰልፍ ብንወጣ እኔን የሚያስደስተኝ ቢመለሱልኝ ነበር ይለናል፡፡ ልዩነቱ መንግሥታት ሕዝብን ሲያስተዳድሩ፣ እግዚአብሔር ግን ልጆቹን ማስተዳደሩ ነው፡፡

እግዚአብሔር ራሳችንን ከኃጢአተኛ ጋር በማነጻጸር ብናመሰግነው ምስጋናችንን ይፀየፈዋል፡፡ ቃሉ እንዲህ ይላል፡– “… ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፥ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ፥ ፈሪሳዊው ቆሞ በልቡ ይህን ሲጸልይ፡እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤ በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፥ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ አለ፡፡ ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን፡አምላኬ
ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር፡፡ እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል (ሉቃ. 189-14)፡፡

ፈሪሳዊው የተናገረው ሐሰት አልነበረም፡፡ ሁልጊዜ ግን የሚያስበው ስለ ጽድቁ እንጂ ስለጉድለቱ አይደለም፡፡ በዚህ ክፍል ላይ እንኳ ጽድቁን አወራ፡፡ ጽድቅን ማውራት በራሱ ኃጢአት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሰጠውን ሳይሆን ለእግዚአብሔር ያደረገውን አጉልቶ ተመለከተ፡፡ ስለዚህ በእርሱ አስተሳሰብ እግዚአብሔርን እያሳቀቀው ነው፡፡ ሌላውን ወንድሙን ይጠየፍ ነበር፡፡ እግዚአብሔር የፈጠረውን ሰው በመናቅ፣ እግዚአብሔር ተስፋ ባልቆረጠበት ላይ ተስፋ በመቁረጥ፣ እግዚአብሔር ባልፈረደበት ላይ በመፍረድ ይበድል ነበር፡፡

ፈሪሳዊው በደሉ ጠፋው፣ እኔ ምን አለብኝ? የዐርባ ቀን ሕጻን ማለት ነኝ ብሎ አሰበ፡፡ ቀራጩ ግን ጽድቁ ጠፋው፣ እግዚአብሔርን የሚያስደስት ምን መልካም ነገር አለኝ? ብሎ አለቀሰ፡፡ ራሱን ከሸለመው ፈሪሳዊ ይልቅ ራሱን የኰነነው ፀድቆ ተመለሰ፡፡ ኃጢአተኛ ነኝ ማረኝ ብለን በራሳችን ብንፈርድ ባልተፈረደብን ነበር፡፡

እግዚአብሔር አንጻራዊ የሆነ ምስጋናን አይፈልግም፡፡ እግዚአብሔር ባይጠብቀን ኖሮ እንደ ቀራጩ መሆናችን አይቀርም ነበር፡፡ ጌታችን የሚደሰተው በሌሎች ጥፋት በመደሰታችን ሳይሆን ስለ ጠፉት በመጸለያችን ነው፡፡ሌሎቹ ሞተው እኛ ግን ያለነው ሳንበድል ቀርቶ ሳይሆን ይህችን ዓመት ልያቸው ተብለን ነው፡፡

ጌታችን በሚያስተምርበት በመዋዕለ ስብከቱ፡–

ሰዎች መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስለ ደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች አወሩለት፡፡ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፡እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለ ደረሰባቸው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን?እላችኋለሁ፥ አይደሉም፤ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ አላቸው(ሉቃ. 131-3)፡፡

እነዚህ የገሊላ ሰዎች መሥዋዕት እያቀረቡ ሳለ ጲላጦስ ያረዳቸው እግዚአብሔር መሥዋዕታቸውን ባይቀበለው ነው ብለው እንዲያስቡ አደረጋቸው፡፡ አንድ የፍልሰታ ሱባዔ የያዘ ሰው በሞቱት መሪዎች እግዚአብሔር መልስ ሰጥቶኛል ብሎ ጾሙን አቋርጦ እንደወጣ ሰምቻለሁ፡፡ እግዚአብሔር በፍርድ ከመጣ የሚተርፍ ማንነው? የተፈረደባቸው የሚመስሉ ሰዎችን አይተን ጌታ ሆይ አንተ ጻድቅ ፈራጅ ነህ ብንለው ቀጥሎ ወዳንተ እመጣለሁ ይለናል፡፡ የዓይነቱ መለያየት እንጂ ሁላችንም ገዳዮች ነን፡፡ ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን፡፡ አንዱ በጥይት ሌላው በብዕር ሌላው በአንደበቱ ይገድላል፡፡ አንዱ አካልን ሌላው ኅሊናን ይረሽናል፡፡

የገሊላ ሰዎች ላይ የደረሰው አደጋ ዜና ሳይሆን ማስጠንቀቂያ መሆኑን ጌታችን ተናግሯል፡፡ እግዚአብሔር በነቢይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ላይ በደረሰው ጥፋትም ያስተምረናል፡፡ ከሚመጣውም ጥፋት የምናመልጠው በንስሐ ነው፡፡

የወደቁ ካሉ ከቆሙት ይልቅ ኃጢአተኛ ሆነው አይደለም፣ የቆሙ ካሉም ከወደቁት ይልቅ ጻድቅ ሆነው አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ቀን ለንስሐ የተሰጠን ተጨማሪ ዕድል ነው፡፡ ዕድልነቱን ዘንግተን ስለ ወደቁት አቤት አቤት ብንል የእኛ ፍርድ ይደርስብናል፡፡

ጌታችን መርዶውን ይዘው ለመጡትና ራሳቸውን እንደ ንጹሕ ለቆጠሩት፡–

ወይስ በሰሊሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ አሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን?አይደሉም፥ እላችኋለሁ፤ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ አላቸው(ሉቃ. 134-5)፡፡

ሞት ሁሉ ቅጣት አይደለም፡፡ ሞት ጥሪም ነው፡፡ ከሞትም የሚቀር የለም፡፡ የሌሎች ሞት ለቆሙት የሚያስተላልፈው ትምህርት አለው፡፡ የሞቱት ከዚህ በኋላ መልካምነታቸውን መቀጠል፣ ጥፋታቸውንም መካስ አይችሉም፡፡ ዕድል ያላቸው የቆሙት ናቸው፡፡ ይህንን ያህል እየበደልነው ለምን አኖረን? ይህችን ዓመት ለምን ጨመረልን? ጌታችን ሌላ ምሳሌ ተናገረ፡–

ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፥ ፍሬም ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም፡፡ የወይን አትክልት ሠራተኛውንም፡እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፤ ቊረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቁላለች?አለው፡፡ እርሱ ግን መልሶ፡ጌታ ሆይ፥ ዙሪያዋን እስክኰተኲትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት፡፡ ወደ ፊትም ብታፈራ፥ ደኅና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቆርጣታለህ አለው (ሉቃ. 136-9)፡፡

ወይን የተባለችው እስራኤል ናት፡፡ ያ የወይኑ ባለቤት እግዚአብሔር ነው፡፡ ሦስት ዓመት ፍሬ ፈለገባት፡፡ በዘመነ መሳፍንት፣ በዘመነ ነገሥት፣ በዘመነ ካህናት መልካምነትን ፈለገባት፡፡ ነገር ግን ሊያገኝባት አልቻለም፡፡ በምድር ለሚኖሩ ሁሉ ክፉ ምሳሌ እየሆነች፣ በድፍረት ኃጢአትም እየተገዛች፣ ብዙ በተደረገላት ቁጥር በብዙ እየበደለች ስታስቸግር የመቆረጥ ፍርድ መጣባት፡፡ በዚህ ጊዜ የወይኑ ተንከባካቢ ክርስቶስ በመስቀል ላይ፡– አባት ሆይ፥ የሚያርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው  በማለቱ ጥቂት የንስሐ ዘመን ተሰጣት (ሉቃ. 23፥34)፡፡ እስራኤል ግን የተሰጣትን ዐርባ የንስሐ ዘመን ስላልተጠቀመች በ7ዐዓ.ም ፈጽማ ተደመሰሰች፡፡ ከ7ዐዓ.ም እስከ 1948 ዓ.ም ፈርሳ ኖረች፡፡

ስለ ገሊላ ሰዎች ጥፋት ለሚደነቁት ከፊት ለፊታቸው የመላዋ እስራኤል ጥፋት እንዳለ ነገራቸው፡፡ አሁንም በሕይወት ያሉት በሌሎች ጥፋት ለመሳቅ ሳይሆንበዚች ዓመት ደግሞ ተዋት ተብለው መሆኑን አላስተዋሉም፡ ፡በገላጋይ እየኖሩ በጽድቃቸው ወጥተው የሚገቡ መሰላቸው፡፡

“ሞት ተምሯል ይላሉ ምን ይማራል ገና ያግዛል” እንደተባለ ሞት በዙፋን ተቀምጦ እየገዛ፣ እንደመኸርም ሰዎች እየታጨዱ ው፡፡ የብዙዎችን መርዶ ሰማን፣ በወዳጆቻችንም ማለፍ ልባችን ተነካ፡፡ ነገር ግን እኛም የኖርነው፡– በዚህ ዓመት ደግሞ ተዋት ተብለን ነው፡፡ ከሌሎች መሞት ይልቅ የእኛ መኖር ይደንቃል!

ይህ ዓመት በተለወጠ ማንነት የምንመላለስበት፣ ጠብና ክርክርን፣ ዝሙትና ስካርን፣… ጥለን ከእግዚአብሔር ጋር የምንስማማበት ዓመት ሊሆን ይገባል፡፡ እግዚአብሔር ሦስት ዘመናት ተመላልሶ የፈለጋችሁ በሕጻንነት፣ በወጣትነት፣ በጎልማሳነት ዘመን የጠራችሁ አስተውሉ! ዘመን የተጨመረልን ያልጨረስነውን ኃጢአት እንድንጨርስ ሳይሆን ለንስሐ ነው፡፡ ዐውደ ዓመቱ ስለ ድግስ ሳይሆን ለምን ዕድሜ ተጨመረልኝ ብለን የምናስብበት ሊሆን ይገባል፡፡

እግዚአብሔር ዓመቱን የሰላምና የፍቅር ያድርግልን!

ያጋሩ

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።