የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገፅ
ሐሙስ፣ መስከረም 29/2007 ዓ.ም.
ሰው በዓይኑ ብቻ ሳይሆን በልቡም ይተያያል፡፡ ይህም የላቀና የጠነከረ ማስተዋል ነው፡፡ አበው “ልብ ካላየ ዓይን አያይም” እንዲሉ፡፡ ሰው ሰላምታውም በእጅ ብቻ የሚታለፍ ሳይሆን በሕሊናም የሚከወን ነው፡፡ ሕሊና ተጣጥፎ እጅ ቢዘረጋ ግንኙነቱ ከበድን ጋር ይሆናል፡፡ አፍኣዊ በሆኑ ነገሮች የምንግባባውን ያህል ውስጣዊ በሆነው ማንነታችን መገነዛዘብ አለመቻላችን እንጂ ይህኛው በእጅጉ ይልቃል፡፡
የመተያየትን ሂደት ስንመረምር አንዳችን በአንዳችን ውስጥ ያለውን ጉልህም ሆነ ህቡዕ፣ ብርቱም ሆነ ድኩም፣ ውጥንም ሆነ ፍጹም የሆነውን ነገር እንደ ንሥር ባለ ዕይታ እንገማገማለን፡፡ መልካሙን ከማስተዋልም ይልቅ ክፉውን ለመንቀስ ዝንባሌያችን ያየለ እንደ መሆኑ ለትችት በሚረዱ ምክንያቶች ላይ ጥሩ ተመልካች እንደሆንን አስባለሁ፡፡ ጠንካራ መተያየት በመካከላችን ላለው ወዳጅነት መጥበቅም ሆነ መላላት ቀዳሚው ቅኝት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ጠበቅና ጠለቅ ወዳለው መተያየት ስንዘልቅ የሚሆነው ነገር አፍአዊ ከሆነው መተያየት የበረታ ነው፡፡ ምክንያቱም ውጫዊ በሆነው መተያየት ውስጥ የቆዳ ጠባሳን ልናይ በውስጣዊው ደግሞ የልብን ጠባሳ ልናስተውል እንዲሁም በዚያ የአካል መቆሸሽን በዚህ ውስጥ ደግሞ የሰብእና ዕድፈትን ልንመለከት እንችላለን፡፡ በዚህ መንገድ ፍተሻችንን ብንቀጥል ደግሞ በሰው ዘንድ ከተሻለው የባሰው፣ ከቀናው የጠመመው ይበዛል፡፡ ለዚህም ይመስለኛል በጉርብትና ከመኖር በባልንጀርነ ት፣ በባልንጀርነት ከመኖር በወዳጅነት፣ ተወዳጅቶ ከመኖርም ተፋቅሮ (በትዳር) መኖር የበለጠ ዋጋ መክፈልን የሚጠይቀው፡፡ በርቀት ያየነው ሰው አይደለም ዕቃ እንኳን ስንቀርበው አልያም ሲቀርበን ማስተዋላችን አንድ ዓይነት አይሆንም፡፡ በሩቅ ከምትወዱትና በቅርብ ከምትጠሉት፣ እርቃችሁ መልካም እንደሆነ ከምታስቡትና ቀርባችሁ ድካሙን ካያችሁት ለየትኛው የተሻለ ስፍራ አላችሁ፡፡ መጽሐፍ ግን እንዲህ ይላል፡- “የተገለጠ ዘለፋ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል” (ምሳ. 27፡5)፡፡ በእኛስ ዘንድ የትኛው የበለጠ ዋጋ አለው;
ሰውን በሥጋ እንደ ማየት አድካሚ፣ በእኔነት ውስጥ ሆኖ እንደ መውደድ አታካች የሆነ ነገር ፈጽሞ የለም፡፡ ማር ይስሐቅ፡- “ሥጋ ያለ ልቡና ያየ እንደሆነ እንስሳን ይመስላል፡፡ ነፍስ ግን ያለ ሥጋ ምክንያት መንፈሳዊውን ራእይ ለማየት ትችላለች” ይላል፡፡
በደመ ነፍስ ከመተያየት የሚልቅ መተያየት ከሌለን ምድሪቱን ማሰብ ይዘገንናል፡፡ በየትኛውም ደረጃ ያሉ ግንኙነቶችም ጣዕም አልባ ይሆናሉ፡፡ ራሳችንን እንኳን በዚህ ሁኔታ ማየት ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ በቅጥራችሁ ውስጥ የታሰረን አንድ በግ አስቡ፡፡ በግነቱ ምን ያህል እንደሚያምር፣ የዋህነቱ ምን ያህል እንደሚስብ፣ የተሸከመውም ሥጋ ለመብላት ምን ያህል እንደሚያጓጓ በጽሞና አድንቁ፡፡ የቀለሙ ንጣት፣ የአቋሙ ስባት፣ የዓይኑ ንጣት፣ የፀጉሩ ብዛት እንዴት ይመስጣል; በጉ እንኳን ሰላማዊውን አራጁንም ያራራል (ሆድ ያባባል)፡፡ ግን እንደ ምንም ጨክናችሁ እረዱት፡፡ አሁን የምናየው በፊት ከምናስተውለው በእጅጉ የተለየና የተብራራ ነው፡፡ ፈርስና ሽንፍላ፣ ጅማትና ሐሞት አሁን በግልጥ ይታያሉ፡፡ ባልጸዳና ባልጣመ ሁኔታው መብላት አይደለም ማየት ፈታኝ ነው፡፡ ይህንን በሰው ደረጃ አስቡት፡፡ ሰዎችም እንደ ሐሞት ያለ መራራ፣ እንደ ፈርስ ያለ የማይረባ የሕይወት ክፍል አላቸው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ብዙ ሰዎች በተብራራ መልኩ ራሳቸውን በሰው ፊት ለማቅረብ አቅም የሚያጡት፡፡ ከዚህም የተነሣ ድብቅነት አንዱ የኑሮ ማጣፈጫ እየሆነ ሊመጣ ችሏል፡፡ ብዙ ወዳጅነቶች ሲፈተሹ ከተብራራ ግንኙነት ይልቅ ሾላ በድፍን ዓይነት ናቸው፡፡ አንዳንዴም ለዘላቂነት እንደ ዋስትና ያገለግላሉ፡፡
በጌታ መተያየት (መተዋወቅ) ከብዙ ጉዳት የመትረፊያ መንገድ፣ የበጐ ስጦታና የፍጹም በረከትም ምንጭ ነው፡፡ በተለይ በክርስትና ሕይወት ያለን በአንዱ እግዚአብሔር ልጅ ስም ኅብረት ለምናደርግ ይህ ተግባር የእምነት አስገዳጅነት ያለበትም ጉዳይ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በ2ቆሮ. 12$2 ላይ “ሰውን በክርስቶስ አውቃለሁ …” ይላል፡፡ በጣም የሚገርመው ቅዱስ ጳውሎስ ሰውን ብቻ ሳይሆን ራሱንም እንኳን የሚመለከተው በክርስቶስ ነበር፡፡ በሰማያዊው ስፍራ የተቀመጥነው፣ ከዘላለም ጥሪ ተካፋይ የሆነው በዚህ መንገድ ነው፡፡ እስቲ ራሳችሁን ያለ እግዚአብሔር እዩት፡፡ አቋሙ ምን ይመስላል; ከለርና ቅርፁ ምን ዓይነት ነው; በደንብ ተመልከቱት! ይታሰብስ ዘንድ የተገባ ነውን; መዝሙረኛው ነቢይ፡- “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድነው; ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድነው;” (መዝ. 8$4) ይላል፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር በልጁ በኩል በሠራው የመስቀል ውለታ ውስጥ ሆነን የማናየው ማንነታችንም ሆነ ወገናችን ከዚህ የተሻለ ምን ሊባልለት ይችላል፡፡ በተለምዶ እንደ እገሌ አይቼህ ነው እንጂ አንተማ … የምንልበት ጊዜ አለ፡፡ የአባትን ክፋት የሚያስረሳ የልጅ ብድራት፣ የልጅን ጥፋት የሚያስረሳ የእናት መልካምነት፣ የባልን መልከ ጥፉነት የሚከድን የሚስት መልከ መልካምነት አለ፡፡ ስለዚህ እንደ እርሱነቱ ስናየው የምንጠላውን በእገሌ በኩል ስናየው እንወደዋለን፡፡ በእርሱ በኩል መጥተህብኝ ነው እንጂ ላንተስ ይህ አልነበረም የሚገባህ እንላለን፡፡
መጥፎውን በደግ ውስጥ ሆነን ስናየው ወደ ደግነት እናመጣዋለን፣ ጥላቻን በፍቅር ውስጥ ሆነን ስናየው ወደ ወዳጅነት እንቀይረዋለን፣ ችግራችንንም በክርስቶስ ውስጥ ሆነን ስናየው ወደ በረከት እንለውጠዋለን፡፡ በመከራ ውስጥ ሆኖ እግዚአብሔርን ለማየት እንደ መጣር ያለ ሥቃይ ግን የለም፡፡ መከራችንን በመከራው በኩል፣ ነቀፋችንን በእርሱ ነቀፋ በኩል፣ ኃጢአታችንን በፈሰሰው ደሙ በኩል እንደ ማየት ያለ ዕረፍትም የለም፡፡ በክርስቶስ ካልተያየን ግን ማብራሪያችን የከፋ ነው፡፡ የገነት ደጅ በሰይፍ የተዘጋበት፣ በሞት ግዞት የተቆለፈበት፣ በበደልና በኃጢአት ሙት፣ ጽድቁ የመርገም ጨርቅ፤ ክብሩ ባርነት ዋናውም ሞት የሆነ ለዘላለም ኲነኔ የተቀጠረለት … ያለ ክርስቶስ ያለው ማንነት እንዲህ ዘግናኝ ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ በጌታ ተያዩ፡፡
ዛሬ ሰዎች በብዙ መንገድ ይተያያሉ፡፡ በገንዘብና በሥልጣን፣ በዘርና በእውቀት፣ በሙያና በሃይማኖት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ዓለማችንን አንድ መንደር ውስጥ ያለ ሰባት ቢሊየን የቤት ቁጥር አድርጓታል፡፡ የተቀራረብን ይመስለናል ግን ማዶ ለማዶ ነን፣ የተባበርን ይመስለናል ግን የምንተያየው ካብ ለካብ ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ራሱንም ሆነ ሰዎችን የሚያየውና የሚያውቀው በክርስቶስ ስለነበረ ካደረገው ይልቅ የሆነለትን፣ ከሠራውም ይልቅ እግዚአብሔር በልጁ በኩል የቆጠረለትን ያወራ ነበር፡፡ ራሳችንን በጌታ ስናየው “ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ” (ኢዮ. 42፣5) ማለት እንችላለን፡፡ ዓለምንም የምንንቀው በከበረውና ግዛቱ የዘላለም በሆነው ጌታ በኩል ስናያት ነው፡፡ እስቲ የባልንጀራችሁን በደል፣ የጐረቤታችሁን ተንኰል፣ የወዳጃችሁን መክዳት፣ የትዳራችሁን ጉስቁልና በጌታ በኩል ለአንድ አፍታ እንኳን ተመልከቱት፡፡ በጠላና በአረቄ፤ በጠጅና በብርዝ የተሸመገሉ ትዳሮች በዚህ ጌታ በኩል ቢሸመገሉ ኖሮ ችግሩ የዕድሜ ይፍታ ባልሆነ ነበር፡፡ ራሳችሁንም መውቀስ አቁሙና በክርስቶስ እዩት፡፡ ያ ደካማ ማንነት ቀራንዮ ላይ በደከመልን ጌታ ድል ተነሥቷል፣ የሚያስነባችሁ ኃጢአት መስቀል ላይ በፈሰሰው ደሙ ተወራርዷል፣ ውድቀታችሁም በትንሣኤው ኃይል ተዋርዷል፡፡ ስለ እናንተ የሚጠይቅ ካለ ስፍራችሁ በሰማይ ነው (አፌ. 2፣6)፡፡
ይቀጥላል…