የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በጠላት ፊት ጽኑ ግንብ

      ዓርብ ጥር 23/ /2006 ዓ/ም
                                                     የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ
 

ሰው ግዙፍ ግንብ አቁሞ፣ በበረቱ ዘቦች ዙሪያው ታጠሮ፣ በአርማታ በተዋቀሩ ሕንፃዎች መሐል እየኖረ፣ ማረሳሻና ማባበያ የሚሆኑ ብዙ ዘመናዊ ዕቃዎች እያሉት፣ መሣሪያ ታቅፎ እያደረ፣ ዓይኑን አላርም (መጥሪያ) ላይ ተክሎ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዙሪያው ቆመው እንዴት እንቅልፍ በዓይኑ ሳይዞር፣ ልቡም ከሥጋት ሳያርፍ ነጋ  ብላችሁ ታውቁ ይሆን? ለጠንቋይ በጀት በጅቶ ሟርተኛ እየቀለበ፣ ከእርሱ የተጣላ አይነጋለትም፣ የበደለውም በጤና አይቆምም የሚባልለት ሰው በእንቅፋት ሞተ መባልን ሰምታችሁ ልባችሁ ተደሞ ይሆን?
     ሰዎች ካሉባቸው ሥጋቶች መካከል አንዱ በጠላት በኩል ያለው ሥጋት ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥታት ለሕዝባቸው መሠረታዊ ፍላጐት ከሚበጅቱት በላይ ለመሣሪያ የሚወጣው ገንዘብ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ርዕሱም ራስን ከጠላት መከላከል የሚል ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት ራስን ለመመከት የጠላትንም ዕቅድ ለማክሸፍ ጥቅም ላይ ይውሉ ከነበሩት ነገሮች መካከል ግንብ አንዱ ነው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ግንብ የሚለውን በገጽ 247 ላይ ሲፈታ ጠላት ሲመጣ ሕዝቡ የሚሸሽበት በከተማ ቅጥር ላይም ጠላትን የሚከላከልበት ነው ይላል፡፡ በተጨማሪም 2ዜና.መ. 14÷ 7፣26÷9፤ ማቴ. 21÷33 እንድናነብ ይጋብዘናል፡፡ በዘመኑ ግንብን ከዚህ ለተለየ ዓላማም ተጠቅመውበት የነበረ ቢሆንም በዋናነት ግን ጠላትን ለመከላከል ይውል ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ያለው የኢየሩሳሌም ቅጥር /ግንብ/ ቅሬታ አገልግሎቱን በሚያብራራ መንገድ በእግዚአብሔር ምድር ላይ ይገኛል፡፡ በአገር ደረጃም ብቻ ሳይሆን በግል ሰዎች ራሳቸውን ከጠላት ለመከላከል እንደ ግንብ የሚያገለግሏቸውን ነገሮች በመያዝ እንደሚንቀሳቀሱ ግልጽ ነው፡፡
     ቅዱስ ዳዊት ግን በሰው ዘንድ ከሚታወቀውና ከዚህ እጅግ በላቀ ሁኔታ በሕይወቱ ያየውን የጸና ግንብ በጠላት ፊት አቁሞ ያስተዋውቀናል፡፡ ዳዊት መዝሙሮቹን የጻፈው በሕይወት ከደረሰበትና በኑሮው ከደረሰለት እግዚአብሔር በመነሣት ስለሆነ ልብን የመንካት አቅም አላቸው፡፡ ብዙ ጊዜ እኛ ያላረፍንበትን ቃል ሌሎች እንዲያርፉበት በመመኘት ብቻ ስናስተላልፈው ውጤቱ ፍጹም ከገመትነው በተቃረነ መልኩ ይሆናል፡፡ ዳዊት ስለ ዕንባ የጻፈው ካነባ ፣ ስለ ደስታ የጻፈው ከተደሰተ በኋላ ስለ እርካታ የጻፈውም ካረፈ በኋላ ነው፡፡ ስለዚህ ስሜት ሳይሆኑ መንፈስ፣ ማባበያ ሳይሆኑ መፍትሔ መሆናቸውን ልብ እንላለን፡፡ 60ኛውንም መዝሙር የጻፈው ያለፈለትን ብርቱ የሕይወት ሰልፍ በማሰብና ከእግዚአብሔር ጋር ያሳለፈውን የድል ዘመን በመቀúጠር ነው፡፡ እህል አሸክማችሁ መንገድ ስትሄዱ እህሉ የእናንተ ሸክሙ ግን ሌላ ላይ እንደሚሆን ሁሉ እግዚአብሔር እየተዋጋ ድሉን ለእኛ ይቆጥርልናል፡፡ ባሕር የከፈለው እግዚአብሔር ቢሆንም እልልታና ደስታ ግን ለእስራኤል ነበር፡፡ ዳዊትም በእምነት የተቆጠረለትን እያሰበ “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድነው? በማለት ይናገር ነበር (መዝ. 8÷5)፡፡ ዳዊት የጐረቤት ብቻ ሳይሆን የወላጅ አባትን ንቀት፣ የጓደኛን ብቻ ሳይሆን የወንድምንም ጥላቻ ያውቀ ነበር፡፡ በባዕድ መተውን፣ በቤተሰብ መገፋትን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እስቲ ትንሽ ከሕይወት ታሪኩ እንዝገን፡፡ 


ውሎው በእልፍኝ ሳይሆን በምድረ በዳ የነበረ በእረኝነት በጐች በመጠበቅ የተሰማራ፣ አባቱ በግድ ያስታወሰው፣ እግዚአብሔር በዘይቱ ያከበረው፣ ከበግ እረኝነት ሕዝብን ወደ ማስተዳደር ከፍ ያለ /ከእንግዲህ ዓሣ አታጠምድም ሰው ታጠምዳለህ እንደ ተባለ/ መራብንም መጥገብንም፣ መብዛትንም መገፋትንም፣ መናቅንም መክበርንም፣ መተውንም መታወስንም ያወቀ ገና በጉብዝናው ወራት ራሱን እግዚአብሔር እጅ ላይ የጣለ ሰው ነበር፡፡ ዘመንን ሳይከስሩ፣ ሕይወት ሳትጠወልግ፣ በምድረ በዳው ሳይዝሉ እግዚአብሔርን እንደ ማግኘት ያለ እድል የለም፡፡ ዳዊት በዕድሜው ማለዳ እግዚአብሔርን ያገኘ፣ በፈቃዱም ፊት የተንበረከከ ነቢይ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ በጭንቅ፣ የጦር ሠፈሩም በፍርሃት በቀለጠበት፣ ለዚህም ምክንያት የሆነው ጐልያድ ድንበር ላይ ይፎክር በነበረበት ዘመን ዳዊት የአባቱን የእሴይን ትእዛዝ በማክበር የወንድሞቹን ደኅንነት ለመጠየቅ በአንድ የኢፍ መስፈሪያ /መጠነኛ መስፈሪያ/ የተጠበሰ እሸት እንዲሁም ዐሥር እንጀራዎችን ይዞ በጦር ሠፈሩ ወዳሉት ወንድሞቹ ሄደ፡፡ አባቱ እሴይ ልጁን የላከበት ልጁ ዳዊት ወደ ወንድሞቹ የሄደበት ጌታ እግዚአብሔር ደግሞ በጦሩ ሰፈር ለዳዊት ያቆየለት ዓላማ የተለያየ ነበር፡፡ በእኛም ሕይወት እንዲሁ ነው፡፡ እኛ የምንተጋበት፣ ሰዎችን የምናስቸግርበት ነገር ሌላ እግዚአብሔር ደግሞ ያሰበልን በሚበልጥ ሁኔታ ሌላ ነው፡፡ በጦር ሠፈሩ ሲደርስ የታላቅ ወንድሙ የኤልያብ ቀúጣ በዳዊት ላይ ነደደ፡፡ አለውም፡- ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂቶች በጐች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? እኔ ኩራትህንና የልብህን ክፋት አውቃለሁና ሠልፉን ለማየት መጥተሃል አለው፡፡ ዳዊት የመጣበትን ዓላማ እጆቹ ላይ ያሉት የተጠበሱ እሸቶች ብቻ በተናገሩ ነበር፡፡ ኤልያብ ግን በጊዜው ከነበረው ተጨባጭ ነገር አንጻር ሳይሆን በልቡ ከተሰናዳው ይናገር ስለነበር እውነቱን አላስተዋለም፡፡ የመሰለንን እንደ ማውራትና በመሰለን እንደ መሥራት ያለ ኪሣራን የሚያሳጭድ ነገር የለም፡፡ ቤተሰብ (አባትና ወንድም) ፣ ሌሎች እንዲሁም እግዚአብሔር በዳዊት ላይ የነበራቸው አስተያየት የተለያየ ነበር፡፡ ግን የእግዚአብሔር ትክክል ነው፡፡ በሐዋ. 13÷22 ላይ “እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ አለ”  ተብሎ ተጽፏል፡፡ ተወዳጆች ሆይ! እግዚአብሔር ያገኘውን ሰው፣ ሰው ቢጠላው ምን ይገርማል! ሀብት ያገኘውን፣ ንብረት የጐበኘውን እንኳ ሰዎች ይጠሉ የለምን? የተጠላችሁበትን፣ የተሰደዳችሁበትን፣ የተራባችሁበትን፣ ዓይናችሁን ንጣችሁ ዕንባ የጨመቃችሁበትን ነገር ለዩ፡፡ በእርግጥ ጌታ እግዚአብሔር አግኝቷችሁ ነው ወይ? ሰዎች እንኳን የክብር ንጉሥ አዲስ ማንኪያና ጭልፋም ወደ ቤታችን ቢገባ ዓይናቸው መፍጠጡ፣ ፊታቸው መፋሙ፣ አንደበታቸው ማጉረምረሙ የሚደንቅ ጉዳይ አይሆንም፡፡ የተናቀውን ዳዊት የከበረው አምላክ አገኘው፡፡ የተገፋው ጐበዝ እግዚአብሔር እጅ ላይ ወደቀ፡፡ የታመነውም ንጉሥ ንቀትን ለጠገበው ዳዊት የሚያስከብር ነገር ይዞ ቆየው፡፡ ዳዊት በእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ላይ ስናፍናን የሚናገረውን ጐልያድ አስተዋለው፡፡ ፍርሃት ብርክ ያስያዘውንም የእስራኤል ማኅበር ተመለከተ፡፡ ከዚህም በኋላ በሕዝቡና በጠላት ፊት መሐል እጅግ የጸናውን ግንብ አቆመ፡፡ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ፡፡ እስቲ በዘመድ፣ በገንዘብ፣ በሥልጣን፣ በብልሃት የሄዳችሁባቸውን ነገሮች አስታውሱ፡፡ በዚህ ስም ያልሄድንባቸው ነገሮች ቢሳኩ እንኳን ዕድሜያቸው ቅጽበታዊ፣ መፍትሔነታቸውም ጊዜያዊ ነው፡፡ ዳዊት የአባቶቹን እውነተኛ ታሪክ ያውቃል፡፡ በእግዚአብሔር ስም የሆነላቸውን የወጡበትን ባርነት፣ የተከፈለላቸውን ባሕር፣ በምድረ በዳ የበሉትን መና የጠጡትን ውሃ፣ በስሙ የወደቀላቸውን ጠላት፣ የተከፈተውን ሰማይ፣ የወረደውንም በረከት ያስተውላል፡፡ ስለዚህ በጠላት ፊት የጸናውን ግንብ አቆመ፡፡ የክፉዎች ምክር የማይከናወንበት፣ ጦርና ፍላጻ ሊያልፈው የማይችል፣ ሟርትና ጥንቆላ የማያዘመው መመከቻ የእግዚአብሔር ስም ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ለቤታችን ዘብ ስንቀጥር እንደ መስፈርት የውትድርና ልምድን እንጠይቃለን፡፡ በጦርነት መሐል ምሽግ ሰባሪ፣ ጠላትንም አባራሪ የነበረ ለዚህም ብዙ ሽልማቶችን ያገኘ ሰው ብናገኝና ለቤታችን ዘበኛ ብንቀጥረው ምን ሊሆን ይችላል? በእርግጥ ስጋታችንን ሁሉ በእርሱ ላይ እንጥላለን፡፡ ይህን የመሰሉ ጉዳዮችንም ወደ እርሱ እናሳልፋለን፡፡ ሰዎች በጊዜ መተኛታችን፣ ቤት ጥለን ከአገር አገር መዞራችን፣ እንኳን ለኮሽታ ለፍንዳታ አለመደንገጣችን፣ ወርቅና ብር፣ ንብረትና የከበሩ ነገሮች አኑረን ጥሬ እንዳሰጣ ሰው እንኳን አለመንቃታችን ይገርማቸው ይሆናል፡፡ እኛን ግን ከዚያ ጀግና ዘብ የተነሣ ምንም አይገርመንም፡፡ ከመዝጊያና ቁልፉ በላይ፣ ከመጥሪያና ከካሜራው በላይ በእርሱ ጀግንነት፣ አላስደፍር ባይነት ልባችን ይተማመንና ያለ መስጋትም እንተኛለን፡፡ 
ታዲያ ወገኖቼ! አንድ ወታደር የነበረ ይህንን ያህል ካስተኛ እግዚአብሔር እንዴት ለዘላለም አያሳርፍም፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን በምሳሌ 18÷ 10 ላይ “ የእግዚአብሔር  ስም የጸና ግንብ ነው ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል” በማለት ከእውነት የተማረውን ይነግረናል፡፡ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ከዚህ የሚበልጥ ምንም ዓይነት ብርቱ መጠጊያ የለም፡፡ ዳዊት የእሴይን ትእዛዝ ሊፈጽም ሄደ፡፡ ቀድሞ የጠበቀውን የእግዚአብሔርን አሳብ በድል ፈጸመ፡፡ ይህም የሆነው ከጸናው ስም ከእግዚአብሔር የተነሣ ነው፡፡ ምን ጊዜም ቢሆን ወደዚህ የሮጡ ከፍታው የእነርሱ ነው፡፡ የእኛን አንድ ኮቴ ጠላት ጆሮ ላይ ሺህ የሚያደርገውም ይህ ስም ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ቀን የታቀዱ ክፋቶች ተግባር ላይ የሚውሉት ሌሊት ነው፡፡ ሰው ሲያንቀላፋ፣ አካባቢው ጭር ሲል፣ ብርሃኑ ዓይን ያዝ ሲያደርግ የታሰበው ይተገበራል፡፡ ታዲያ ሰዎች ተዘግቶ ከነበረው ቤታችን ማለዳ የሚጠብቁት መርዶ፣ የተበላሸ አእምሮ፣ የሰለለ ነገር ነው፡፡  ይህ ስም ያላቸው ግን ወጥመዱን ይሻገራሉ፡፡ ለጠላትም እልልታ አይሆኑም፡፡ ያመኑት ይከተላቸዋል፡፡ አለኝ ያሉትም ጌታ ይጋርዳቸዋል፡፡ በዚህ ስም በላያችን የቆሙ ይዋረዳሉ፡፡ ንሴብሖም ለእግዚአብሔር ይሆናል፡፡
1ሳሙ.18 ከድል በኋላ የዳዊት ሕይወት ምን እንደሚመስል ያስነብበናል፡፡ ፍልስጤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ እየዘመሩና እልል እያሉ ከበሮና አታሞ ይዘው ንጉሡን ሳኦልን ሊቀበሉ ሴቶች ከእግዚአብሔር ከተሞች ሁሉ ወጡ፡፡ እነርሱም ሳኦል ሺህ ዳዊት እልፍ ገደለ እያሉ ተናገሩ፡፡ የእግዚአብሔር አሠራር ለአስተዋለው ከመደነቅም በላይ ነው፡፡ ያ ሕዝብ የወጣው ንጉሡ ሳኦልን ለመቀበል ደግሞም ለጆሮ በሚያምር ዜማ ለማስደሰት ነው፡፡ ዳሩ ግን ዳዊት ተሞካሽቶ ሳኦል ደግሞ አዝኖ ተመለሰ፡፡ ባላቅ የእስራኤል ሕዝብ እንዲረገም በበለዓም አንደበት ላይ ገንዘብ ከፈለበት ነገር ግን በለዓም ሕዝቡን ሊረግም ሲወጣ ንጉሡ ባላቅ በከፈለበት አንደበት የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሕዝቡን መረቀበት (ባረከ)፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን ያደርግ ዘንድ ቻይ አሳቡም ይከለከል ዘንድ ከቶ የማይቻል ነው፡፡ ሳኦልም በሆነው ነገር ተቆጣ፡፡ በምዕራፉ መጨረሻ ቀúጥር ላይ እንደምናነበውም ዕድሜውን ሁሉ ለዳዊት ጠላት ሆነ፡፡ ይህ በእጅጉ ልብን የሚያሳዝን ነገር ነው፡፡ መልካም ነገር የሚነዝራቸው፣ በበጐ ነገር መደረግ ታመው አልጋ የሚይዙ፣ ከተፋቀሩ ይልቅ ተናከሱ ልባቸውን ስለሚያስደልቀው፣ ተንኮል ዕረፍት አልባ ስላደረጋቸው ወገኖች ማሰብ ለአንድ እውነተኛ ክርስቲያን ጭንቅ ነው፡፡ ሳኦል ስለ ዳዊት ማሰብ የጀመረው ጀብደኝነቱ ሲነገር፣ ለሕዝቡም ለዋለው የጀግና ውለታ ሙገሳ ሲመጣ ነው፡፡ እስቲ ጠይቁ፡- ስለ ጥጋባችሁ ያናፈሱ ሰዎች ሆዳችሁን ሲቆርጣችሁ፣ ጨጓራችሁ የሚፈጨው አጥቶ አደን ሲሰማራ የት ነበሩ? ጠጪ ናቸው ብለው ያወሩ ብርጭቆ ውሃ አቀባይ አጥታችሁ ጥም ሲሰማችሁ የት ነበሩ? በጥፍሩ መሄድ ነው የቀረው የሚሉ ሰዎች አልጋ ይዛችሁ በነበረ ጊዜ ወዴት ነበሩ? በብዙ ትገረሙ ይሆናል፡፡ ተርባችሁ ያልደረሱ የጠገባችሁ ቀን ጨጓራችሁ በሰከንድ ምን ያህል እንደሚፈጭ አስልተው ሊነግሯችሁ ይችላሉ፡፡ የሣር ፍራሽ ላይ ትተኙ በነበረበት ወቅት ለአይዞህ የሰሰቱ ወገኖች የዕቃ ለውጥ ስታደርጉ አዲስ አዲስ የሚሸት ነገር ካለ ቤት ሳታደርሱት ስሪቱ የየት አገር እንደሆነ ደውለው ሊነግሯችሁ ይችላሉ፡፡ በጉብዝናችን ወራት ያገኘነው አምላክ ግን የሕፃንነታችንም ወዳጅ ነበረ፡፡ እርሱ የወደደን ከለበስን፣ ነፍስ ካወቅን፣ ባልንጀሮችን ካፈራን፣ በትምህርትና በዕውቀት ካደግን፣ ትዳር ከመሠረትን አይደለም፡፡ በራቁትነት (በባዶ) ወራት፣ የእኔ ብለን የምንቆጥረው ምንም ባልነበረን የሕፃንነት ወቅት ነው፡፡ ለዚህም ነው የምንጨምረውም ሆነ የምንቀንሰው ታሪካችን እግዚአብሔርን የማይደንቀው፡፡ የሰጠውን ቢነሳ፣ የነሳውን አብዝቶ ቢመልስ ተቆጭ የሌለው ጌታ ስሙ ቡሩክ ይሁን! 
ዳዊት ግን በዕድሜ ልክ ጠላቱ ፊት በገና ይደረድር ነበር፡፡ እኛ ትላንትና ባስቀየሙን ሰዎች ፊት ሰላምታ እምቢ ብሎናል፣ ቅድም ለተቀየምናቸው ሰዎች ልባችን ለበጐ ቃል አሻፈረኝ ብሎብናል፡፡ የዳዊት እምነት በጸናው ግንብ ላይ ነው፡፡ እርሱ የሚቆጥረው ሳኦል ያደረገበትን ሳይሆን እግዚአብሔር ያረገለትን ነው፡፡ እርሱ ሳኦል ባቀደበት አይሰጋም፡፡ እግዚአብሔር ያቀደለትን ይናፍቃል፡፡ ሳኦል መልካም የዋለለትን ዳዊት ከግንቡ ጋር አጣብቄ እመታዋለሁ ብሎ ጦሩን ወረወረ፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ፡- “አብርሃም ባያውቀን እስራኤልም ባይገነዘበን አንተ አባታችን ነህ አቤቱ አንተ አባታችን ነህ ስምህም ከዘላለም ታዳጊያችን ነው” (ኢሳ. 63÷16) ይላል፡፡ የኢያሪኮን ቅጽር ያፈረሰ፣ አማሌቅን ምድረ በዳ ላይ ሽንፈትን ያለበሰ፣ ሕዝቡን በድል የመራ ይህ ስም ነው፡፡ ሳኦል ከዳዊት ጀርባ ያለውን የሰውም እጅ ያነጸውን ግንብ ያይ ነበር፡፡ ዳዊት ደግሞ በእምነት በእርሱና በጠላቱ መሐል ያለውን የጸና ግንብ ያስተውል ነበር፡፡ ባልንጀራ የጐዳችሁ፣ ወዳጅ ፍላፃ የወረወረባችሁ፣ አምናችሁ የተከዳችሁ፣ አጉርሳችሁ የተነከሳችሁ፣ በወርቅ ፈንታም ጠጠር የተመዘነላችሁ፣ ወንድሜ ያላችሁት ቃየል የሆነባችሁ ወገኖቼ ሁሉ ተቤዢአችሁ ብርቱ ነው፣ ትጥቁም ምሽግን ለመስበር ኃያል ነው፣ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፡፡ ሙግታችሁንም ፈጽሞ ይምዋገታል (ኤር. 50÷34)፡፡ ይህ ስም ከስም ሁሉ በላይ ነው (የሐዋ. 4÷12)፡፡ የጨለማው ታሪክ በሚደነቅ ብርሃን የተተካበት፣ የጥል ግድግዳ የፈረሰበት፣ የበረከትን ደጆች ያስከፈተ፣ ባርነት ላይ ነጻነትን ያወጀ፣ ለዓለሙ ሁሉ መዳን የተሰጠ፣ ሕያውነቱም የዘላለም የሆነ ስም ክርስቶስ ኢየሱስ ነው!

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።