የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በፍቅር ብቻ

  

ነፋስና ፀሐይ “እኔ ነኝ የማሸንፈው ፣ እኔ ነኝ” እያሉ ተከራከሩ ። ነፋስም፡- “እዚያ ታች ጋቢ ለበሶ ፣ ቀጸላ ደርቦ የሚሄደውን ሰው ጋቢውን ገፍፌ ፣ ቀጸላውን መሬት ጥዬ ሳሸንፈው ታዪአለሽ ፣ ደግሞም ኮሳሳ ነው” አለ ። ፀሐይ ግን ፈገግ ብላ፡- “አታሸንፈውም” አለችው ። ነፋስም በጉልበቱ ተመክቶ “ሳሸንፈው ታዪአለሽ” በማለት ፎከረ ። ነፋስም ሽቅብ ቁልቁል ፣ ከግራ ወደ ቀኝ መንፈስ ጀመረ ። በዚህ ጊዜ ያ ኮሳሳ ሰው መጀመሪያ የውስጥ ኮቱን ቆለፈ ። ቀጸላውንም በአንገቱ አሰረ ። ጋቢውንም ጨምድዶ ይዞ አልቅም አለ ። ነፋስም በጉልበቱ ማስጣል እንዳልቻለ ባወቀ ጊዜ አዘነ ። ፀሐይም፡- “የሰውዬውን ልብስ እንዴት እንደማስወልቀው ታያለህ” አለች ። ነፋስም በስላቅ፡- የእኔ ጉልበት ያልቻለውን አንቺ እንዴት ትቺያለሽ?” አላት ። ፀሐይ ግን ፈገግ ማለት ስትጀመር ያ ኮስማና ሰውነቱ በሙቀት እየተበረታታ መጣ ። የፀሐይ ሙቀት ቀስ እያለ ሲጨምር ቀጸላውን አወለቀ ፣ ጋቢውንም አጣጥፎ በእጁ ያዘ ። አሁንም ሙቀቷን ስትጨምር የቆለፈውን ኮቱን መክፈት ጀመረ ። ፀሐይም ቀስ እያለች ግለቷን በመጨመር ልብሱን በሙሉ በፈቃዱ አስወለቀችው ። ፀሐይም በጉልበት ሳይሆን በፍቅር ፣ በመግለብለብ ሳይሆን በትዕግሥት ድል ማድረግ ትችላለህ በማለት ነፋስን አስተማረችው ። 

ብዙ ጦርነቶችን ስናይ በኃይልና በጉልበት ሳይሆን በቆራጥነትና በጽናት ድል እንዳለ ያስተምሩናል ። “ለመውረር ጉልበት እንጂ ምክንያት አያስፈልግም” ይላሉ ። ጉልበታም ሁነው የሰው አገር የወረሩ ግን ዛሬ አንዳቸውም ከወረሩት አገር የሉም ። በአድዋና በማይጨው ጦርነት ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ተዋድቀው ነጻነትን አስከብረዋል ። ኢትዮጵያውያን ለመዋጋት እውነትና ምክንያት ሲደግፉአቸው ተዋጊ የጣሊያን ወታደር ግን የሰው አገር ወራሪ መሆኑን ውስጡ ይነግረዋል ፣ “በእኔ ሊደረግብኝ የማልሻውን በሰው እያደረግሁ ነው” የሚለው ምክንያት አልባነት ያራቁተዋል ። በዚህ ምክንያት ያለ ኃይል መመጣጠን ድል ለኢትዮጵያውያን ሆነ ። ድል በእውነት እንጂ በጉልበት ፣ በፍቅር እንጂ በግዳጅ አይገኝም ። 

በሰላም የሚኖሩትን ሕዝቦች የሚፎካከሩ ኃያላን ያወድሟቸዋል ። በዘመናዊው ዓለም የኃያላን የትግል ሜዳ ድሆች መሆናቸው ያሳዝናል ። ቅኝ ለመግዛት ቁጭ ብለው መክረው ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ምዕራቡ ላንተ ምሥራቁ ለእኔ ብለው ተከፋፍለው ፣ ቆመው ተኩሰው ፣ ብዙ ንጹሐንን ጨርሰው ፣ ወደማያውቁት አገር አግዘው ፣ ንብረታቸውን ከኋላ በስርቆት መርከብ ጭነው ፣ ያለ ባሕልና  ቋንቋ አስቀርተው ፣ የአተላ ማፍሰሻ አድርገው መና አስቀሩአቸው ። ከዚህ ሁሉ በኋላ ሦስተኛው ዓለም ፣ የጨለማው ምድር በማለት ስም ሰጡአቸው ። ኃያላን በፉክክር በሰላም የሚሄደውን ወገን እያወኩት ነው ። ፉክክር የልጅነት ጠባይ እንጂ የብስለት ማሳያ አይደለም ። ይልቁንም በሌላው ሞት ላይ መደራደር ከሰውነት ውጭ የሚያደርግ ነው ። 

ነፋስ ይግለበለባል ። የከበደውን ሊያቀል ፣ የለበሰውን ሰው ሊያራቁት ፣ በሰላም የሚሄደውን ወደ ኋላ ሊመልስ ሽቅብ ቁልቁል ይላል ። እንደ ነፋስ የሌሎችን ቀጸላ ወይም ዝምታ ለመስበር የሚታገሉ ብዙ ናቸው ። ተናግረው ለማናገር ፣ ተሳድበው ስድብ ለመስማት የሚሹ አያሌ ናቸው ። ባለጌን የምንበቀለው በዝምታ ነው ። ምላሽ ከሰጠነው አንደኛ ሰሙኝ ይላል ፣ ሁለተኛ አከበሩኝ ብሎ በደስታ ይፈነጥዛል ። የባለጌ ሞቱ መልስ ማጣቱ ። አንዳንድ ሰዎች ቆመዋል ። የሚሄድ ሰው አይወዱም ። ቆሞ ወግ የሚያወጋቸው ፣ ካልተቻለ የሚሰድባቸው ይሻሉ ። ስለዚህ የስድብ ናዳ ሰው ላይ ያወርዳሉ ። በሰላም የሚሄደውን ራሳቸው ጀምረው በሚጨርሱት ነገር ይወተውቱታሉ ። ከራሱ በላይ እንደሚያውቁት ይናገራሉ ። መጋረጃ ገጥሞ ፣ በር ዘግቶ ፣ ጣራ ከድኖ የሠራውን እናውቃለን በማለት እግዜር ነን ይላሉ ። ራሳቸው ከሳሽ ፣ ራሳቸው ምስክር ፣ ራሳቸው ዳኛ ሁነው በእውር ድንብር የሚመሩትን ሕዝብ “ይሰቀል” ብለው ያስጮሁበታል ። እንደ ነፋስ የሚግለበለቡ ፣ እንኳን የምሰድበው የሚሰድበኝ አጣሁ እያሉ ሰውን ዝቅ ሲያደርጉ የሚውሉ አሉ ። መልስ በተሰጣቸው ቍጥር የበላቸውን እያከኩላቸው ስለሆነ እየጋሉ ይመጣሉ ። ለመማር አእምሮአቸውን ፣ ለመሥራት ጉልበታቸውን ፣ ለመኖር ጠባያቸውን ፣ ለማገልገል ጸጋቸውን ስለጣሉ አሁን እንደ እነርሱ ቆሞ የሚሰድባቸው ይፈልጋሉ ።

ነፋስ የሚነፍሰው ሰውዬው በዕድሜው ልክ የለበሰውን የክብር ልብሱን ለማስወለቅ ነው ። ትንንሽ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ትልልቅ ሰዎችን በማዋረድ ይደሰታሉ ። ወይም ትንንሽ አስተሳሰብ ያላቸው በትልልቆች ውድቀት ይረካሉ ይባላል ። ነጥቡ ያለው ማነው የሚሰድበኝ ? ላይ ነው ። “ጭራ ቀረሽ ነው ስሜ” የምትል ዘፋኝ ንጉሡ ያወጡልኝ ስም ነው በማለት ትወደው ነበር ። በትልቅ ሰው መሰደብም እንደ ክብር ነው ። በአእምሮአቸው ገብቼ ፣ በአፋቸው ወጣሁ እንደ ማለት ነው ። እንደ ነፋስ የሚግለበለቡ የሰውን ክብር ዝቅ የሚያደርጉ ፣ በዕድሜ የሚበልጡአቸውን አንተ ፣ በማዕረግ ከፍ ያሉትን አንቺ ለማለት የሚደፍሩ ናቸው ። የሰውን ክብር በስድብ ልናቃልል እንችላለን ፣ ትንሽ ልናደርገው ግን አንችልም ። ክብሩን ልንገፍ እንችላለን ፣ ክብሩን የእኛ ማድረግ ግን አንችልም ። ትልቅ ሌብነት የማይሰረቅ ነገርን ለመስረቅ መሞከር ነው ። የሌሎች ጸጋ ፣ ጠባይና ክብር ልስረቅህ ብንለው የማይሰረቅ ነው ። 

ሰዎች የሚያምኑትን ነገር በጉልበት አስለቅቃለሁ ማለት ሞኝነት ነው ። እንደ ዋዛ የያዙትን ነገር አጥብቀው የሚይዙት እኛ በጉልበት ለማስለቀቅ በሞከርን ቍጥር ነው ። ብዙ ሃይማኖቶችን ተመልከቱ ። በጉልበት ፣ መቃብር በመከልከል ፣ በመሳደብ ፣ ከዕድር በማስወጣት ፣ በማውገዝ ለማስጣል ሞከርን ። ዛሬ ግን በአናታችን መጡ ። ካህሊል ጅብራን፡- “በሰው ልጅ እግር ላይ ስትቆም ክንፍ አበጀህለት” ብሏል ።

ዘበኛዬ ነው ፣ የቤት ሠራተኛዬ ናት ፣ በእኔ ሥር የሚተዳደሩ ናቸው ፤ ስለዚሀ እኔ ያመንኩትን ማመን አለባቸው ብለን ወደ ጉልበት ስንሄድ ኮሳሳዎቹ ኃያላን እየሆኑ ይመጣሉ ። መኖር ብንከለክላቸው መሞትን እንደማንከለክላቸው ያውቁታል ። በሰማዕትነት ልክ ሲጠብቁን እኛን ነፍሰ ገዳይ ያደርጉናል ። ሰው የያዘውን ነገር በጉልበት ማስጣል አይቻልም ። በልጆቻችን ላይ የምንመዘው ዱላ ፣ በአገራት ላይ የምንጥለው ማዕቀብ ምንም ለውጥ አያመጣም ። ለዚህ እነ ሰሜን ኮሪያ በማዕቀብ ብዛት ውስጥ የኒውክለር ባለቤት ሁነዋል ። ልጆቻችንም ደስታዎቻችን መሆናቸው አብቅቶ ስጋቶቻችን ሁነዋል ። በጉልበት የሚያሳምን በመጨረሻ አፍሮ ይቀራል ። እኛ ያላመነውን ካላመናችሁ ሥልጣን አይገባችሁም የሚል አስተሳሰብ ረጅም መንገድ መሄድ አይችልም ። በጉልበት ሰውን እናጠነክራለን እንጂ አናሸንፈውም ። በዘር ፣ በሃይማኖት የተቋቋሙ ባንኮች በጉልበት ለማሸነፍ የሚጥሩ ናቸው ። የገፉአቸው ሰዎች ግን ከእነርሱ በላይ ጠንክረው ይመጣሉ ።

ከሳሽ ንጹሕ የሚሆነው ተከሳሽ እስኪመጣ ነው ይባላል ። ተከሳሽ መጥቶ መናገር ሲጀምር ከሳሽ ማፈር ይጀምራል ። “ከሳሽ የተከሳሽን ልብ ቢያውቅ ኖሮ ፍርድ ቤት ባልሄደ ነበር” ይባላል ። ኮሳሳ የምንላቸው በውስጣቸው ያለውን ኃይል እንዲወጣ የሚያደርገው በጉልበት የሚሞክራቸው ሰው ሲመጣ ነው ። በውስጣቸው ያለውን መንፈሳዊ ብርታት ነፍሳዊ እውቀት ብናውቅ በጉልበት አንሞክራቸውም ነበር ። ሰው በላይ ሰውነቱና በጨርቁ አይለካም ። አፍሪካውን፡- “ላም በሕይወት እስካለች ቀንዷን የሚቆርጥባት የለም” ይላሉ ። 

ሰዎችን መውደድና መፈለግ ያለብን ውርርድ ውስጥ ሁነን ከሆነ የወደድነው ቁማራችንን ለመብላት ነው ። “ያንን ሰው የእኔ አደርገዋለሁ ፣ ልቡን በፍቅር ጥዬ ሲሸነፍ አሳያችኋለሁ” ማለት ፍቅርን ማርከስ ነው ። በእውነተኛ መንገድ ልናሸንፋቸው የምንፈልጋቸውን ሰዎች መጀመሪያ ጥሩ ፈገግታ እናሳያቸው ። ሸክማቸውን እንጋራቸው ። ራሳቸው እስኪያወሩልን ድረስ ታማኝ እንሁንላቸው ። ውስጣቸውን እስኪገልጡልን ድረስ እንታመንላቸው ። ሰውን በፍቅር እንጂ በጉልበት ፣ በትዕግሥት እንጂ በመግለብለብ ገንዘብ ማድረግ አይቻልም ። 

“የሚቀብሩ ምስጋናዎች እንዳሉ ሁሉ ከፍ የሚያደርጉ ተቃውሞዎችም አሉ።” 

በጉልበት ሳይሆን በፍቅር የምናሸንፍበት ዓመት ይሁንልን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መስከረም 2 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ