የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በፍቅር የረጠበ ክርስትናን አድለን

“አቤቱ የአባቶቻችን አምላክ ሆይ ፥ በሰማይ ያለህ አምላክ አንተ አይደለህምን ? የአሕዛብንስ መንግሥታት ሁሉ የምትገዛ አንተ አይደለህምን? ኃይልና ችሎታ በእጅህ ነው፥ ሊቋቋምህም የሚችል የለም ።” 2ዜና. 20፡6።
የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ከመጣበት ወራሪ ያዳንህ እግዚአብሔር እኛንም ከመጣብንና ካመጣነው መከራ አድነን ። የብርቱዎችን ልብ መልስ ፣ ለትሑታንም ጸጋን አልብስ ። ለሚፈሩህም ድልን ስጥ ። በጥዋት በማታ ደጅ ለሚጠኑህ ፈጣን የሆነች እጅህ ትድረስላቸው ። አቤት ፣ አቤት እያሉ አንተን የሚጠሩ “እግዚአብሔር አያሳፍርም” ብለው ምስጋና ይንገሩ ። የወጣውን በሰላም እንድታስገባው ፣ ደጁን የፈራውን ነጻነት እንድትሰጠው ፣ የሚደክመውን የእጁን ፍሬ እንድትባርክለት ፣ የሚያገለግልህን ካህን በሞገስ እንድትከልል ፣ ዘመነ ቅዱሳን ዘመነ ጻድቃን አድርገህ የሰጠኸንን ዘመን እንድትባርክ እንለምንሃለን ። ካሳዳጅ የተነሣ ሊማጸኑህ የመጡትን ፣ ከጭንቀት የተነሣ እግዚአብሔር ወዴት ነው የሚሉት እባክህ አትርሳ ።
የምድር ነገሥታትን ልቡና ወደ አንተ መልስ ። ምክራቸውን በምክርህ ቀድሰው ። ስብሰባቸውን በቅዱስ ፍርሃት ሙላው ። ለበታች የሚያዝኑበት ፣ ድሀ ተበደለ ፣ ፍርድ ተጓደለ የሚሉበት ዘመን ይሁንልን ። የበታቹም የበላዩን የሚያከብርበት ዘመን አድርግልን ። የምድር ነገሥታት ስደተኛን የሚወዱበት ፣ በተንኮል ምክር ሳይሆን በጽድቅ ምክር የሚያስተዳድሩበት እንዲሆን እባክህን ይህን የእኛን ዘመን ባርከው ። ያለ ፍርድ የሚሰቃዩትን ፣ ሊገደሉ የተፈረደባቸውንም በምሕረትህ አድን ። በሁሉ ቤት ያለውን ድብቅ ልቅሶ የምትሰማ አንተ ነህና አቤቱ ሰምተህ በረድኤት መልስልን ።መሥዋዕታችንም በብሩህ ገጽ ተቀበልልን ። ቤተ ክርስቲያንን አጽናልን ። ሃይማኖትን ጠብቅልን ።
አቤቱ ጌታችን ሆይ በምንችለውም በማንችለውም ያንተ ኃያል ክንድ ይዘርጋልን ። የፈራናቸውን ቀኖች አሻግረን ። ለአገራችን ፍጹም ትንሣኤ ለሕዝቧም ፍቅር ሰላም እዘዝልን ። ድሆቿን እንጀራ አጥግብልን ። በሽተኞች እንዲፈወሱ ፣ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ያሉ ትንሣኤ እንዲያገኙ ፣ በማይድን በሽታ የተያዙ በተአምራትህ እንዲፈቱ ፣ በመግባት በመውጣታቸው ፍርሃት የሚንጣቸውን ልባቸውን በሰላም እንድትጠብቅ ፣ ነገ ምን እሆናለሁ የሚሉትን እምነት እንድታለብስ ፣ የራቀውን እንድታቀርብ ፣ የቀረበውንም እንድታጸናልን አቤቱ እንለምንሃለን ። በመካከላችን የደከመች ነፍስን አበርታ ። በስህተት ትምህርት ተይዛ ፣ በኑፋቄ ማዕበል ተመትታ የምትጨነቀውን መንፈስ ወደ ቀና ጎዳና መልስ ። የምድር ነገሥታት ሁሉ ገዥ አንተ ነህና ግፍ የሚፈጸምባቸውን አገሮችና ሕዝቦች ዛሬ ታደግ ። ሳይኖሩ የሚሞቱትን፣ ይህች ዓለም በሰቆቃ የተቀበለቻቸውን ሕፃናትን እባክህ አድን ። ለእኛም መልካም ያደረጉትን አትርሳ።
ጌታ ሆይ መለያየትን ሁሉ አርቅልን ። አንድ ልብና አንድ ቃል መሆንን ስጠን ። ወንድም ስለ ወንድም በጎ የሚናገርበትን ዘመን አምጣልን ። ነቀፋና ሐሜትን አርቅልን ። በፍቅር የረጠበ ክርስትና አድለን ። ኃይልም መንግሥትም ያንተ ነውና ለዘላለሙ አሜን ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ