መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ማርያም » ቡርክት ሆይ !

የትምህርቱ ርዕስ | ቡርክት ሆይ !

ከታደሉት የታደልሽ ነሽ ። የታደልሽ ሆነሽ ድሀ መሆን ፣ የታደልሽ ሆነሽ በበረት መውለድ ፣ የታደልሽ ሆነሽ በግብጽ መሰደድ ፣ የታደልሽ ሆነሽ በታላቅ ኀዘን ማለፍ ምሥጢሩ ምን ይሆን ? ለካ ባለጠጋ የሚባለው ገንዘብ ያለው ሳይሆን እግዚአብሔር ያለው ነው ። የታደለም ዝና ያለው ሳይሆን ዜና ሥላሴን የሚያውቅ ነው ። እኛ አምላክን በሕልም አየን ብለን “አትንኩኝ የሹም ዶሮ ነኝ” እንላለን ። አንቺ ቡርክት ሆይ ፣ የአምላክ እናት ሆነሽ መከራን በደስታ ትቀበያለሽ ። ጸጋ ሲበዛ መከራ ይበዛል ፣ መከራ ሲበዛም ጸጋ ይበዛል ። ልጅሽ የሕማም ሰው ነው ፣ ባንቺም በነፍስሽ ሰይፍ አለፈ ። ከሐዋርያት በፊት መስቀሉን ተሸከምሽ ፣ ከአማንያን ቀድመሽ ልጅሽን ተከተልሽ ። አዛኝቱ ሆይ ሰላምታ ይገባሻል !

የክርስቶስ የመስቀል ጉዞ የተጀመረው ገና በተፀነሰ ቀን ነው ። በሄደበት ሁሉ ተከተልሽው ። ልጅሽ ባለ መስቀል እንጂ መስቀል አልባ አይደለም ። አንቺ ስለ ልጅሽ ኖርሽ ፣ እርሱ ስለ ዓለሙ ሁሉ ሕይወቱን ሰጠ ። የመሥዋዕቱን በግ የተንከባከብሽ ፣ እንደ እናት እያለቀስሽ ፣ እንደ አማኝ በልጅሽ ሞት ያመንሽ ቡርክት ሆይ ደስ ይበልሽ ! እናትነትን ከአማኝነት ማስተባበር ፣ ለመስቀል አጋር እንጂ እንቅፋት አለመሆን ይደንቃል ! የወደደው ጴጥሮስ እንኳ ፍኖተ መስቀሉን ሊያስተጓጉል ተነሣ ፣ የወለድሽው አንቺ ግን አንድም ቀን መስቀሉን አልተጋፋሽም ። በቃና ዘገሊላ በተወደደ ምልጃሽ ውኃው ወደ ወይን ጠጅ በተቀየረ ጊዜ መስቀሉ እንደሚፋጠን ታውቂ ነበር ። ቃና ዘገሊላና ቀራንዮ ይሳሳባሉ ። በቀራንዮ ሙሽራው ክርስቶስ ፣ በደም ማጫ ቤተ ክርስቲያንን የራሱ አደረጋት ። በቃና ዘገሊላ ተአምር ፣ በቀራንዮ ቤዛነት ሆነ ። በቃና ቻይነቱ ፣ በቀራንዮ ቤዛነቱ ተገለጠ ። በቃና ለሰርገኞቹ አዘንሽ ፣ በቀራንዮ ለልጅሽ አዘንሽ ። መስቀል የተለየውን ክርስቶስን ሳይሆን ባለ መስቀሉን ኢየሱስ አገለገልሽ ። ቡርክት ሆይ አንቺ ከሴቶች ሁሉ የተለየሽ ነሽ ።

የያዕቆብና የዮሐንስ እናት ለልጆችዋ ሹመትን ለመነች ። አንቺ ግን ልጅሽ ቤዛ እንደሚሆን እያወቅሽ እያለቀስሽ ትደሰቺ ነበር ። ልቅሶው የእናትነት ፣ ደስታው የአማኝነት ነው ። አዳምን የሠሩ እጆች ካልተቸነከሩ አዳም አይድንምና ። እንደ ለመንሽ ተጽፏል ። እርሱም ለራስሽ ሳይሆን ለሌሎች ነው ። በደጅ ስታድሪ ቤትን ፣ ስትሰደጂ አገርን ፣ ስታዝኚ ሞትን አለመንሽም ። የተመሰገነው ትዕግሥትሽ ለልጅሽ የማዳን ሥራ ምቹ ነበር ። ቡርክት አንቲ እምአንስት በማለት ሰማይ አድንቆሻል ። ከሴቶች ሁሉ ሳይሆን ከነሣራ ፣ ከነርብቃ ተነጻጽረሽ አንቺ ልዩ ነሽ ። ሣራ ብትወልድ ይስሐቅን ፣ ኤልሳቤጥ ብትወልድ ዮሐንስን ነው ። አንቺ ግን የወለድሽው ንጉሠ ነገሥት ፣ አምላከ አማልክት ኢየሱስ ክርስቶስን ነው ። ከሴቶች ተለይተሸ የታደልሽ ነሽ ።

ልጅ ሁሉ መኖርን ዓላማ አድርጎ በዓለም ይወለዳል ፣ ያንቺ ልጅ መሞትን ዓላማ አድርጎ ተወለደ ። የበጉ እናት ፣ የመሥዋዕቱ አገልጋይ ሆይ ቡርክት አንቺ እምአንስት ነሽና ደስ ይበልሽ። መስቀልን ከደስታ ፣ ደስታን ከመስቀል ጋር አስተባብረሻልና ። ብርሃን በመስተዋት ቢያልፍ መስተዋቱ አይሰበርም ፣ ወዝ ቢወጣ ቆዳ አይቀደድም ። አንቺም በኅቱም ድንግልና ወልደሻል ፣ ድኅረ ወሊድም ለዘላለም ድንግል ሆነሽ ትኖሪያለሽ ። እናትነትና ድንግልና የታረቁብሽ ሆይ ተፈሥሒ !

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 30 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም