የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ባላገር ለሆናችሁ

“እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም ።” ኤፌ. 2 ፡1 9 ።

የይሁዲ እምነት በዋናነት የተሰጠው ለእስራኤል ሲሆን ሌሎችን በጥምቀት አማካይነት በመቀበል የሃይማኖቱ ተከታዮች ያደርግ ነበር ። እነዚህ አሕዛብም ከአይሁድ ጋር በአንድነት ቆመው ለማመለክ አይችሉም ነበር ። በአሕዛብ አደባባይ ላይ ሁነው ያመልኩ ነበረ ። በመካከላቸውም የሚለይ ግንብ ነበረ ። አንዱን አምላክ በግንብ አጥር ተለያይተው ያመልኩት ነበር ። በዚህም በዚያም ውስጥ ቆመው ለሚጸልዩ ግን አንድ ሰማይ ይታያቸው ነበር ። ይህ ግንብ እስራኤላውያንን ትምክሕተኛ ሲያደርግ አሕዛብን ደግሞ ያሸማቅቅ ነበር ። በአብርሃም ሃይማኖት አንድ ከመሆን ይልቅ በአብርሃም የሥጋ ልጅነት አንድ መሆንን ያስበልጡ ነበር ። የአብርሃም ዘር ግን የምድር አሸዋ የተባሉት እስራኤል ብቻ ሳይሆኑ የሰማይ ከዋክብት የተባሉት አሕዛብም ነበሩ ። ምድረ እስራኤል ሁሉን አንድ ማድረግ ፣ መቅደሱም ሕዝብና አሕዛብን ማስታረቅ አልቻለም ነበር ። ሰማይ ግን ሁሉን አንድ እንዲያደርግ ክርስቶስ ከልደቱ እስከ ሞቱ የአንድነትን ሥራ ሠራልን ። እነዚህ የኤፌሶን ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም መቅደስ በነጻነት መቆም ፣ ከአይሁድ ጋርም አንዱን አምላክ ማምለክ አይችሉም ነበር ። ክርስቶስ ግን በደሙ ዋጋ ገዝቶ ፣ ሁሉን በራሱ አንድ አድርጎ ፣ የሁሉም ብቃት ራሱ ሁኖ ወደ ሰማይ ማደሪያ አስገባቸው ።

“እንግዲያስ” ይላል ። ነጻነትን አግኝተው ሳለ አሁንም በባርነት ሕሊና ለሚኖሩት ፣ እንዲደረግላቸው ሳይሆን የተደረገላቸውን እንዲያስተውሉት ዘራፍ ብሎ ይናገራል ። ለብዙ ሰው መቃተት አዲስ ቸርነት መደረግ አያስፈልገውም ። የተደረገለትንና የጨበጠውን ጸጋ እንዲያስተውለው መምከር ብቻ በቂ ነው ። ዳቦ ይዞ ስለ ዳቦ የሚያለቅስን ፣ ውኃ ምንጭ አጠገብ ቆሞ ውኃ ጠማኝ እያለ የሚያነባውን እግዚአብሔር የሚረዳው ዓይኑን በመክፈት ብቻ ነው ። በክርስትናው በጎ በረከት መደሰት በሚገባን ልክ አለመደሰታችን የሰማይ ወዳጆቻችንን ያሳዝናል ። ያ ደስታ እሳትንና ስለትን ያስናቀ ደስታ ነው ። ያ ደስታ የሚጨበጥና እንደ ጉም በሆነው የዓለም ነገር ውክክ ማለትን ያስቀረ ደስታ ነው ። እግዚአብሔር ባደረገልን ነገር ከእኛ የሚጠበቅ ነገር ካለ አምስት ነው ። የመጀመሪያው መደሰት ፣ ሁለተኛው ማመስገን ፣ ሦስተኛው መመስከር ፣ አራተኛ ራሳችንን የሚጎዳንን ኃጢአት መተው ፣ አምስተኛ ጸጋቸውን ላላወቁና ከጸጋው ለተራቆቱ መጸለይ ነው ። ይህም ጸጋ የነበረው ነቢዩ ሳሙኤል ጸጋ ለራቀው ንጉሥ ሳኦል እንዳለቀሰው ነው ።

በምድር ላይ ወላጅ ያወረሰን ርስት ፣ እኛም ለፍተን የገዛነው ቤት ንብረት ላይኖረን ይችላል ። በምድር ላይ ራሳቸውን የአገር ፈጣሪ አድርገው በሚያስቡ ገዥዎች ተሰድደን ፣ በሰው አገር የምንኖር ልንሆን እንችላለን ። በምድር ላይ የለፋንበት ሀብት ተወርሶ በሌሎች እጅ እያየነው ሊሆን ይችላል ። ሐዋርያው ግን፡- “ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ” ይላል ። ከመቼ ጀምሮ ነው ካልን “ከእንግዲህ ወዲህ” ይለናል ። ስንሞት ወይም በዕለተ ምጽአት ሳይሆን ከአሁን ጀምሮ የቅዱሳን ማኅበረተኞች ፣ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ሁነናል ።

ባላገር የሚለውን ቃል ገጠሬ ፣ ያልሰለጠነ ፣ ዘመን ያልገባው ብለን እንተረጕመው ይሆናል ። ባላገር ማለት ግን “ባለሀገር” ወይም ሀገር ያለው ማለት ነው ። ያንን ራሱን የሆነውን ፣ በሌሎች ጌጥ የማይኮራውን ፣ የማንነት ቀውስ የሌለበትን ፣ የራሱን አለባበስና ባሕል ጠብቆ የሚኖረውን ፣ ሃይማኖትን በውሰት ያላመጣውን ባለ ሀገር ካልን እኛ ሀገር አልባ መሆናችንን እየመሰከርን ነው ። አንድ አስቸጋሪ ወጣት ቤተሰቦቹ ብናርፍ ብለው አሜሪካ ላኩት ። ከስንት ጊዜ በኋላ ደውለው “እንዴት ነህ ? ለመድህ ወይ ?” ብለው ቢደውሉለት “እንግሊዝኛውን ሳለምደው አማርኛው ጠፋኝ” ብሎ መለሰላቸው ። ሀገር አልባ ማለት እንዲህ ያለው ነው ። የሌላውን ሳይዝ የራሱን የለቀቀ ፣ የራሱን ሳይዝ የሌላውም ያመለጠው ማለት ነው ። ዘመናዊነት ዥንጉርጉርነት ፣ ወጥነት ማጣት ፣ ሁለት ዓይነት አለባበስ ፣ ሁለት ዓይነት የቋንቋ ቅይጥ ፣ ራስን እየረገሙ ሌሎችን ማድነቅ ከሆነ ቢቀር ይሻላል ። በሰው አገር ላይ አገር እንደሌለን ሲንቁን ማየት ያስከፋን ይሆናል ። ከሁሉ በላይ ግን በሰማይ ስደተኛ መሆን ያስጨንቃል ። ለጌታችን ክብር ምስጋና ይድረሰውና ከቅዱሳን ጋር ባላገሮች ሁነናል ።

አዝማደ መንግሥት መሆን ቀላል አይደለም ። የንጉሡ ሚስት እቴጌ ወይም ቀዳማዊት እመቤት በአዋጅ የተፈቀደ ሥልጣን ባይኖራቸውም ባለሥልጣን ናቸው ። ልጆቻቸውም ልዑላንና ልዕልቶች ይባላሉ ። የንጉሡ ዘመዶችም አዝማደ መንግሥት ናቸውና ይከበራሉ ። እኛ ግን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ነን ። በዚህም ልባችን ሊመካ ይገባዋል ። የተፈቀደ ትምክሕት በእግዚአብሔር መመካት ነውና ። በምድር ላይ መጻተኞችና ስደተኞች ብንሆንም በሰማይ ግን ልጆች ነንና ወደ አባታችን ርስት እንገባለን ። ልጅ ወራሽ መሆኑ በሕሊናም ፣ በፍትሕ ሥጋዊም ወመንፈሳዊም የታወቀ ነው ። ልጅ ግን አባቱን መምሰሉ ግድ ነው ። የንጉሡ ልጅ አባቱን በሥልጣን ሳይሆን በመልክ ይመስላል ። በባሕርያዊ ልደት በመገኘቱም ልጅነቱ ሲያስከብረው ይኖራል ። እግዚአብሔርን መምሰል ሲባል አምላክ መሆን ማለት ሳይሆን እርሱ ቅዱስ ነውና ቅዱሳን መሆን ማለት ነው ።

ክብር ምስጋና ላዳነን ከኃጢአታችን በደሙ ላጠበን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ይሁን አሜን !

ያጋሩ