የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገፅ
ሰኞ ፣ መስከረም 26 / 2006 ዓም
ቁርሳችንን ጣፋጭ ያደረገው ባለ መዓዛው ኅብስት፣ የጥቅምቱ ማር፣ የሻዩ ቅመም ብቻ አይደለም፤ መግባባት የነበረበት ንግግር፣ ድንበር ያልነበረው የፍቅር ጨዋታችንም ምግቡን አጣፍጦት ነበር፡፡ የምግብ ጣዕሙ ፍቅር ነው፡፡ በሕይወቴ ሦስት ግብዣዎችን አስታውሳለሁ፡፡ ሦስት እህቶች በተለያየ ጊዜ፣ በተለያየ ቦታ፣ በየተራ የጋበዙኝ ሦስት ግብዣዎች ድቅን ይሉብኛል፡፡ ከተወለድኩ ጀምሮ የበላሁት ስንት ሰሐን ይሆን@ እነዚህ ሦስት ሰሐኖች ግን ይታወሱኛል፡፡ አንደኛው ሰሐን በታወቀ ክትፎ ቤት የተጋበዝኩት፣ አንደኛው ሰሐን እቤት ተጠርቼ የበላሁት ዶሮ፣ አንደኛው ሰሐን የገበታ ቅቤ እየተቀባ የበላሁት ልዩ ምግብ ነው፡፡ እነዚህ ውድና ጣፋጭ ምግቦች ግን ዛሬም በአፌ ላይ ይመሩኛል፡፡ እነዚህ ወገኖቼ እየጋበዙኝ አብረው ነገር አብልተውኛል፡፡ እስከ ዛሬ ሐሞት የበላሁ እየመሰለኝ ይዘገንነኛል፡፡ ክፉ ሰው እየጋበዘ ነገር ያበላል፡፡ ያለ ፍቅር ጮማ ከመቁረጥ በፍቅር ጥሬ መቆርጠም እንደሚሻል እኔ ምስክር ነኝ፡፡
የዛሬው ቁርስ ግን ከፍቅር ጋር ስለነበረ የዳቦው መዓዛ የማይገፋ፣ የማሩ ጣዕም የማያንገፈግፍ፣ የሻዩ ቅመም ልብ የማይመታ ነበር፡፡ ፍትፍቱን ከፊቱ ጋር የሚጋብዝ እውነተኛ አፍቃሪ ነው፡፡ የፍቅር ወጪው ትንሽ ነው፡፡ የቅንዓት፣ የምቀኝነት … ወጪው ግን ብዙ ነው፡፡
ገበታ ሳይነሣ መነሣት ነውር ቢሆንም ተንቀሳቃሽ ስልክ ከመጣ በኋላ ግን ሳይፈቀድ አልቀረም፡፡ የስልኩ ጥሪ እንደመጣ አብሮኝ የነበረውን ወንድሜን ትቼ ተነሣሁ፡፡ ወደ ግራ ገባሁና ወጥቼ ወደ ሌላ ክፍል ስሄድ ያ እንዳስቀመጥኩት እርግጠኛ የነበርኩበት ወንድሜ ለካ ተነሥቷል፡፡ ከኋላዬ ነው ብዬ ተማምኜ ወደፊት ገሰገስኩ፡፡ ልገባበት ካሰብኩት ክፍል ድንገት ብቅ ሲል ክው አልኩኝ፡፡ ሰውነቴ በቅጽበት ከግራ ወደ ቀኝ ነዘረኝ፡፡ ሰዓቱ ጨለማ አይደለም፣ ከረፋዱ አራት ሰዓት ነው፡፡ ሌላ ሰው ይገባል ተብሎ አይሰጋም፣ በጽኑ የተቀጠረ ግቢ ነው፡፡ ማንም ሰው ገብቶ ይደበቃል የሚል ጥርጣሬ እንኳ የለኝም፡፡ እኔ ግን ደነገጥኩ፡፡ የማውቀውን ወይም የማላውቀውን ሰው በማየት ሳይሆን ባልጠበቅሁት ስፍራ ያልጠበቅሁትን ሰው በማየት ደነገጥኩ፡፡ የማላውቀው ሰው ቢሆን ምን ሊሠራ መጣ፣ ሌባ ነው ብዬ ድንጋጤዬ ወደ ዘራፍ ይለወጥ ነበር፡፡ የማውቀው ያውም ወዳጄ በመሆኑ ግን ደንግጩ እንዳልደነገጠ ለማስመሰል፣ ድንጋጤዬን አፍኜ ለብቻዬ ለመሆን ፈጠንኩ፡፡
ገበታ ሳይነሣ መነሣት ነውር ቢሆንም ተንቀሳቃሽ ስልክ ከመጣ በኋላ ግን ሳይፈቀድ አልቀረም፡፡ የስልኩ ጥሪ እንደመጣ አብሮኝ የነበረውን ወንድሜን ትቼ ተነሣሁ፡፡ ወደ ግራ ገባሁና ወጥቼ ወደ ሌላ ክፍል ስሄድ ያ እንዳስቀመጥኩት እርግጠኛ የነበርኩበት ወንድሜ ለካ ተነሥቷል፡፡ ከኋላዬ ነው ብዬ ተማምኜ ወደፊት ገሰገስኩ፡፡ ልገባበት ካሰብኩት ክፍል ድንገት ብቅ ሲል ክው አልኩኝ፡፡ ሰውነቴ በቅጽበት ከግራ ወደ ቀኝ ነዘረኝ፡፡ ሰዓቱ ጨለማ አይደለም፣ ከረፋዱ አራት ሰዓት ነው፡፡ ሌላ ሰው ይገባል ተብሎ አይሰጋም፣ በጽኑ የተቀጠረ ግቢ ነው፡፡ ማንም ሰው ገብቶ ይደበቃል የሚል ጥርጣሬ እንኳ የለኝም፡፡ እኔ ግን ደነገጥኩ፡፡ የማውቀውን ወይም የማላውቀውን ሰው በማየት ሳይሆን ባልጠበቅሁት ስፍራ ያልጠበቅሁትን ሰው በማየት ደነገጥኩ፡፡ የማላውቀው ሰው ቢሆን ምን ሊሠራ መጣ፣ ሌባ ነው ብዬ ድንጋጤዬ ወደ ዘራፍ ይለወጥ ነበር፡፡ የማውቀው ያውም ወዳጄ በመሆኑ ግን ደንግጩ እንዳልደነገጠ ለማስመሰል፣ ድንጋጤዬን አፍኜ ለብቻዬ ለመሆን ፈጠንኩ፡፡
እንዳስቀመጥኩት እርግጠኛ የነበረው ሰው ተነሥቷል፡፡ ከኋላዬ ያለ የሚመስለኝ ሰው ተግባሩን አከናውኖ እየተመለሰ ነው፡፡ ከጀርባዬ ነው የምለው ፊቱን አዙሮ ወደ እኔ እየመጣ ነው፡፡ ተማምኜ እያወራሁ ለምሄደው፣ ፀጥታ ያለበት ክፍል ለምሻው፣ ማንም ሰው በዚያ የለም ለምለው ለእኔ ለአላዋቂው ያስደነግጣል፡፡ እርሱ አላጠፋም፣ እኔም አልበደልኩኝም፡፡ ነገር ግን መብረቅ የወረደ ያህል ደነገጥኩኝ፡፡ በመደንገጤ ደነገጠ፡፡ ድምፅ ሳያሰማ በማለፉ፣ በሩን ገርበብ አድርጎ ድንገት በመክፈቱ… ሊሆን ይችላል፡፡ እኔስ ምን ሆኛለሁ ያስቀመጥኩት ሰው ይነሣል፣ ያስቀመጥኩት የሻይ ሲኒ ግን አይነሣም፡፡ አይ ለራሴም ማዘን አለብኝ፡፡ ለራሴ ድምፅ ልሰጥ፣ ራሴን ልክ ነህ ልበለው፡፡ መደንገጥህ ትክክል ነው፣ ራሴ ሆይ ያስቀመጥከው ሰው በመነሣቱ፣ ኮቴውን ሳያሰማ በማለፉ፣ ከፍቶ ሳይሆን ገርበብ አድርጎ ተግባሩን በመፈጸሙ፣ የምትከፍተውን በር እርሱ ከፍቶ ብቅ በማለቱ፣ ከኋላ ስትጠብቀው ከፊት ድቅን በማለቱ መደንገጥህ እውነትህን ነው፡፡ የሚያስነቅፍህ መደንገጥህ ሳይሆን ደንግጠህ መቅረትህ፣ እንደ ዳዊት ከድንጋጤህ የተነሣ ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ነው ማለትህ ነው (መዝ. 115÷2)፡፡
ፊቱን ጥቁር፣ አንገቱን ስግግ አድርጎ በመድረሴ ሊለቅልኝ ቅልጥፍ ብሎ እየወጣ ያለው ያ ወንድሜ በመደንገጤ፡- “አይዞህ በስመ አብ…” አለ፡፡ እኔም እንዳልደነገጠ “እሺ” ብዬ የውሸት ፈገግታ ፈገግ ብዬ አለፍኩ፡፡ ሥጋዬ ግን እንዲህ ተማትቶ ተመልሶ አያውቅም፡፡ እንደ መሬት መንቀጥቀጥ ነዝሮ ተመለሰ፡፡ የስልኩ ወሬ አለቀ፡፡ ያላሰብኩትን መሥራት ጀመርኩ፡፡ ድንጋጤ ካላሰቡት ያውላል፡፡ እንደ ወትሮው ልቤን አዳመጥሁ፡፡ ልቤ ደህና ነው፡፡ በሕይወት ውስጥ ሥጋ ይርዳል ውስጥን ሲያዳምጡት ግን ሰላም የሚሆንበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ፊቴን በመስተዋት አየሁ፡፡ ውሃውን ከፍቼ ታጠብሁ፡፡ ውሃው እስኪደርቅ ልቤ፡- “ድንጋጤ ባልጠበቁት ስፍራ የማያውቁትን ሰው ማየት ሳይሆን ባልጠበቁት ስፍራ የሚያውቁትን ሰው ማየት ነው” አለ፡፡ አዎ በቺካጎ አንድ ነጭን ማየት አያስደነግጥም፡፡ እርሱ በእኛ ለመደንገጥ ግን ምክንያት አለው፡፡ በቺካጎ እኛ ያሳደጉንን ጎረቤታችንን ወ/ሮ ማንጠግቦሽን ማየት ግን ያስደነግጣል፡፡ ከዚህ ሀሉ በላይ የድሮ ደርባባነታቸውን ጥለው የወጣቶችን አጭር ቀሚስ ለብሰው ከፈረንጆች ጋር ሲደንሱ ማየት ጭንቅላት ያዞራል፡፡
“በእኔ ይብቃ” ማለት የኤድስ በሽተኞች ለወገናቸው የሚራሩበት ድምፅ ወይም ዘመናዊ ቋንቋ ይመስለን ይሆናል፡፡ “በእኔ የደረሰ በእናንተ አይድረስ” የሚለው ምርቃት ግን ጥንታዊ የአገራችን ዕንባ ያዘለ ምርቃት ነው፡፡ ምርቃት ሁሉ የተስፋ ቸርነት ነውና ፊትን አፍክቶ፣ ልብን ሞልቶ፣ አምላክ አለኝ ይሰጥሃል ብሎ በመተማመን የሚያፈስሱት ነው፡፡ “በእኔ የደረሰ በእናንተ አይድረስ” የሚለው መራቂ ግን በዓይኑና በልቡ የሚያለቅስ፣ ብዙ ነገሮች ያጨለሙት ነው፡፡ ይህ ምርቃቱ የታላቅ ስብራት መግለጫ ቋንቋም ነው፡፡ ከከረመበት ሥራ በጉን እየጎተተ ሲመለስ ልጆቹና ሚስቱ በጠላት የተገደሉበት አባወራ የመጨረሻው ቃሉ፡- “በእኔ የደረሰ፣ በእናንተ አይድረስ” የሚል ነው፡፡ የገዛ ባሏ የገዛ ልጁንና ልጇን የገደለባት ባልቴት የመጨረሻው ቃሏ፡- “በእኔ የደረሰ፣ በእናንተ አይድረስ” የሚል ነው፡፡ ብድር ለመቀበል ወደ ቀበሌ የሄደው ነጋዴ ሲመለስ ሱቁ ሁሉ ተቃጥሎ ሲያገኘው የመጨረሻ ቋንቋው፡- “በእኔ የደረሰ በእናንተ አይድረስ” የሚል ነው፡፡ ደቀ መዝሙሩ ያሳደደው መምህር የመጨረሻው ቃሉ፡- “በእኔ የደረሰ፣ በእናንተ አይድረስ” የሚል ነው፡፡ ወዳጁ ጠላት፣ አውቀዋለሁ የሚለው ወንድሙ የሚያውቀው የሆነበት፣ በወዳጅ ቤት ቁስል የሚማቅቀው ወገን የመጨረሻው ቃሉ፡- “በእኔ የደረሰ፣ በእናንተ አይድረስ” የሚል ነው፡፡ ከቋንቋ በላይ የሆኑ፣ ከመናገርም የሚያልፉ፣ ከዕንባም አስረጂነት በላይ የሆኑ ነገሮች የሚገለጹበት መግለጫው ይህ ነው፡፡ ባልጠበቁት ስፍራ የሚያውቁትን ሰው ማግኘትም ለደረሰበት ሁሉ፡- “በእኔ የደረሰ በእናንተ አይድረስ” የሚያሰኝ ነው፡፡
እያበሉ የሚበሉ፣ እየሳሙ የሚነክሱ፣ እንደ አመንዝራ ባማረ ጥርሳቸው ልብን የሚያቀልጡ፣ እጃቸው እንጂ ልባቸው የማይጨበጥ፣ ከምግብ ጋር ነገር የሚያጎርሱ፣ ባልተመቸ ቀን እንደ ድመት እግር የሚያሹ በተመቻቸው ቀን እንደ ነብር ደም መጠው የሚገድሉ፣ ከእኛ ጋር እየዋሉ ከጠላት ጋር የሚያድሩ፣ ያወቅናቸው የመሰለን ገና የማናውቃቸው፣ ተጠንተው የማያልቁ፣ እንደ አዳኝ ኮቴአቸው የማይሰማ፣ በሽንገላቸው ዐውረውን እነርሱ የሚያዩን እኛ የማናያቸው፣ ደግነታችንን እንደ ሞኝነት፣ ፍቅራችንን እንደ ጊዜ ማሳለፊያ የሚቆጥሩ፣ እኛን የማይወዱ ገንዘባችንን የሚያፈቅሩ፣ እየጠሉን ለሚወዱን ለእኛ ሰላምታ የሚልኩ፣ ከእኔ ጋር ናቸው እያልን ስንፎክርባቸው ከራሳቸውና ከጠላቶቻችን ጋር የሆኑ፣ ተቀምጠዋል ተረጋግተዋል ስንላቸው የተነሡ፣ ሳናያቸው የሚቀመጡ ስናያቸው የሚበረብሩ፣ እየተከተሉኝ ነው ከኋላዬ አሉ እያልን ለራሳችን ስንነግረው ከፊት ለፊታችን ጦር ይዘው የሚመጡ፣ እየጸለይን ነው እያሉ በር ዘግተው አድማ የሚያስመቱብን፣ ተንኮላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ክዳታቸውን ወደ ተሻለ ነገር ማደግ በማለት የዳቦ ሰም የሚሰጡ፣ ራስን የማየት ፕሮግራም ብለው ሰው ሲያሙ የሚውሉ፣ ርኩስ መባልን የሚፈሩ ርኩስ የሆኑ፣ የቅብ ኑሮ ባይኖር ለአንድ ደቂቃ አብረዋቸው ለመሆን የሚከብዱ እነዚያ ሰዎች የኑሮ ፈተናዎቻችን ናቸው፡፡ ዛሬ ስናውቃቸው ደነገጥን፣ እነርሱ ግን ድሮም እንደዚህ ነበሩና በድንጋጤአችን ይስቁብናል፡፡ እኛ ከዚህ ጠባያቸው ጋር ይቅር ብለን ለመኖር እንፈልጋለን፡፡ እነርሱ ግን በማያውቋቸው አገር እንደ ጅብ ቁርበት አንጥፉልኝ ለማለት ገና ይሄዳሉ፡፡ ወይ ጉድ “ደንቆሮ የሰማ ቀን ያብዳል” የምንባለው ለካ እኛ ነን!
ታሪኩ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የተፈጸመ ነው፡፡ ሰውዬው መልኩ ያማረ፣ አሰጣጡም ያማረ ለገንዘብ የማይሳሳ ቸር መሆኑን ያየችው እናት ልጇን ዳረችለት፡፡ ሠርጉ በልዩ አልፎ ሙሽሮቹ ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡ ለካ ያ ሰው በቂ እግር የሌለው በሽተኛ መሆኑን ሙሽሪት ያወቀችው ጫማውን ሲያወልቅ ነው፡፡ “እህ” እያለች መተንፈስ፣ ማማጥ ጀመረች፡፡ በዚህ ጊዜ ሙሽራው ገባውና “እቱ እህ ትበል እናትሽ ብሬን አይታ የዳረችሽ” አላት ይባላል፡፡ እኛ ዐይተናቸው ያጨናቸው፣ ሰዎች ዐይተው ያጩልን እግራቸው ግን በሽተኛ የሆነ፣ ሲሄዱ የሚኖሩ፣ ጎድተውን የሚሄዱ ብዙዎች ናቸው፡፡
ከፍቅር ጋር ትንሹ ብዙ፣ ያረረው ጣዕም ያለው መሆኑን ልናውቅ ይገባል፡፡ ፈገግታ ያለው ፊት ሁሉ የፍቅር መግለጫ አይደለም፡፡ ረቂቅ ሌቦች፣ የዝሙት አዳሪዎች የተካኑት ጥበብ ነው፡፡ ይህን ግን በክርስቲያኖች ላይ እያየነው ነውና ማልቀስ ይገባናል፡፡ ነቢዩ ዳዊት፡- “የደም ሰዎችና ሽንጋዮች ዘመናቸው ግማሽ አይሞላም፤ እኔ ግን$ አቤቱ$ እታመንሃለሁ” (መዝ.54(55)$23) ያለውን ስናስብ ለሸንጋዮች ማልቀስ ይገባናል፡፡ የሚሸነግሉት ረጅም ዘመን ለመኖር ብለው ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ዕድሜአቸውን ይቆርጠዋል፡፡ የሰው ዕድሜ ቢበዛ ሰማንያ ነው ተብሏልና የዘመን ግማሽ ዐርባ ዓመት ነው፡፡ በእውነት ብዙ ሸንጋዮችን ባየሁ ጊዜ ልቤ ያለቅሳል፡፡ እንደማይኖሩ በሕይወቴም ዐይቻለሁ፡፡
የተከልናቸው የሚመስሉን፣ ስንመለስ ግን የተነቀሉ፣ የጽድቅ ዛፎች ሳይሆኑ የስሜት አረሞች የሆኑ፣ ተከልኩ አጠጣሁ ያልንላቸው ነገር ግን ኮምጣጤ ያፈሩ፣ ከሩቅ ስናያቸው ለእርዳታ የመጡ እየመሰለን ደስ ደስ ሲለን ጦር መርተውብን የመጡ፣ አሳሳማቸው ያልተለወጠ ነገር ግን ከመታመን ወደ መሸጥ ራሳቸውን ያወረዱ ገጥመውን ይሆናል፡፡ በእነዚህ ሰዎች ብዙ ጊዜ ደንግጠናል፡፡ ከድንጋጤ የሚብሰው ድንጋጤ ዐርፈዋል ያልናቸው እንደገና ሲቅበዘበዙ፣ ገብተው የማያልቁ፣ ተፈልገው የማይገኙ፣ ተጨብጠው የሚተኑ፣ ደቀ መዝሙር ስንላቸው ደቀ ሰይጣን የሆኑ፣ አርአያነታችንን ይዘዋል ልክ እንደ እኛ ናቸው ስንላቸው ልክ እንደ ጠላቶቻችን የሆኑ፣ ገና እየመጡ ነው ስንል ግቡን ነክቼው ሐሰት መሆኑን ተረዳው እያሉ አፍጥጠው ሲገናኙን፣ ልጅ ናቸው ብለን ስንቀጣቸው ገልብጠው የጣሉን፣ ለፀጥታ የመደብነውን ጊዜ በወዳጅ ጦራቸው ሲያውኩብን፣ በሹክሹክታ ሲያማክሩን ኖረው ርቀው ያሙን፣ ሁሉን እሺ ያልናቸው ስህተትን ሳይቀር ያስወሰኑን ዛሬ እንደሌሉበት አምባገነን ናቸው ብለው ሲከሱን፣ ሊቅ ያልናቸው ሊጥ ሲሆኑብን፣ ቤቱን አደራ ብለናቸው ሄደን አሳድመው የቆዩን፣ … አዎ እነዚያን ሰዎች ማሰብ ሰውነትን ያርዳል፡፡ ከድርጊታቸው ይልቅ አለመጠበቃችን ይጎዳናል፡፡ እነርሱም ደፋሮች፣ ለጥፋታቸውም ካሣ ከፋይ መሳዮች ናቸው፡፡ በክፋታቸው ጥለውን ከበው ነፋስ እንድናገኝ ያራግቡልናል፡፡ ስንነቃ ጥለውን ይሄዳሉ፡፡ ታግሠናቸው የኖሩ ቢሆኑም ታግሼ ታግሼ ስለቸኝ ብለው ሲያማርሩን እንሰማለን፡፡ አዎ የጨረስን የመሰለን ነገር ግን ገና ያልጀመርነው ቢሆንም፣ የሰው ሕንፃ አለቀ ሲሉት የሚመሠረት ቢመስልም እግዚአብሔር ግን ትልቅ ነው፡፡
ሰው በብርሃን የሚጨልምበት፣ በረፋዱ የመሸ የሚመስለው፣ ወዳጁን በማይጠብቀው አመለካከት፣ በማይጠብቃቸው ሰዎች መካከል፣ በማይጠብቀው ስፍራ ሲያየው ነው፡፡ አጥራችን ሌባን ሲመልስ ኖሯል፡፡ አስመሳዮችን ግን አጥር አይመልሳቸውም፡፡ የሰፈር ዱርዬዎች ግቢያችን ገብተው አያውቁም፡፡ ዘመናዊ የሚመስሉ ዓለም አቀፍ ዱርዬዎች ግን ማረፊያችን ድረስ ገብተዋል፡፡ ሲጋራ የሚያጨሱ፣ ጫት የሚቅሙ ዱርዬዎችን ተከላክለናል፡፡ ሰውን የሚያጨሱ፣ ወዳጅን የሚቅሙ ዱርዬዎችን ግን መከላከል አልቻልንም፡፡ ለእነዚህ ሽፍቶች ዘበኛ አይጠራም፡፡ የሚባለው ይሁዳንና ጴጥሮስን ይቅር ያለውን ጌታ ድረስልኝ ብቻ ነው፡፡
ይሁዳ ጦር እየመራ የመጣው የጎረሰው ከጉሮሮው ገና ሳይወርድ ነው፡፡ ወዳጅነት ሳያልቅ ጠላትነት መጀመሩ ያሳዝናል፡፡ ጴጥሮስ ከጠላቶች ጋር የጨዋታ እሳት መሞቅ ጀመረ፡፡ ከይሁዳ በላይ በማይጠበቅበት ቦታ የተገኘው ጴጥሮስ ይገርማል፡፡ ሰውን እያወቁት አለማወቅ ምንኛ ከባድ ይሆን! እንዲህ ያለውን ጉድ ለማውራት አይቀልም፡፡ ስለነዚህ ሰዎች ብዙ የመከሩን፣ ተዉ ያሉን ብዙዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እኛ ግን ጠሉብኝ ብለን ይበልጥ እፍ ብለን ይሆናል፡፡ የተባለው ሁሉ ሲደርስ ግን አውቃቸዋለሁ ያለው አንደበታችን መናገር ያቅተዋል፡፡ አዝኖ እንዳላዘነ መሆን ይገጥመናል፡፡ ሰው ላይሆኑን ሰው ያሳጡንን እነዚያን ከዳተኞች ለመራገም እንዳዳለን፡፡ ነገር ግን ፍርዱ ለእግዚአብሔር መሆኑን ልናስብ ይገባናል፡፡
ሰውን ከርሞ በስፍራው ማግኘት ከባድ ነው! እስከ ዛሬ የወደድናቸው የሙከራ ጊዜ ነው፡፡ ሁሉን ዐይተው ሲመለሱ ግን ዘላቂ ወዳጆቻችን ይሆናሉና በሩን ከፍቶ መሸኘት ያስፈልጋል፡፡
አዎ ከጀርባ የነበረ ሰው ከፊት ሆኖ ፍልስፍናውን ሲያወርድብን፣ አንቀጽ እየጠቀሰ ሲከሰን፣ በጠላቶች ፊት መረጃ አለኝ እያለ ሲያሳጣን ማየት ቀጥሎ ባንሰቀልም የመሰቀልን ያህል ይጐዳል፡፡ ነገር ግን ለጊዜው እንጂ እስከ መጨረሻው መደንገጥ አይገባም፡፡
ትዕግሥተኛው በድንገት ቁጠኛ፣ አፍቃሪው ቂመኛ የሚሆነው በዚህ ድንጋጤ ነው፡፡ ይህ ከዳተኛ የበጋ መብረቅ ነው፡፡ የበቃ መብረቅ ስለማይጠብቁት፣ ስለማይጠነቀቁት ያስደነግጣል፣ ይጐዳል፡፡ የወዳጅ ጠላትም እንደዚሁ ነው፡፡ ልብ አድርጉ! የማይወድ አይጠላም፣ የማያፈቅር አይቀየምም፡፡ ማዘናችን ስለምንወዳቸው ነው፡፡ የደረሰብንን ነገር ስናስብ ብስጭቱ ለሥጋ በሽታ፣ ሀዘኑ ለአእምሮ በሽታ አሳልፎ ያልሰጠን በእኛና በጉዳቱ መካከል ጣልቃ መድኃኒዓለም ጣልቃ ስለገባ ነው፡፡ እግዚአብሔር ያጽናናል፡፡ አዎ ድንጋጤ ባልጠበቁት ስፍራ የማያውቁትን ሰው ማየት ሳይሆን ባልጠበቁት ስፍራ የሚያውቁትን ሰው ማየት ነው፡፡
በእኔ የደረሰ በእናንተ አይድረስ ማለት ትልቅ ሀዘን፣ ትልቅ ምርቃት ከሆነ ካለፈው መማር፣ ሰውን ሰው ብቻ ማለትም ከእኛ የሚጠበቅ ነው፡፡ ጉዳታችን ሰውን መልአክ ከማለት የመጣ ነውና፡፡ “ሰው ከአፈር የተሠራ፣ ቢያጥቡት የማይጠራ” የተባለውን ማሰብ ይገባናል፡፡ የድሮ ወዳጅ ዛሬ ባይኖር፣ ቀድሞ የሚያውቁን ዛሬ ቢታጡ፣ ስለ እኛ እውነቱን የሚናገር ቢጠፋ የጥንቱ ወዳጅ፣ በማኅፀን ውስጥ ሳለን የተወዳጀን እግዚአብሔር አለን፡፡ በትላንት ማንከሳችን ለምንድነው@ በቅድሙ መተከዛችን ሞኝነት ነው፡፡ የኋላችንን እየረሳን ወደፊት መዘርጋት የክርስትናው ጥሪ ነው (ፊልጵ. 3$13)፡፡
በዓለም ላይ ከባዱ ሰውን አውቀዋለሁ ማለት ነው፡፡ ቃሉ፡- “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል@” ቢልም እኛ ግን አውቀዋለሁ እያልን አስቸግረናል (ኤር. 17$9)፡፡ ስለዚህ ችግሩ ያለው ቃሉን ከማናስተውለው ከእኛ እንጂ ከሰዎቹ አይደለም፡፡
እህ ማለት ያለበት የፈርምንለት ሳይሆን ላዩን ዐይተን የመረጥነው እኛ ነን፡፡ እህ ማለት ያለበት ራሳችንን የሰጠነው እግረ በሽተኛው ሳይሆን በስሜት ያበድነው እኛ ነን፡፡ አዎ የመቀበልን ፍቅር አግኝተን ከሆነ ይቅርታ የሚያደርገው ፍቅር ደግሞ ያስፈልገናልና ከጌታ ዘንድ እንለምን፡፡ ሰዎቹ በአካል አብረውን ላይኖሩ ይችላሉ፡፡ አካላቸው ሄዶ ቂማቸው ቀርቶብን ከሆነ ይቅርታን መለማመድ አለብን፡፡
ምናልባት ለዓይናችን ካየናቸው ረጅም ጊዜ ሆኖን ለዓይነ ሥጋ አብቃን እያልን ሱባዔ ገብተን ያገኘናቸው ወዳጆቻችን ዓይን በሚያፈስ ተንኰል መጥተውብን ይሆናል፡፡ ስለ እነዚህ ወዳጆች ስንቃትት ያዩን፡- “አህያ ተማልላ ጅብ አወረደች” እያሉን ይሆናል፡፡ የቅን ፈራጅ ግን በሰማይ ተቀምጧል፡፡
በቀጣይ ዘመናችን ያቀድነውን ትልቅ ዕቅድ በስማቸው ለመሰየም ያጨናቸው የእኛ ትልቆች፣ የሙያችንን መታሰቢያ ልንሰጣቸው የመረጥናቸው የእኛ ውዶች፣ ብናልፍም ስማችንን ያስጠሩታል ያልናቸው የእኛ ወራሾች ከሰቃዮቻችን ጋር ቁጭ ብለው እሳት እየሞቁ፣ በእኛ ላይ የሚፈረደውን ክፉ ፍርድ እያፀደቁ ይሆናል፡፡ በማይጠበቅ ስፍራ ወዳጅን ማየት ይከብዳል፡፡
አዎ እግዚአብሔር ከዚህ ሁሉ ደግነት ከዚህ ሁሉ ንፉግነት፣ ከዚህ ሁሉ ወዳጅነት ከዚህ ሁሉ ከዳተኝነት በላይ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህንንም ዐይቷልና ደስ ይበላችሁ!