የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ባሕር ተከፈለ

ቍጥር የሌለው ኃጢአታችንን ቍጥር በሌለው ፍቅርህ ደምስሰህ ይኸው ባሕር ተከፈለ ። መውለድ መሐን መሆን ሁለቱም ሲያስፈራን ፣ ፍቅር ጥላቻ ሁለቱም ሲያውከን ፣ የምንመርጠውን ለማናውቅ ለእኛ ባሕር ተከፈለ ። ገነትን አጥተን ግዞት ለወረድነው ፣ ንገሡ ብንባል በሌብነት ቅጠል ሥር ለተሸሸግነው ፣ ልጆቻችን ሲጋደሉ ላየነው ፣ ሞትን በልጅ ለጀመርነው ለእኛ ለትኩዛን ደስ ይበለን ባሕር ተከፈለ ።

ውኃ ተሸክመን ፣ ውኃ ሆነን ውኃ ለምንፈራ ፣ በውኃ ጅራፍ ልክ የሌለው መከራ ለደረሰብን ፣ ሞገድ የማይቀርበው መርከብ ኢየሱስ ክርስቶስ ፣ ልብሱን ውኃ እንዳይነካው ዕርቃኑን ተሰቅሎ ባሕር ከፈለልን ። በእውነት ደስ ይበለን ። የባለጠጋው አብ ልጅ ፣ ባለጠጋው ኢየሱስ ድሀ መሆን ምን ያስቀናዋል ! ብርዝና ጠጁ ሳለ ሀብታም ሁሉ በድሀ እየቀና ውኃ ፣ ውኃ አለ ። ድሀ የያዘው ሁሉ ሀብታም ያስቀናዋል ። ድሀ መሬት ሲተኛ ፣ መሬት መተኛት ለጤና ጥሩ ነው እያለ ሀብታም በድሀ ቀና ። ባለጠጋው ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ከድሀ ቤት ማደርህ ፣ እንደ ድሀ መኖርህ ፣ በአንዲት ጨርቅ ዕድሜ ልክህን መታየትህ ፣ ምንም እንደሌለው ዕርቃንህን መሰቀልህ ፣ መሬት ላይ ለሦስት ቀን መተኛትህ ፣ ስለ እኛ ብትቀና ነውና ድሀ ሆነህ ባለጠጋ ያደረግኸን የሰማይና የምድር ውበት ፣ የቁንጅና ዳርቻ አማኑኤል ተመስገን ።

ባሕር ተከፈለ ሰዎች እልል በሉ ። በባሕር ላይ መሻገር ሳይሆን በተከፈለ ባሕር ውስጥ ማለፍ ለእኛ ሆነ ። በባሕር ላይ መሻገር ብልጠት ፣ በባሕር ውስጥ ማለፍ የእምነት ኃይል ነው ። የትላንት ገዥ ፣ የጣለኝ ድጥ መልሶ ሊይዘኝ ፣ ወጣሁ ስል ሲያስቀረኝ እየገሰገሰ ነው ። ትላንትናዬ ነገ ላይ ተሻግሮ መንገድ ሊዘጋብኝ ነው ። የትላንት ታሪክ ፣ የዛሬ ሕይወት ፣ የነገ ተስፋ የሌለኝ ሊያደርገኝ ነው ። ምስጋና ለአማናዊው ሙሴ ይሁን ባሕር ተከፈለ ። በእምነት የተሻገሩትን ፣ የሚሞክሩ የተዋጡበት የቀይ ባሕር ምሥጢር ድንቅ ነው ። እምነት ያሻግራል ፣ ሙከራ ያሰጥማል።

ባሕር ተከፈለ በአማናዊው ሙሴ በክርስቶስ ሞት የጀርባ ታሪክ ሆነ ። ልጆቻችንን የበላ ፣ በውዶቻችን ደም ጡብ የሠራ ፣ ኖረንለት የገደለን ፈርዖን ዲያብሎስ ድል ተነሣ ። ላንገናኝ ከሰይጣን ተለያየን ። በሕልማችን እንዳያውከን የፈርዖን ሬሳ በቀይ ባሕር ታየን ። እባቡ እንዳያስደነግጠን ራሱ ተቀጠቀጠልን ። በደምመላሽ ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በጠላት ራስ ላይ ቆመን ዘመርን ። የወይራው ቀንበጥ መንፈስ ቅዱስ መዳናችንን አረጋገጠልን ። እውነትን በእውነት ተቀበልን ። መንፈሱ ለመንፈሳችን መሰከረልን ። ስለነገሩን ሳይሆን ስለተሰማን በእውነት በእርሱ ዐረፍን ። ባሕር ተከፈለ ሰዎች ደስ ይበለን !!!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም.

ያጋሩ

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።