የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ባንተ በመደነቅ

ጥበብህ ከሰማይ ከዋክብት ይበዛል ፣ እውቀትህ ከጸዳል ይደምቃል ። የእኔ መድኃኔዓለም ሥራህ በእውነት ይደንቃል ! አንተ ኃያል ሆይ የልቤን ልንገርህ ። አብረውኝ ገበታ የቆረሱ ሥጋና ደምህን አብረውኝ ካልተካፈሉ ፣ ጎረቤቶቼን ከመንግሥትህ ካጣኋቸው ፣ ዘመዶቼ በአርያም ባዳ ከሆኑኝ ፣ ለጊዜው አብረውኝ የነበሩ ለዘላለም ከተለዩኝ ፣ ልጆቼን ከብርሃን አዳራሽ ካጠገቤ ሳጣቸው ጌታ ሆይ ምንኛ ከባድ ነው ! እባክህ እኔ ለወንጌልህ እተጋለሁ ፣ አንተ በጸጋህ አግዛቸው ።

ሲታሰሩ አዝኜ የጠየቅኋቸው ወገኖቼ በሱስ ቀንበር ሲያዙ ጨክኜ ፈረድሁባቸው ። ሲታመሙ ብርቱካን ይዤ የጠየቅኋቸው በኃጢአት ጦር ራሳቸውን ሲወጉ ስማቸውን አጠፋሁባቸው ። አቤቱ ጌታዬ ለሥጋ ሕመምተኞች እንዳዘንሁ ለነፍስ ታማሚዎች እንድራራ እርዳኝ ። በእኔ መራራነት ያንተን ጣዕም ስለሸፈንሁ ፣ በእኔ ትዕግሥት ማጣት ሰዎች እንዳይሰሙ ስላደረግሁ ይቅር በለኝ ። በአንተ ስም እኔነቴን ስለ ሰበክሁ ፣ “ክብሩ ለእግዚአብሔር ይሁንና” እያልሁ የእኔን ጀብዱ ስላወራሁ ይቅር በለኝ ። የተፈጥሮ ችሎታዬን ፣ የአማኝነት መክሊቴን ፣ የጉብዝና ጉልበቴን ለዓለም እንጂ ላንተ ስላልሰጠሁ ይቅር በለኝ ። ክህደት ዛሬ የጀመረ መስሎኝ ብደነቅም ሙሉ አገር የካደበትን የኤልያስን ዘመን አስታውሰኝ ። እውቅ ሰዎች ጆሮንና ዓይንን መያዛቸው ሲገርመኝ እነ ኤልዛቤልን አስታውሰኝ ። የቀጠለ እንጂ የጀመረ ግፍና ኃጢአት የለምና በአንተ በመደነቅ ቀኔን ባርክልኝ ። አሜን ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 7 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ