የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ብሥራተ ገብርኤል 2

 አርብ፣ ታኅሣሥ 27 2004 ዓ.ም.
ካለፈው የቀጠለ

ስድስተኛ ወር

መልአኩ ገብርኤል ከስድስት ወር በፊት የብሥራት ቃል ይዞ ወደ ይሁዳ ወደ ዘካርያስ ዘንድ ሄዶ ነበር፡፡ ለዘመናት ልጅ አጥተው የነበሩ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ በእርጅና ዘመናቸው ልጅ አገኙ፡፡ ይህ ልጅ በመልአኩ ብሥራት ከተፀነሰ ስድስት ወር ነው፡፡ ያ ጽንስ ዮሐንስ መጥምቅ ነበረ፡፡ ዮሐንስ የወላጆቹ የዘመናት ጸሎት መልስ ነበረ፣ የክርስቶስ ደግሞ መንገድ ጠራጊ ነበረ፡፡ ከንጉሡ ፊት መንገድ ጠራጊው ይሄዳል፣ ከንጉሥ ክርስቶስ በፊትም ሕዝቡን ለማዘጋጀት ዮሐንስ ወጥቷል፡፡ ዮሐንስ መጥምቅ ጌታችንን በሥጋ ልደት ስድስት ወር ይቀድመዋል፡፡
ዮሐንስና ጌታችን ተመሳሳይ የሚሆኑባቸው ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው በብሥራተ መልአክ መወለድ ነው፡፡ ያበሰረውም አንዱ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ ልደታቸው ተአምራዊ ነው፡፡ ዮሐንስ በመካንነትና በእርጅና ላይ የተወለደ ሲሆን ጌታችን ደግሞ ያለ ወንድ ዘር የተወለደ ነው፡፡ የሁለቱም የስብከታቸው መጀመሪያ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ የሚል ነው፡፡ በእነዚህ በሦስት ነገሮች ይመሳሰላሉ፡፡ የሚያለያያቸው ነገር ደግሞ ዮሐንስ ነቢይ ሲሆን ኢየሱስ ግን እምላክ ነው፡፡ ዮሐንስ በበረሐ ያገለገለ ሲሆን ኢየሱስ ግን በከተማ ያገለገለ ነው፡፡ ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ የሚያመለክት አገልግሎት ነበረው፣ ኢየሱስ ግን ፍጻሜው ነው፡፡

 

መታጨት
“… ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች. . .” ( ሉቃ. 1÷27)፡፡ ይህ በእግዚአብሔር ጥበብ የተከናወነ ነበር፡፡ አንዲት ሴት ያለ ወንድ ፀንሳ ብትገኝ እንደ ሕጉ አመንዝራ ናትና ተወግራ እንድትሞት ታዟል፡፡ ድንግል ማርያም ያለ ወንድ ዘር መጽነሷ ለሥጋዊ ጆሮ የሚቀበለው አይደለም፡፡ ስለዚህ ያንን የመዳን ጽንስ ለመጠበቅ እግዚአብሔር አረጋዊ ዮሴፍን እንደ መጋረጃ ተጠቀመበት፡፡ ለዮሴፍ መታጨቷ ለግርዶሽ እንጂ ለሥጋዊ ፍትወት አይደለም፡፡ ከወለደችም በኋላ ልጆችን ወልዳ ቢሆን ኖሮ ጌታ በመስቀል ላይ ሆኖ ለዮሐንስ አደራ አይሰጣትም ነበር (ዮሐ. 19፡26)፡፡ ከልጅ ደቀ መዝሙር አይቀርብምና፡፡ ጌታም የእናቴን ነገር ለወንድሞቼ አደራ ይል ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ስለሌለ ግን ዮሐንስ ወደ ቤቱ ይዟት ሄዷል፡፡ በትዳር ዓለም የኖረች ብትሆን ወደ ቤቷ ትሄድ ነበር፡፡ ይህ ትምህርት እስከ አራተኛው ክፍለ ዘመን እንዲህ ነበር፡፡ ከአራተኛው ክፍለ ዘመን  መጨረሻ ላይ የመጣ አስተሳሰብ ግን ድንግል ማርያም በድንግልና እንደኖረች የሚክድ ነው፡፡ የሐዋርያትን እግር ተክተው የተነሡት አባቶች ግን የድንግል ማርያም መታጨት የእግዚአብሔር ጥበብ መሆኑን፣ ጌታችንን ከወለደች በኋላም በድንግልና መኖሯን ተናግረዋል፡፡
የድንግሊቱም ስም
“የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ” (ሉቃ. 1÷27)፡፡ ድንግልና እንደ መጠሪያና መታወቂያ ሆኖ የተቀፀለው ለንጽሕት ድንግል ማርያም ነው፡፡ ከእርስዋ በቀር በድንግልና ፀንሳ የወለደች ሴት ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ አልተነሣችም፤ አትነሣምም፡፡ ጌታችን በድንግልና መጸነስ ያስፈለገው ለምንድነው ስንል፡- እርሱ በሰማይና በምድር አባቱ እግዚአብሔር አብ ብቻ ስለሆነ በምድር ላይ አባት አላስፈለገውም፡፡ ሁለተኛ የውርስ ኃጢአት ይሄድ የነበረው በወንድ ዘር በኩል ነው፡፡ ኢየሱስ እንበለ ዘርዐ ብእሲ (ያለ ወንድ ዘር) መወለዱ ከአዳም ኃጢአት ጋር ያልተባበረ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የአምላክነቱም ማስረጃ ነው፡፡
ማርያም የሚለው ስያሜ የመጣው ከሙሴ እህት ጀምሮ ነው፡፡ ማር ማለት በዕብራይስጡ መራራ ማለት ሲሆን ያም ወይም ዮም ማለት ደግሞ ዘመን ማለት ነው፡፡ ዘመነ መራራ ማለት ነው፡፡ ይኸውም በግብፅ አገር ሕፃን ሲወለድ እየታነቀ ይገደል ነበርና የሙሴ እህት ስትወለድ የዘመኑን መራራ ሀዘን ለመግለጥ ማርያም አሏት፡፡
የሙሴ እህት ማርያም ባሕረ ኤርትራ ተከፍሎ ሲሻገሩ ከበሮዋን ነጥቃ ሰብሕዎ እያለች አመስግናለች፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፡- “ብሊት ማርያም የብሉይ ኪዳን ጥንት እንደሆነች ሐዳስ ማርያምም የሐዲስ ኪዳን ጥንት ናትና፤ አስቀድሞ በማርያም ዘመን የኾነው ግፍና መከራ ድንቅ ሥራ ሁሉ ኋላ በድንግል ማርያም ለሚሆነው አምሳል መርገፍ ሆኖ ተጥፏል፡፡ ማርያሞች እንዲነጻጸሩ ፈርዖንና ሄሮድስ፣ ሙሴና ክርስቶስ፣ ንሴብሖና ታዐብዮ ይነጻጸራሉ (ዘፀ. 15÷1-21፣ ሉቃ.1÷46-55)፡፡ ብሊት ማርያም በልደተ ሥጋ እኅተ ሙሴ እንደተባለች፣ ሐዳስ ማርያምም ለሥግው ቃል ልጇ በልደተ ነፍስ እኅት ትባላለች፡፡ ማስተባበር ልማዷ እንጂ ነው፤ ድንግልናን ከወሊድ እንዳስተባበረች፣ እኅትነትንም ከናትነት አስተባብራለች፤ በሰንበት ላይ ደብረ ዘይት እንዲሉ” (ኪዳነ ወልድ ከፍሌ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ገጽ 610)፡፡
ታላቁ ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሁለቱን ማርያሞች አነጻጽረዋል፡፡ የሚያመሳስል ነገር እንዳላቸውም በግልጽ ይታያል፡፡ ይኽውም፡- በፈርዖን ዘመን ሕፃናት አልቀዋል፤ በሄሮድስ ዘመንም ሕጻናት አልቀዋል፡፡ ባሕረ ኤርትራ ሲከፈል የመጀመሪያዋ አመስጋኝ የሙሴ እኅት ማርያም እንደነበረች፤ ባሕረ ሞትም ሲከፈል የመጀመሪያዋ አመስጋኝ ድንግል ማርያም ናት፡፡
ብሥራት
“መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ፡- ደስ ይበልሽ÷ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ÷ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት” (ሉቃ. 1÷28)፡፡
ድንግል ማርያም ዓለምን ሁሉ ወክላ የብሥራቱን ቃል ተቀበለች፡፡ ታላቅ እንግዳ ወደ ዓለም በሥጋ እንደ መጣ የምታውቀው እርስዋ ብቻ ናት፡፡ የዛሬዎቹን ምእመናን፣ የዛሬዎቹን አብያተ ክርስቲያናት ወክላ ክርስቶስን አስተናግዳለች፡፡ ዓለም እንደ ዳነ የሰማችው የመጀመሪያይቱ  ተሰባኪ ድንግል ማርያም ናት፡፡ የመጀመሪያዋ የወንጌል ሰባኪ የክርስቶስን አዳኝነት የተረከችም ድንግል ማርያም ናት (ሉቃ. 1÷47)፡፡ ሞት ወደዚህ ዓለም የገባው በሴት በርነት ነው፡፡ ይህም የሴት ዓለምን ያሸማቀቀ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ይህን ውርደት አነሣ፡፡ ሕይወት በሴት በኩል መጣ፡፡ እኛ ሁላችን በአባት ዘር መምጣታችን፣ በአባት ስም መጠራታችን ያኰራን ይሆናል፡፡ ኢየሱስ ግን የሴት ዘር ነው፡፡ የሴት ልጅ የሚለውም ስድብ ሳይሆን ማዕረግ ሆኗል፡፡
የልጅ ብሥራት ደስታ የሚሆነው ልጅ ተርበው ለኖሩ ለእነ ኤልሳቤጥ ነው፡፡ ለአንዲት ወጣት ድንግል እንዲሁም ድንግልናን ለመረጠች ሴት ልጅ ብሥራት ላይሆን ይችላል፡፡ የኢየሱስ መወለድ ግን የልጅ መወለድ ብቻ ሳይሆን የአዳኝም መወለድ ነው፡፡ የኢየሱስ መወለድ የቤትን ጭጋግ የሚገፍ ልጅ ሳይሆን የዓለሙን ጨለማ የሚያበራ ልጅ ነበረ፡፡ የእርሱ ልደትም የሕፃን ልጅ ልደት ብቻ አልነበረም፤ የሰላም መወለድ፣ የፍቅር መወለድ ነበር፡፡ የተወለደው አዳኝ ነው፡፡ በድንግል ማኅፀን ያደረው ዓለም የማይችለው ነው፡፡ በክንዷ የታቀፈችው ዓለሙን የተሸከመውን ነው፡፡ ልጅ ሁሉ ከወላጆቹ በኋላ የተገኘ ነው፡፡ ድንግል ግን የወለደችው ከእርሷ በፊት የነበረውን ፈጣሪዋን ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ፈጣሪ በአንድ ልጅ፣ በአንድ ጊዜ መለኮት በአንድ ጊዜ ሰው መባሉ በድርብ ክብር ለሚኖረው ለክርስቶስ የተገባው ነው፡፡
ጸጋ ካልተትረፈረፈ አምላክን መውለድ የማይቻል ነው፡፡ ለድንግል ማርያም የተሰጠው ጸጋ የማይደገም ጸጋ ነው፡፡ የሴትነት ችሎታም አይደለም፡፡ የሴትነት ወግ ልጅን ያረግዛል፡፡ አዳኝነት ግን መጽነስ አይችልም፡፡ ትልልቅ ሴቶች በዓለም ላይ ተነሥተዋል፡፡ ንጉሥ ፣ ጳጳስ በመውለዳቸውም ተከብረዋል፡፡ ከሴቶች የተለየች ድንገል ማርያም ግን አምላክን ወልዳለች፡፡ ይህ ማንም ሊቀማና ሊሰጥ የማይችለው፣ በችሎታም የማይገኝ በጸጋ የሆነ መመረጥ ነው፡፡ የእስራኤል ደናግል ከሙሴ እህት ከማርያም ኋላ ሆነው ንሴብሖ እንዳሉ የሴት ዓለምም ከፊታውራሪዋ ታዐብዮ ብላ ከዘመረችው ከድንግል ማርያም ጋር ስለ ክርስቶስ ማዳን መዘመር ይገባዋል፡፡ የእርስዎ ልጆች የሚሆኑት ነፍሳቸው ጌታን ስታከብር፣ መንፈሳቸውም አምላክና መድኃኒት በሆነው ጌታ ሐሴት ስታደርግ ብቻ ነው (ሉቃ. 1 ÷47)፡፡
ድንግል ማርያም ትሑት ነበረች፡፡ ብትኰራም የሚያምርባት እርሷ ነበረች፡፡ ነገር ግን መታወቂያዋ ትሕትናና ምሥጢር መጠበቅ ነበር፡፡ አንደበቷንም የምትከፍተው ለመንፈስ ቅዱስ መገልገያነት ብቻ ነው፡፡ መልአኩ መመረጧን በነገራት ጊዜ ይገባኛል አላለችም፡፡ መመረጥ ከመራጩ ጸጋ እንደሆነ ታውቃለች፡፡
መልአኩ ገብርኤል፡- “… እነሆም÷ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ÷ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ፡፡ እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል÷ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል÷ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም…” አላት (ሉቃ. 1÷30-35)፡፡
ዛሬም ይህ ብሥራት ለተጨነቀው ዓለም መልስ አለው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ሆኖ በቤት በመንደራችን ሊወለድ ይፈልጋል፡፡ አዳኝ ሆኖ የሞት ጥላ ባጠላበት ምድር ላይ ሊወለድ ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን የብሥራቱን ድምፅ አምኖ መቀበል ይጠይቃል፡፡ ዛሬ ለእኛ የተሳኑን ነገሮች አቅም ስናገኝ የሚሄዱ አይደሉም፡፡ የሚያስፈልገን የሥልጣኔ አቅምን ማጎልበት ሳይሆን በሥጋ የመጣውን ጌታን ማመን፣ ሞቶ ዓለምን አዳነ የሚለውን ብሥራት መቀበል ብቻ ነው፡፡ እኛስ ብሥራቱን ተቀብለናል?
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ