ወዳጄ ሆይ !
ምድራዊ በረከት ማጣትህ ሰማያዊውን በረከት እንዳያሳጣህ ፣ ወደ ምሬትና ራስን ወደ መጥላት ውስጥ እንዳይከትህ ተጠንቀቅ ። እውነተኛ ሀብትህ የረካህበት ነገር ነው ። የመልካሞች አድራጎት ከማረከህ አንተም እንደዚሁ እድርግ ። የክፉዎች ተግባር ካሳቀቀህ ከዚያ ራቅ ። አጽናፈ ዓለሙን የሚያስተዳድር አምላክ ብለህ እየጠራኸው ያንተ የአጥቢያ ችግር አይረብሽህ ። የኃጢአት ውርደት የንስሐ ክብር ተሰናድቶለታል ። ጻድቅ ተብለህ ከመወደስ ኃጥእ ተብለህ ያለ ጥፋትህ መከሰስ የተሻለ ጽድቅ ነው ። ጻድቅ ሲሉህ ትታበያለህ ፣ ኃጥእ ሲሉህ ግን ክብር ታገኛለህ ።
ወዳጄ ሆይ !
አሁን ካልሆነ ብለህ እንደ ሕፃን አታልቅስ ። የወጣን ሰው ጸልይለት እንጂ መቼ ትመለሳለህ ? ብለህ አታስጨንቀው ። መመለሻው ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነው ። ክፉ ቀን አውሬ ነውና አንተንና የምትወዳቸውን እንዳይበላ ለአፍህ አርምሞ ፣ ለልብህ ትዕግሥት ለምን ። ጉዞህ የሚያስደስትህ እግዚአብሔርን ስታስቀድም ነው ። ጎዶሎ ልብ ሲንቦጫቦጭ መላው የአካል ክፍል ይሰማል ። በአገር የጠፋ ክብር ባንተ ቤት ሲገኝ ቤትህ አገር ትሆናለች ። በመሸፈን ለወንድምህ ያለህን ፍቅር እንደምትገልጥ ጥላቻህንም በማጋለጥ ትገልጣለህ ። በር ዘግተህ እየተኛህ የሰውን በር አትስበር ። ልብስ ለብሰህ እየወጣህ የሌላውን ጠባሳ አታስስ ። ንስሐ አባት እየፈለግህ የሰውን ኃጢአት አትዘርዝር ። አማካሪ እየሻህ የነገሩህን ምሥጢር አታውጣ ።
ወዳጄ ሆይ !
ሰው ያመጣውን መከራ በእግዚአብሔር ትሻገራለህ ፣ እግዚአብሔር ያመጣውን መከራ በንስሐና በጸሎት ታልፋለህ ። አሁን አይተኸው አሁን የምታጣው ፣ ከጥቅምት ደመና ፣ ከጠዋት ጤዛ ፣ ከእንጨት ጢስ ፣ ከውኃ እንፋሎት ፣ ከአውድማ እብቅ ይልቅ ቶሎ ለመጥፋት የቀረበው ፣ ከሸክላ ይልቅ የሳሳው ፣ ወድቆ የማይነሣው የሰው ልጅ ነውና እባክህ ተስማማ ።
ወዳጄ ሆይ !
ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን እንደመጣ ዓለምን ለማጥፋት የሚመጡ ክፉዎች አሉ ። በጥልቀት ስትሆን ምጥቀትን ፣ በምጥቀት ስትሆን ጥልቀትን አትርሳ ። የባሕር መንገደኛ በእግዚአብሔር ማመን ግዱ ነው ፣ በባሕር ዓለም ላይ ያለ ሰውም ከእምነት ውጭ ዕረፍት የለውም ።
ወዳጄ ሆይ !
በቤት ወጪ ታማኝ የሆነ በአሥራት በኵራት ካልታመነ ያው ሌባ ነው ። ቤትህን ሠርተህ የእግዚአብሔርን ቤት ከረሳህ ብትበላ አትጠግብም ፣ ብትለብስ አትደምቅም ፣ ቤት ብትሠራ አታርፍም ። ክፉ ግለሰብ እንጂ ክፉ ጎሣ የለም ። በጠባብ ቀን ውስጥ ስታልፍ እግዚአብሔር ባሰፋልህ ዘመን ተመስገን አላልክምና ንስሐ ግባ ። ኖሮት የማያውቅ ያገኘ ቀን የሚያጣ አይመስለውም ። አማልክት የማይመልሱትን አንዱ አምላክ ግን ይመልሳል ።
ወዳጄ ሆይ !
መመኘትህ የሥራህ ምትክ አይሁን ። ስታገኝ ስስታም አትሁን ። ያለህን በሥርዓት ተጠቀም ፣ ከሌለህ አትቆጥብምና ። እግዚአብሔር እንዲሠራ ከፈለግህ መንገዱን አታስረዳው ። ሰውነት ሲዋረድ ሁሉም ነገር ክብሩን ያጣል ። የመሸባቸውን ስታይ ያንተ ምሽት እንደዚህ እንዳይሆን አልቅሰህ ጸልይ ። የእርዳታ ጸሎት ወደ ፈጣሪህ ስታቀርብ ምጽዋት እየመጸወትህ ይሁን ። ክፋት ድንበር ካጣ የሚቆመው በሲኦል እሳት ውስጥ ነው ። ሌላው እንዲኖር ካላደረግህ መኖርህ አጠራጣሪ ነው ። ስትሰስት አዳምን ፣ ስትሰጥ ክርስቶስን ትመስላለህ ። ገንዘብ የሰጠ ደግ ቢባልም እንደ ዮናታን ዙፋንን የሰጠ ደግ ግን አላየንም ። የአሁኑ የመጨረሻው ነው ብለህ አታስብ ፣ እውነተኛው መጨረሻ በዕለተ ምጽአት ነው ።
ወዳጄ ሆይ !
ስጦታ መዋደድን ይጨምራልና ስጦታ መስጠትን አትርሳ ። ፍቅርና እሳት ካልቆሰቆሱት አይነድምና መፈላለግን አትርሳ ። ምርቃት ባነሡለት ቍጥር የሚጨምር ሀብት ነውና ተመረቅ ። የእግዚአብሔርን መልእክተኛ ገፍተህ የእግዚአብሔርን ምሕረት መፈለግ ከንቱ ድካም ነው ። ሎጥ መላእክትን ባይቀበል ኖሮ በዚያ ቀን ከሚጠፉት አንዱ በሆነ ነበር ። የምትቀበላቸው ማን መሆናቸውን አታውቅም ። እግዚአብሔር የሚያድረው ኃጢአትን በሚሸፍነው በሴም ድንኳን ነው ።
ወዳጄ ሆይ !
ወንድ ልጅ ስትወልድ ዕቃ እንዳይሰብር ጠብቀው ፣ ሴት ልጅ ስትወልድ እንዳትሰበር ጠብቃት ። በምሥራቅ ያየሃት ፀሐይ በምዕራብ ትጠልቃለች ፤ ሰውም የተወለደበት ቦታ ላይሞት ይችላል ። ኑሮህ እንዳያስጠላህ የንጽጽር አስተሳሰብን ካንተ አርቅ ። ድንኳንህ እንዳይናወጥ በቃሉ ካስማ አቁመው ።
ወዳጄ ሆይ !
ማስተዋል ከዳግም ኀዘን ይጋርዳል ። የሰው መውደቅ ሰውን ካላሳዘነው ሰው አውሬ ሆኗል ማለት ነው ። በዙሪያህ ዘመድ ሳይሆን ቅዱሳን መላእክት ቢኖሩ ይሻላል ። እግዚአብሔርን ስትፈራ በእግዚአብሔር መላእክት ታጥረሃል ። እማሆይ ትሬሣ ደግ ናቸው ፣ ሂትለር ጨካኝ ነው ፤ አንተስ ምንድነህ ?
ክርስቶስ በሰላም በምድራችን ይገለጥ !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም.