የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ብርሃን ወጣላቸው (ክፍል 3)

                                        እሑድ ነሐሴ 10/2007 ዓ.ም.
 “ቅፍርናሆም መጥቶ ኖረ
/ማቴ. 4፡14/
ቅፍርናሆም ማለት የናሆም መንደር ማለት ነው፡፡ የነቢዩ የናሆም መኖሪያ ስለነበረች ይህን ስያሜ  አግኝታለች፡፡ ቅፍርናሆም የተመሠረተችው በባሕር ዳርቻ ላይ ነው፡፡ የቅፍርናሆም ነዋሪዎች ኑሮአቸውን የመሠረቱት በባሕሩ ዳርቻ በጥብርያዶስ ድንበር ላይ ነው፡፡ የባሕሩ ዳርቻ የተለያዩ መገለጫዎች አሉት፡፡
1.        የባሕሩ ዳርቻ የሰማይ ዳር የሚታይበት ይመስላል፡-
በባሕር ዳርቻ የሚኖሩ ሰዎች የሰማዩን ጥግ የሚያዩት ይመስላቸዋል፡፡ አሻግረው ሲያዩ ባሕሩ ላይ የተከደነ የሚመስል ሰማይን እንጂ የተዘረጋ ሰማይን አያዩም፡፡ እነርሱ ከሚያዩት ውጭ ሰማይም አገርም ያለ አይመስላቸውም፡፡ የሰማይን አድማስ፣ የመሬትን ድንበር የሚለኩት በሚያዩት ርቀት ነው፡፡ ከመንደራቸውና ከዕይታቸው ውጭ ሰማይም መሬትም እንዳለ መቀበል ይከብዳቸዋል፡፡ የሚወስኑት በሚያዩት ብቻ ነው፡፡ የባሕር ዳርቻ እንዲህ ያለ መገለጫ አለው፡፡ ኢየሱስ መጥቶ የኖረው በዚህ በቅፍርናሆም በባሕሩ ዳርቻ ነው፡፡
የሰማይ ድንበሩ ያለው የዕይታችን መጨረሻ ላይ አይደለም፡፡ ሰማይ ከዕይታችን ይሰፋል፡፡ በማየት የምንቀበለው ጥቂቱን ሲሆን በማመን የምንቀበለው ብዙ ነገር ነው፡፡ የዚህችን ዓለም መጠን በሚያዩት ዓይናቸው ብቻ የወሰኑ ሰዎች እነዚህ የቅፍርናሆም ነዋሪዎች የባሕሩ ዳርቻ ሰዎች ናቸው፡፡ ካሉበት ዓለም ውጭ ሌላ ዓለም እንዳለ የማይቀበሉ፣ የሚያዩትን ብቻ ሕይወት ብለው የሚያስቡ ወገኖች ዛሬም አሉ፡፡ ሕይወትን በመንደር መጠን መወሰን ከባድ ነው፡፡ በሌሎች ዘንድ ያለውን በረከት እንዳንቀበልም እንቅፋት ይሆንብናል፡፡ ምንም ጎበዝ ብንሆን በሁሉም ነገር ምሉኣን ልንሆን አንችልም፡፡ እግዚአብሔር ጸጋውን ሁሉ ጠቅልሎ ለአንድ ግለሰብ፣ ለአንድ አጥቢያ ቤ/ክ፣ ለአንዲት አገር አልሰጠም፡፡ እግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋዎቹን በልዩ ልዩ ቦታዎች አስቀምጧል፡፡ ተፈጥሮአችንን ስናየው የምንሰጥ ብቻ ሳይሆን የምንቀበልም ነን፡፡
ዓለማችን በዚህ ታላቅ የቴክኖሎጂ ዘመን የገጠማትና ያፈርሳታል ተብሎ የሚያሰጋት ነገር ቢኖር ጠባብነት ነው፡፡ የኒውክለርን ያህል ጠባብነት አስጊ ነው። የእኛን እናት ለመውደድ የሌላውን እናት መጥላት ተገቢ አይደለም። አገራችንን ለመውደድ ጎረቤት አገርን መጥላት፣ ሃይማኖታችንን ለመውደድ ሌሎችን ሃይማኖቶች መንቀፍ አያስፈልግም። ድንበር የለሽ ስለሆነ ዓለም በሚወራበት ዘመን ሰዎች በመንደር ተከፋፍለዋል። ስለ ዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት በሚለፈፍበት ዘመን አንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በአንድነት ልትቆም አልቻለችም። ሁሉም ሰው በቡድንተኝነት ስሜት ስለተያዘ አንዱ እግዚአብሔር የመግባቢያ ርእስ፣ የአንድ አዳም ዘር መሆናችን የመቀባበላችን ምክንያት ሊሆን አልቻለም። የሚወራውና የሚኖረው ለየቅል ሆኖ ዓለም ደንቁራለች። በቀለም፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት ያለው ጠባብነት ለዓለም ጉዞ ትልቅ እንቅፋት እየሆነ መጥቷል፡፡ ሁሉም የራሱን ደሴት ከመሠረተ መፈላለግና መከባበር ደግሞ በፍቅር መተያየት ሊኖር አይችልም፡፡ አራዊትን በማልመድ ሥራ ተጠምደን ከወንድሜ አልግባባም ማለት አሳፋሪ ነው። ሰውን ከሚያህል ፍጡር ጋር የማይፈታ ኅብረት አለን። ከሰው ጋር ጨርሶ የማንግባባ አይደለንም። እስከ ቀዩ መስመር እንኳ መነጋገር አለመፍቀዳችን፣ በአንዱ አለመግባባት በሁሉም አለመግባባት ነው ብለን ማሰባችን ይህ ውርደታችን ነው። የሚለያዩንን ግንቦች ስንገነባ ከመዋል የሚያገናኙንን ድልድዮች ስንዘረጋ ብንውል ክብር ነው። የአጽናፈ ዓለሙ ገዥ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ እስከሚገዛበት ዳርቻ ልባችን ሰፊ መሆን አለበት፡፡ ዛሬ ችግረኛን እንኳ ለመርዳት ዘርና ሃይማኖት ሲለይ እናያለን፡፡ ችግር የሰውነት ጉዳይ እንጂ የዘርና የሃይማኖት ጉዳይ አይደለም፡፡ ምጽዋት ወይም እርዳታ ክቡር የሚሆነው የእኔ ለማንለው ቸርነት ስናደርግ ብቻ ነው፡፡

ይህች ዓለም የምትንቀሳቀሰው በተፈጥሮ ሀብት፣ በዕውቀት፣ በሰው ኃይል ነው። እነዚህ አቅሞች ተበታትነው ተቀምጠዋል። ሀብቱ ዐረቦች ጋ ነው ብንል፣ ዕውቀቱ ምዕራባውያን ጋ፣ የሰው ኃይሉ አፍሪካውያን ጋ ይገኛሉ። የሚያፈላልገን ይህ የተፈጥሮ መሻት ነው። የአፍሪካን ወርቅ አልማዝ አውሮፓውያን ይጠቀሙበታል፣ የቻይናን ምርት አፍሪካውያን ይገዙታል፡፡ መላውን ዓለም የሚያስተሳር ያልተሟላ ፍላጎት አለ፡፡ ብዙ የምዕራብ አዋቂዎች በአፍሪካ ምርምር ያካሂዳሉ፣ የአፍሪካ ልጆች በምዕራብ አገሮች ለትምህርት ይጓዛሉ፡፡ አንዱ ካንዱ የሚፈልገው ቁሳዊ፣ አእምሮአዊና መንፈሳዊ በረከት አለ፡፡
ጌታችንን ስናገኝ ከምናገኘው ስጦታ አንዱ ልበ ሰፊነት ነው፡፡ ልበ ሰፊነት ከሌለ፡-
      ሳንደማመጥ እንወጋገዛለን
      ሳንተያይ እንራራቃለን
      ሳናነብ እንተቻለን
      ሳንሰማ እንወስናለን
ልበ ሰፊ ያልሆነ ሰው መናገር እንጂ ማዳመጥ አይችልም፡፡ የተፈጠረለት አንደበት እንጂ ጆሮ እስከማይመስል በራሱ ምሕዋር የሚሽከረከር ነው፡፡ ልበ ሰፊ ያልሆነ ሰው ቶሎ የሚቀበለው የሰውን ክፉነት እንጂ መልካምነቱን አይደለም። ነገር ግን ሁሉን መስማት የሚሻለውን መምረጥ፣ ሁሉን መፈተን የሚበልጠውን መከተል ሕይወትን ለሚፈልግ ሰው የተገባ ነው፡፡
2.     ድንገተኛ ርጥበት የሚያቀዘቅዝበት ስፍራ ነው፡-
     የባሕሩ ዳርቻ ድንገተኛ ርጥበት የሚያቀዘቅዘን፣ አካባቢው ደርቆ በነፋሻ አየር የሚሞላን ስፍራ ነው፡፡ እንደ ባሕሩ ዳርቻ በድንገት የመረበሽ ስሜት የሚሰማቸው፣ በደመቀ ጨዋታ ውስጥ በአሳብ ጭልጥ ብለው የሚጠፉ፣ እየሳቁ ሳቁ ሳያልቅ የሚያለቅሱ፣ የሆነላቸውን መልካም ነገር እየተናገሩ ወዲያው በምሬት የሚታመሙ፣ በዓመት የገነቡትን በዕለት የሚያፈርሱ፣ በድንገት ተስፋ ቆርጠው ሁሉን አፍርሰው ለመሄድ የሚወስኑ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች መጀመር፣ ብዙ ነገሮችን መወጠን አይከብዳቸውም፡፡ ችግራቸው መፈጸም ነው፡፡ ስለብዙ መሠረቶች እንጂ ስለአንድ ጉልላት ወይም ፍጻሜ መናገር የማይችሉ ናቸው፡፡ ሕይወታቸው ሁልጊዜ በግልግል የቆመ ነው። መች እንደሚያብዱ እንኳ ለራሳቸው ማወቅ አይችሉም፡፡ ወፈፍ ያለ ቁመና አላቸው፡፡ ሳቅና ልቅሶአቸው የሚቀላቀልባቸው፣ እያመሰገኑ ምስጋና ሳያልቅ ርግማን የሚጀምሩ፣ አደፋፍረው እነርሱ የማይሄዱ፣ አደራጅተው የማይፈጽሙ ናቸው፡፡ ገና ሌላ ለመጀመር ያስባሉ እንጂ ስላለፈውና ስላልተፈጸመው መሠረት ማሰብ እንኳ አይፈልጉም፡፡ ሁልጊዜ በሙቀት ይጀምራሉ፣ መፈጸም ግን የሞት ያህል ይከብዳቸዋል፡፡ ይህ የባሕሩ ዳርቻ ጠባይ ነው፡፡ ጌታችን መጥቶ የኖረው ወደ እነዚህ ሰዎች ነው፡፡ ባሕርይውን ሊያለብሳቸው ከማይመቸው ባሕርያቸው ጋር ኖረ።
ሰው ሊመራ/ሊጓዝ የሚገባው በዕውቀቱ ወይም በስሜቱ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ነገሮችን ሁሉ በስሜታችን እንደማረጋገጥ ያለ ደካማነት የለም፡፡ የዕውቀት መለኪያው ስሜት ሳይሆን ቃሉ ነው፡፡ ስሜት ተጓዥ፣ የማይቆም የነፋስ ሠረገላ ነው፣ ስሜት ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ከስሜት ነዋሪነት ወደ እውነተኛ ነዋሪነት የምንመጣው ጌታ በመካከላችን መጥቶ ሲኖር ነው፡፡ ወደ ቅፍርናሆም መጥቶ መኖሩ ለስሜታውያን የዕውቀት ብርሃን ለመሆን ነው፡፡
3.     የረጋ ነገር አይታይም፡-
ባሕሩ የሚኖረው እንደ ተናወጠ ነው፡፡ የአፍታ እርጋታ የለውም፡፡ ባሕሩ የማይችለው ማዕበል ሲመጣም ቤቶች መፍረስ ይጀምራሉ፡፡ የባሕሩ ዳርቻ ነዋሪዎች ኑሮአቸው ስጋት የሞላበት ነው፡፡ ዛሬ በባሕር ዳርቻ ላይ የተመሠረቱ ትልልቅ ከተሞች ስጋት ላይ ወድቀዋል፡፡ የባሕሩ ዳርቻ እስከ ጊዜው ደስ የሚል መጨረሻው ግን በጥፋት የሚያበቃ ነው፡፡
የብዙዎች ኑሮ እንደ ባሕሩ ዳርቻ የሚናጥ ነው፡፡ መረጋጋት የለበትም፣ ለማሰብ የጎረሱትን ለመዋጥ እንኳ ጊዜ የላቸውም፡፡ ሁሉም ነገራቸው ጥድፊያ ነው፡፡ ባልንጀሮቻቸው፣ ዓለሙና ዘመኑ ያመለጣቸው እየመሰላቸው ይሮጣሉ፡፡ የሚመኙትን ለመጨበጥ ሲጣደፉ የጨበጡትን ይጥላሉ፡፡ የሚያዩአቸው ታታሪ ይሏቸዋል፡፡ ትጋት በሚመስል መክነፍ ውስጥ እንደሚኖሩ አያውቁም፡፡ ያማረ ቤት ቢሠሩ አርፈውበት፣ የመዋኛ ገንዳ ቢያበጁ ዋኝተውበት አያውቁም፡፡ የሀብቱ ስሙ ካልሆነ በቀር ጥቅሙ ደርሶአቸው አያውቅም፡፡ ራሳቸውን እያጡ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን እየከሰሩ ቢሰበስቡም በመጨረሻ ላለፉበት ለሌሎች ጥለውት ይሄዳሉ፡፡ የእነርሱ እርካታ ቢስነት እነርሱን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡንም ይበጠብጣል፡፡ ባለማስተዋል፣ ሁሉን ልጨብጥ በሚለው መንገዳቸው በመጨረሻ ቤተሰቡ ይፈርሳል፡፡ ያላቸውን ከሌላቸው፣ የሚያስፈልገውን ከማያስፈልገው ለመለየት አቅም የላቸውም፡፡ የመግቢያውን በር እንጂ የመውጫውን በር አያዩም፡፡ ሁሉንም ነገር የሚችሉት፣ ሁሉም ቀዳዳ የሚያሾልካቸው ይመስላቸዋል፡፡ ስለዚህ የሚሰበስቡት ለመበተን፣ የሚታዩት ለመጥፋት ነው፡፡ እነርሱ ተረጋግተው የተቀመጡ ቀን ዓለም የሚያልፍ ይመስላቸዋል፡፡ ያሰቡትን በትክክል ሳይናገሩ፣ ፍቅራቸውን በቅጡ ሳይገልጡ፣ ልጆቻቸውን በእርጋታ ሳያጫውቱ፣ ትዳራቸውን ጊዜ ሳይሰጡት፣ ወዳጆቻቸውን ለይተው ሳያውቁ በረው የቀሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ሰዎች በምክር መመለስ አንችልም፣ ከጉዳታቸው አይማሩም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በራእይ መጓዝን ይሰጣቸዋል፡፡
4.     የባሕሩ ዳርቻ ለጊዜው ነው፡-
የባሕሩ ዳርቻ ለመዝናናት አስደሳች ነው፡፡ ለመኖር ግን አስጊ ነው፡፡ የተለያዩ ሰዎች ስለሚመላለሱም የባሕሩ ዳርቻ ነዋሪዎች ወረተኞች ሁልጊዜ አዲስ ፊት ናፋቂዎች ናቸው፡፡ የሌሎችም መዝናኛ ሆነው ዘመናቸውን ይፈጽማሉ፡፡ የባሕሩ ዳርቻ ሱስ ስላለው ርቀው መሄድ አይሆንላቸውም፡፡
ሕይወት ተጠቅመን የምንጥላት ዕቃ አይደለችም፡፡ ሕይወት ዘላቂ ናት፡፡ ሕይወታቸውን ለጊዜያዊ ነገር ያዘጋጁ፣ ዛሬን ተደስተው ነገ የፈለጉትን ለመሆን የቆረጡ ሰዎች ዛሬም አሉ፡፡ ሁልጊዜ አዲስ፣ አዲስ ነገር የሚፈልጉ የሰነበተ ፍቅር፣ የሰነበተ ሰው፣ የሰነበተ በረከት የሚሰለቻቸው ሰዎች አሉ፡፡ የዓለም ሕዝብ ሁሉ በዙር እነርሱ ጋ የሚመጣ ሁልጊዜ ሰው እያለዋወጡ የሚኖሩ የሚመስላቸው፣ አንድ ቀን ብርቱ ብቸኝነት እንደሚመጣ የማይገመቱ ሰዎች እነዚህ የባሕሩ ዳርቻ ነዋሪዎች ናቸው፡፡
ጌታችን መጥቶ መጥቶ የኖረው በዚህች በቅፍርናሆም በባሕሩ ዳርቻ ነው፡፡ ከእነዚህ ሰዎች ጋር መኖር ከባድ መስሎ ቢታይም ጌታ ግን አብሯቸው ኖረ፡፡ እነዚህ ሰዎች ያን ያህል አስበውና አልመው ሰውን የሚጎዱ አይደሉም፣ ራሳቸውን ግን በብርቱ ይጎዳሉ፡፡ የተደገፋቸውን ቤተሰብም አደጋ ላይ ይጥላሉ፡፡ ኑሮአቸው ሁሉ ጅው ጅው ያለበት ነው፡፡ ከአእምሮአቸው እግራቸው ይፈጥንባቸዋል፡፡ ጌታ ግን አስፈልጋቸዋለሁ ብሎ አብሯቸው ኖረ፡፡
አብሮ መኖር ትልቅ ዋጋ መክፈል ነው፡፡ ሰዎች አሳባችንን ይካፈላሉ እንጂ አብረውን ለመኖር አይደፍሩም፡፡ በተመጠነ ሰዓትና በተመጠነ እግር ያገኙናል እንጂ አብረውን ለመኖር አይፈቅዱም፡፡ አብሮን ለመኖር የሚፈቅድ ካለ ትልቁ ወዳጃችን ነው፡፡ አብሮን ለመኖር ወደ እኛ የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ሰዎች የሚለወጡት በስብከት ብቻ ሳይሆን አብረናቸው በመኖር፣ ችግራቸውን በመካፈልም ነው፡፡ ሰዎች በፍቅር ይማረካሉ፡፡ እኛም ሕይወት እንደ ባሕሩ ዳርቻ ነዋሪዎች  ሆናብን ከሆነ ጌታ ሆይ  ወደ ግዛቴ ወደ ኑሮዬ ደሴት ግባ ብንለው የተዝረከረከውን አስተካካይ፣ የተበላሸውን አዳሽ ኢየሱስ ክርስቶስ ይገባል፡፡
                   ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ