የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

‘‘ብርሃን ወጣላቸው’’ /ክፍል 5/

የአሕዛብ ገሊላ
                                          /ማቴ. 4፡16/     ረቡዕ ነሐሴ 20/2007 ዓ.ም.
በዓለም ላይ በሁለት ጥግ ላይ የቆሙ ጽንፈኞች ብቻ ሳይሆን ከሁለቱም የሚመቻቸውን መርጠው የራሳቸውን እውነት ፈጥረው የሚኖሩ ለዘብተኞችም አሉ፡፡ ለሰይጣን ረጅም ግብ የሚመቱለት ከአክራሪዎቹ ለዘብተኞቹ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ያወቁ ስለሚመስላቸው ዕውቀትን፣ የጨረሱ ስለሚመስላቸው ንስሐን አይፈልጉም፡፡ ራሳቸውን እያታለሉ ዘመናቸውን ይፈጽማሉ፡፡ በመጨረሻም የሰይጣን ይሆናሉ፡፡ ሰይጣን በትልቁ የሚዋጋው ዕድሜአችንን ነው፡፡ ዘመናችንን በማታለል ከፈጸመ በኋላ በመጨረሻ የእርሱ እንድንሆን ያደርጋል፡፡
ሕይወት ውስብስብና የማትታወቅ አይደለችም፡፡ ሕይወት ብርሃንና ጨለማ ናት፡፡ ራሳችንን የምናገኘው ወይ በብርሃን ወይ በጨለማ ውስጥ ነው፡፡ በብርሃን ውስጥ ካለን በጨለማው ውስጥ የለንም፣ በጨለማው ውስጥ ካለን በብርሃን ውስጥ የለንም፡፡ በዓለም ላይ ያሉት ሁለት ካምፖች ናቸው፡፡ ሦስተኛና ገለልተኛ ካምፕ የለም። ወይ ከክርስቶስ ካምፕ ወይ ከሰይጣን ካምፕ ውስጥ ነን፡

ብዙ ለዘብተኞች ግን ከሁለቱም የለንበትም ለማለት ይሞክራሉ፡፡ በደርግ ዘመን በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር በነበረው ፍልሚያ ከአንዱ የሆነ አንድ ጥይት ሲያገኘው ከሁለቱም ጋ አለሁ የሚል ሁለት ጥይት ያገኘው ነበር፡፡ ከአንዱ መሆን የሕይወት ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ የአሕዛብ ገሊላ ነዋሪዎች ግን ከሁለቱም አለን የሚሉ በሁለቱም የሌሉ ነበሩ፡፡
በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ዘመነ መንግሥት የእስራኤል መንግሥት ለሁለት ተከፈለ፡፡ ዐሥሩ ነገድ ሰሜናዊ መንግሥት አቋቋሙ፡፡ የእስራኤል መንግሥት ተባሉ፡፡ ሁለቱ ነገድ፣ ነገደ ይሁዳና ነገደ ብንያም የደቡብ መንግሥት አቋቋሙ፡፡ የይሁዳ መንግሥት ተባሉ፡፡ መለያየትን የሚከተለው ጥፋት ነውና ሰሜናዊው መንግሥት በ722 ዓ.ዓ. ከክርስቶስ ልደት በፊት በአሦራውያን ተወረረ፡፡ አሦራውያንም ያደረጉት ወረራ እጅግ ብርቱ ነበር፡፡ ከአሦር ጎበዞችና ባለጌዎችን ሰብስበው ወደ እስራኤል አመጡ፡፡ ስለ እስራኤል የሚያውቁ ሽማግሌዎችን ወስደው በአሦር አስቀመጡ፡፡ በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፣ ተጋባ፣ ባሕሉ ደፈረሰ፣ ሥነ ምግባሩ ፈረሰ፡፡
የአሕዛብ ገሊላ የተባለው ከዚህ ጊዜ በኋላ ነው፡፡ በገሊላ የሚኖሩ ሰዎች አብዛኛዎቹ ቋንቋቸው ተቀላቀለ፣ ባሕላቸው ተለወጠ፣ ከእውነተኛቹ እስራኤላውያን ጋር ተለያዩ፡፡ ከአረማውያን ጋር በጋብቻ ተቀላቀሉ፡፡ ስለዚህ በደቡብ የሚኖሩት አይሁድ እነዚህን ወገኖቻቸውን እንደ ርኩስ ቆጠሯቸው፡፡ በኢየሩሳሌም መቅደስ እንዳይገቡም በከለከሏቸው ጊዜ በሰማርያ በደብረ ገሪዛን መስገድ ጀመሩ፡፡ ጌታችን መጥቶ የኖረው በዚህ ምድር ነው፡፡ 

መቀላቀል፣ መበረዝ፣ መከለስ እጅግ ከባድ ነው፡፡ በኃይል ከተያዙ ጭቁኖች ይልቅ የተቀላቀሉ ጭቁኖች ያሳዝናሉ፡፡ የአሕዛብ ገሊላ  ናቸው፡፡ ገሊላ ብቻ አይደሉም፣ አሕዛብም ናቸው፡፡ አሕዛብም ብቻ አይደሉም ገሊላም ናቸው፡፡ ይህንን መዋሐድ በመደብ በመደብ ማስቀመጥና መለየት አይቻልም፡፡ እነዚህ ወገኖች የተቀላቀሉ ናቸው፡፡ ከአሕዛብ የወረሱት አለ፣ ከእስራኤልም የወረሱት አለ፡፡ ለፍርድ አይመቹም፡፡ እንደ አሕዛብ መደዴ እንደ እስራኤል ባለሕግ፣ እንደ አሕዛብ ጣዖታውያን እንደ እስራኤል በአንዱ ጌታ አማኝ ይመስላሉ፡፡ ጥቁር አይደሉም፣ ቀይም አይደሉም፤ ጉራማይሌ ናቸው፡፡ በአገራችን አጠራር ዓሊ ገብረማርያም ናቸው፡፡ ከአንዱ በቅጡ ስለሌሉ ከሁለቱም የሉም፡፡
ከአንዱ ያልሆነ በሁለት ጥይት ይሞታል እንደተባለው የሁለት ዓለም ስደተኛ ሆኖ የሚቀር አንዱን ያልመረጠ ሰው ነው፡፡ የሕይወት ጣዕም ያለው በመወሰን ውስጥ እንጂ በማቻቻል አይደለም፡፡ የማይታረቁ ነገሮችን ለማስታረቅ መሞከር የሕይወት ትልቁ መከራ ነው፡፡ በሕግ፣ በባሕል፣ በሃይማኖት የማይታረቁ ነገሮችን ለማስታረቅ መሞከር በሕግ መከሰስን፣ በባሕል መገለልን፣ በሃይማኖት መወገዝን ያስከትላል፡፡ የብዙ ሰው ሕይወት ሁለት የያዘ መስሎት አንድም የሌለው ነው፡፡ የተሰጠን ዕድሜ ቶሎ ወስነን ሥራችንን የምንፈጽምበት እንጂ የምናመነታበት አይደለም፡፡
የብዙዎች አምልኮ የአሕዛብ ገሊላ ነው፡፡ አምልኮ የሚገባው፣ ፈጥሮ የሚገዛው ጌታ እያለ በእርሱ ላይ ይደርቡበታል፡፡ እግዚአብሔር በአምልኮቱ ቀናተኛ መሆኑን እየረሱ አምልኮውን ያጋሩበታል/ዘጸ. 20፡1-7፤ ኢሳ. 42፡8/፡፡ ሰው በባሕርይ ድካም  ይበድል እንጂ እንዴት በአምልኮቱ ይበድለዋል; ሕንዶቹ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ሲነገራቸው እርሱ የሚመሰልበት መልክ ምንድነው; ቀርፀን እናመልከዋለን ይላሉ፡፡ ከሁለት ሚሊየን በላይ ጣዖቶች ባሉበት አገር ላይ ኢየሱስ ክርስቶስንም ከእነርሱ እንደ አንዱ አድርገው ለማምለክ ይፈልጋሉ፡፡ እርሱ ግን ብቻውን አምላክ፣ ብቻውን ጥበበኛ ሆኖ የሚኖር ነው፡፡ ከኃጢአት ሁሉ የሚበልጥ ኃጢአት የአምልኮ አመንዝራነት ነው፡፡ አመንዝራ በሕግ ባሏ ላይ ውሽማ እንደምትይዝ ሕጋዊውን አምላክ ትቶ ፍጡርን ማምለክ መንፈሳዊ ዘማዊነት ነው፡፡
የጋብቻ ጥምረትን በተመለከተ የብዙዎች መኖሪያ የአሕዛብ ገሊላ ነው፡፡ ጋብቻ ከአካል ይልቅ የአሳብ አንድነት ነው፡፡ ጋብቻ በሁለት እስር ከተገመደ ይፈታል፡፡ እግዚአብሔር ሦስተኛ ሆኖበት ከተገመደ ግን አይፈታም /መክ. 4፡12/፡፡ እግዚአብሔር ያልከበረበት ጋብቻ በእልልታ ይጀመራል፣ በኡኡታ ይፈጸማል፡፡ በጋብቻ ላይ ቀዳሚው መስፈርት ሀብት አለው ወይም አላት ሳይሆን እግዚአብሔር አለው ወይም አላት የሚል መሆን አለበት፡፡ እግዚአብሔር ያለው ምንም አይጎድልበትም፡፡ በእግዚአብሔር አምላክነት፣ በክርስቶስ አዳኝነት ማመን ትልቁ የጋብቻ መስፈርት ነው፡፡ የጋብቻ መሥራቹ እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ የጋብቻ ዝርዝር መረጃ፣ የሰላም ሰነዱ ያለው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ያላስቀደመ ጋብቻ የሰዎች ኅብረት ብቻ በመሆኑ መጋባት ሳይሆን ግራመጋባት፣ መስማማት ሳይሆን መጐዳዳት የበዛበት ይሆናል፡፡ ይልቁንም ከማያምኑ ሰዎች ጋር በቃል ኪዳን መተሳሰር ከባድ ነው፡፡ ከማያምኑ ጎረቤቶች ጋር መኖር ይቻል ይሆናል፡፡ ከማያምኑ ጋር ጋብቻ መመሥረት ግን ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ጋብቻ ከመግባት በፊት በቃለ እግዚአብሔር ሥልጣን ማመን ትልቅ መሥፈርት ሊሆን ይገባዋል፡፡ የጋብቻ መንገድ እንደ ፈጣን መንገዶች በአገራችን ቀለበት መንገድ ብለን እንደምንጠራው መንገዱን ከሳትን ለመመለስ ረጅም ርቀት ያስጉዛል፡፡
የተቀላቀለ የጋብቻ ሕይወት ባለበት ቤት ውስጥ ሰላም የለም፣ ልጆችም ከዚህ ሁኑ ከዚያ እየተባሉ እየተጨነቁ ያድጋሉ፡፡ በመጨረሻ ልጆቹ ሃይማኖት የለሽ ይሆናሉ። ምክንያቱም ሃይማኖት የልጅነታቸውን ሰላም እንዴት እንደጎዳው ያውቃሉና። አስቀድሞ መጥኖ መደቆስ ወሳኝ ነው፡፡ አስቦ ማድረግ እንጂ አድርጎ ማሰብ የሰውነት ባሕርይ አይደለም፡፡
የብዙዎች ሕይወት የአሕዛብ ገሊላ ነው፡፡ ቋንቋቸው የተደባለቀ አዛጦናዊ ነው/ነህ. 13፡23-24/፡፡ ባለ ሁለት ደብተር ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በዓለም ስም ጥሪ ሲካሄድ ሁለቱም ቦታ አቤት ይላሉ፡፡ እግዚአብሔርና ዓለም ቢታረቁላቸው ሰላም ይሰማቸዋል፡፡ ኃጢአትን ሲኩሉ፣ ሲቀባቡ ይውላሉ፡፡ እግዚአብሔር በቃሉ ርኩስ ያለውን በዘመናዊ አስተሳሰብ ወይም በሳይንሳዊ ድጋፍ ቅዱስ ለማለት ይሻሉ፡፡ ይህንን ሕይወት የሚኖሩ ሰዎች ራሳቸውን የሚያታልሉ በእግዚአብሔር ስለመዘበታቸውም ለታላቅ ፍርድ የተዘጋጁ ናቸው፡፡
ጌታችን መጥቶ የኖረው በአሕዛብ ገሊላ ነው፡፡ እርሱ የውሳኔ ኃይል ነው፡፡ ሁለት ዓለምን እያጣቀሱ ለሚኖሩ፣ እንደ ድንበር ላይ ነዋሪ ሁለት ቋንቋ ለሚናገሩ ለውሳኔ የሚረዳ ኃይል ነው፡፡ ያለ ውሳኔ ሰይጣንን ደስ ማሰኘት ይቻል ይሆናል፡፡ ያለ ውሳኔ ግን እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ጋር መመለክ አይከፋው ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ግን ከሰይጣን ጋር መመለክን አይወድም፡፡
በእውነት ጌታችንን ስናገኘውና ሲያገኘን ቆራጥ ወታደሮች ያደርገናል፡፡ እኛስ አምልኮአችን፣ ኅብረታችን፣ ሕይወታችን የተቀላቀለ ይሆን; በሁለት መንገድ የሚሄድ አንድ ግብ የለውምና በቶሎ እንወስን፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ