የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

“ብርሃን ወጣላቸው” /ክፍል 6/

ታላቅ ብርሃን
                                        ሰኞ ነሐሴ 25/2007 ዓ.ም.
ብርሃን ደስታ ነው፡፡ ብርሃን መጽናናት ነው፡፡ ብርሃን መገናኛ ነው፡፡ ብርሃን ማድነቂያ ነው፡፡ ብርሃን የሥራ መጀመሪያ ነው፡፡ ብርሃን የእግዚአብሔር መንግሥት መገለጫ ነው፡፡ ብርሃን ማስተዋል ነው፡፡ ብርሃን ክርስቶስ ነው፡፡ የጌታችን ልደት የሕጻን ልደት ሳይሆን የብርሃን ልደት ነበር፡፡ እርሱ በገባባቸው መንደሮች፣ በተጓዘባቸው ጎዳናዎች የሕይወት ብርሃን ነበር፡፡ ጨለማ ለሰዓታት እንኳ ያስጨንቃል፡፡ 55ዐዐ የተጋረደው የኃጢአት ጨለማ የቃለለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ለዕረፍት የተሰጠን የሌሊቱ ጨለማ እንኳ ያስፈራል፣ ቅጣት ሆኖ የወደቀብን የነፍስ ጨለማ ይበልጥ ያስፈራል፡፡ ጨለማ በብርሃን እንጂ በጉልበት አይወገድም፡፡ እነዳዊት በንግሥናቸው፣ እነሰሎሞን በጥበብና በሀብታቸው ያላስወገዱት ጨለማ በእግዚአብሔር ልጅ መምጣት ተወግዷል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ የተናገረው የብርሃን ተስፋ በክርስቶስ ተፈጽሟል፡፡ ይህንንም ወንጌላዊው ማቴዎስ ትንቢቱን ከፍጻሜው ጋር አስማምቶ ተርጉሟል፡- “… በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፥ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው” (ማቴ. 4፥14-16፣ ኢሳ. 9፥1-2)፡፡
ጌታችን፡- “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ”ብሏል (ዮሐ. 8፥12)፡፡ ፀሐይና ጨረቃ እንዲሁም ከዋክብት በሚያበሩበት ዓለም እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ አለ፡፡ እነዚህ የተፈጥሮ ብርሃናት ለዓይን እንጂ ለሕይወት አያበሩም፡፡ የሕይወትን ጨለማ የሚያስወግድ ያ ፈጣሪ ብርሃን ነው፡፡ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የተፈጠሩ ብርሃናት የሕይወትን ጨለማ የኃጢአትን ጽልመት አያስወግዱም፡፡ ብርሃናዊው ጌታ ግን የጽድቅ ፀሐይ ነው፡፡

ፀሐይና ጨረቃ እንዲሁም ከዋክብት የሚያበሩት በዚህ ዓለም ነው፡፡ የወዲያኛው ዓለም ብርሃን ግን ራሱ ክርስቶስ ነው/ራእ. 21፡22-27/፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ፀሐይ ገለል ስትል ጨለማ ይሆናል፡፡ ከስፍራው የማይታጣው ጌታ ባለበት ሰማይ ግን ሌሊት የለም። ፀሐይና ጨረቃ ለዓይን ያበራሉ፤ የልቡናና የሕይወት ብርሃን ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
በጥንተ ፍጥረት ብርሃን ባለመኖሩ የተከሰቱ ዋና ዋና ችግሮች ነበሩ፡-
1.     ባዶነት “ምድርም ባዶ ነበረች” /ዘፍ.1፡2/
2.    ጨለማ “ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ” /ዘፍ. 1፡2/
3.    ዝርክርክነት “የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር” /ዘፍ. 1፡2/። የእግዚአብሔር መንፈስ በታላቅ ዝግጅት ላይ የነበረው የተዝረከረከውን ለማስተካከል ወይም መልክ፣ መልክ ለመስጠት ነው።
እነዚህ ችግሮች እንዲወገዱ እግዚአብሔር “ብርሃን ይሁን” አለ (ዘፍ. 1፥3)፡፡ ብርሃን ለታላላቅ ችግሮች መፍትሔ ነው፡፡ የተፈጥሮ ብርሃናት ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት የተፈጠሩት በአራተኛው ቀን ነው፡፡ “ብርሃን ይሁን” ተብሎ የታወጀው አዋጅ ግን ራሱ እግዚአብሔር ብርሃን የሆነበት ነው፡፡ ዛሬም ባዶነት እንዲወገድ፣ ጨለማ እንዲገፈፍ፣ ዝርክርክነቱ እንዲስተካከል እግዚአብሔር ራሱ ብርሃን ሊሆንልን ያስፈልጋል፡፡ በፍጥረተ ዓለም መነሻ ላይ የነበሩት እነዚህ ችግሮች በፍጻሜ ዘመንም ታላቅ ችግር ሆነዋል። መልሱ ግን ብርሃናዊው ጌታ ነው።
ቃሉ፡- “… እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቅ ብርሃናትን አደረገ፤ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሰለጥን ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን፤ ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ”(ዘፍ. 1፥16) ይላል፡፡ ታላቁ ብርሃን የተባለችው ፀሐይ ናት፡፡ ከፀሐይ ግን የሚበልጥ ትልቅ ብርሃን መጥቷል፡፡ “በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ” የተባለለት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ማቴ. 4፥16)፡፡ የእርሱ ትልቅነት ከጨለማ ጋር ተወዳድሮ ሳይሆን ከብርሃናት ጋር ተነጻጽሮም ትልቅ ብርሃን ነው፡፡ የመልካሞች መልካም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ሁሉ ስለ እርሱ ይወደዳሉ፣ እርሱ ግን ስለ ራሱ ይፈቀራል፡፡

ነቢዩ ኢሳይያስ እንደተናገረው፡- “በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ” (ማቴ. 4፥16፣ ኢሳ. 9፥1-2)፡፡ “በጨለማ የተቀመጠው” አለ፡፡ በጨለማ መቆም የለም፣ ጨለማ እስረኛ አድርጎ ያስቀምጣል፡፡ ብርሃን ሲበራ ብቻ ጉዞ ይጀመራል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወታችን መብራት ሲሆን አዲስ ራእይ፣ አዲስ አስተሳሰብ ይገኛል፡፡ ሰው ምን ላድርግ? የሚለው ክርስቶስን ሲያገኝ ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በብርሃንነት በተገለጠባቸው ከተሞችና ትውልዶች የተቃለለው ጨለማ ምንድነው? ስንል፡-
1.     የበታችነት ስቃይ
2.    ሁሉን ላስደስት የሚል ፍርሃት
3.    ለስህተት መቃረብ
4.    የበጎ ነገር ተመልካች መሆን
5.    የተቀላቀለ ማንነት ነው፡፡ እነዚህ የሕይወት ጨለማዎች ናቸው፡፡
የበታችነት ስቃይ
የበታችነት ስቃይ አለው፡፡ በበታችነት ስሜት የሚንገላቱ ሰዎች ራሳቸውን መቀበል አቅቷቸው የሚሰቃዩ ናቸው፡፡ ራሳቸውን ከሌሎች ጋር እያስተያዩ ከሰዎች እኩል መቆም የማይችሉ መስሎ ይሰማቸዋል፡፡ በሥነ ምግባር አጊጠው የተወለዱበትን ዘር እያሰቡ ይሸማቀቃሉ። ትልቅ ቁምነገር እንጂ ትልቅ ዘር የለም። ያማረ ሙያ እያላቸው ኰሌጅ ስላልገቡ ይሸማቀቃሉ፡፡ አለመማርም መብት መሆኑን ይዘነጋሉ፡፡ እነርሱ የሚችሉትን የተማሩ የሚባሉ እንደማይችሉት ይዘነጋሉ፡፡ በዚህ የበታችነት ስሜት ቤተሰባቸውን፣ ትዳራቸውን፣ ከሁሉ በላይ ራሳቸውን ያሰቃያሉ፡፡ ለእግዚአብሔርም አይመቹም፡፡ ሁልጊዜ ያማርሩታል፣ ሁልጊዜ ያሙታል፡፡ ያላቸውን ነገር ባለማወቃቸው በድህነት ስሜት ይንገላታሉ፡፡ ከማንም ይልቅ ቅንና መልካም ሰዎች ቢሆኑም ዋጋ የለኝም በሚል አስተሳሰብ ስለተያዙ እየሸሹ ይኖራሉ፡፡ ራሳቸውን ለመርሳትና ደፋር ለመሆንም በሱስ ውስጥ ይዘፈቃሉ፡፡ ሞኝነት ስለሚያጠቃቸውም ራሳቸውን በአጉል ነገር ውስጥ በመክተት ቤተሰባቸውንና ትዳራቸውን የተበቀሉ ይመስላቸዋል፡፡ በምንም ነገር የማይረኩ ስለሆኑ አጠገባቸው ላሉ ሰዎች ትልቅ ፈተና ናቸው፡፡
በዚህ ስሜት የሚንገላቱ ሰዎች ስሜቱ ራሱ ስላደረባቸው ያላቸውን ነገር እንኳ በዜሮ እያባዙ የለኝም በማለት ያለቅሳሉ፡፡ ቤተሰብ እያላቸው ቤተሰባቸው ያገለላቸው፣ አንዳንዴም ከሌላ የተወለዱ ሆነው ራሳቸው ይሰማቸዋል፡፡ በሕይወት ላይ የበታችነት መንፈስ ትልቅ ስቃይና ጨለማ ነው፡፡ በዚህ ጨለማ የተያዙ ቀጣዩ ቀን፣ በዙሪያቸውና በእጃቸው ያለው የከበረ ነገር ስለማይታያቸው መከረኞች ናቸው፡፡ ይህንን ጨለማ ሊያቃልል የሚችል ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡
ራስን መቀበል አለመቻል ከባድ ነው፡፡ ብዙዎች ያለጊዜያቸው ይህችን ዓለም የተሰናበቱበት ጨለማ ነው፡፡ ራሳችንን የምንቀበለው ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወታችን ላይ ሲያበራ ብቻ ነው፡፡ በመንፈሳዊው ዓለም ከማንም እበልጣለሁ ማለት ኃጢአት እንደሆነ ሁሉ ከሁሉም አንሳለሁ የሚለው የበታችነት ስሜትም ኃጢአት ነው፡፡ የበታችነት ስሜትና ትሕትና ፍጹም ልዩነት አላቸው፡፡ ትሕትና ሁሉም ነገር እያለን እንደሌለን መቁጠር፣ ያለንን ነገር ለሌሎች በፍቅር ማበርከት ነው፡፡ የበታችነት ስሜት ግን ራስንና ሌሎችን አጨልሞ ማየት ነው፡፡ መስጠትም መቀበልም አለመቻል ነው፡፡
ሁሉን ላስደስት የሚል ፍርሃት
ሁሉን ማስደሰት ኃጢአት አይደለም፡፡ ሁሉን ማስደሰት ግን አይቻልም፡፡ በዚህ ጨለማ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሰው ፊቱን ያጠቆረባቸው ቀን ፀሐይ የጨለመች ያህል መስሎ ይሰማቸዋል፣ ሰው የተቆጣቸው ቀን የመሬት መንቀጥቀጥ የመጣ ያህል ይጨነቃሉ፡፡ ስለዚህ ማንንም ላለማስቀየም የሁሉን ይሁንታ ለማግኘት ይፈልጋሉ፡፡
ሁሉን ላስደስት የሚሉ ሰዎች የረባ እንቅልፍ እንኳ የላቸውም፡፡ ተቀምጠው ቆመዋል፡፡ ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነው የሚሮጡላቸው ሰዎች ስሜታቸውን ስለማይረዱላቸው ጉልበታቸውን ያለውለታ ይጨርሳሉ፡፡ ላላመኑበት ነገር ድምፅ ይሰጣሉ፡፡ እምቢ ማለትም መልስ መሆኑን አያውቁም፡፡ ለሁሉ መሳቅ፣ ለሁሉ ማልቀስ ግዴታ ሆኖ ይሰማቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች በቁማቸው ተኰንነው የሚኖሩ የጨለማ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ አሳባቸው ተቃውሞ እንዳይገጥመው እንቅልፍ ያጣሉ፡፡ ባልንጀሮቻቸው ቢከዷቸው የሚሞቱ መስሎ ይሰማቸዋል፡፡ ችግሮች ተነሥተው መፍትሔ ከመፈለግ ችግሮቹ ተዘግተው በሰላም መኖርን ይመኛሉ፡፡ ችግሩ ፈንድቶ የወጣ ቀን በሀዘን ይጎዳሉ፡፡
የምንኖረው ለእግዚአብሔር ክብር እንጂ ሰዎችን ለማስደሰት አይደለም፡፡ እግዚአብሔርን ለማስደሰት ስንኖር የእግዚአብሔር የሆነው ሁሉ ይደሰትብናል፡፡ የመኖሪያ ፈቃዳችን የሚታደሰው በሰዎች አይደለም፡፡ የሚያኖረን እግዚአብሔር ነው፡፡ የዚህች ዓለም ባለቤትም ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ ሰጥቶን የሚከለክለን እርሱ ከልክሎንም የሚሰጠን ማንም የለም፡፡ ይህ ብርሃን የሚበራልን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወታችን ገዢ ሲሆን ብቻ ነው፡፡
ለስህተት መቃረብ
ሁሉም ስህተት አቅም ማጣት፣ የባሕርይ፣ የድካም ውጤት አይደለም፡፡ አንዳንድ ስህተቶች ከዕውቀት ማነስም ይፈጠራሉ፡፡ ይልቁንም ብዙ ሰዎች ለስህተት ቅርብ ሆነው ይኖራሉ፡፡ ቤታቸውን በባሕሩ ዳርቻ የመሠረቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ቅድስናን ይፈልጉ ይሆናል። ፍላጎት ግን ብቻውን ቅድስናን አያመጣም፡፡ ቅድስና ውሳኔ ይጠይቃል። ቅድስና ዋጋ ያስከፍላል፡፡ አቤል ቅድስናን ሲፈልግ ቅዱስ ባልሆነው ቃየን አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ ዮሴፍ አላመነዝርም በማለቱ ወኅኒ ወርዷል፡፡ ቅድስና ተጋድሎ አለው/ዕብ. 12፡4/፡፡
ለስህተት ቅርብ ሆነው የሚኖሩ ሰዎች ግን ሁሉን አስማምተው መጓዝን ይፈልጋሉ፡፡ ክፉ ባልንጀርነታቸውን መተው አይፈልጉም፡፡ ዛሬ እገሌን ካላገኘሁ አልሰክርም እግዚአብሔር እንዳልጠጣ ከፈለገ እገሌን ይያዝልኝ የሚል ድራማ ይሠራሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ሁኔታው እንዲመራቸው እንጂ እውነቱ እንዲመራቸው አይፈልጉም፡፡ ሁኔታ ተለዋዋጭ ነው፡፡ እውነት ግን ቋሚ መርህ ነው፡፡
“የሚያዳልጡ ስፍራዎች ጎበዞችን ሳይቀር ይጥላሉ” ይባላል፡፡ ወደ እውነተኛ የሕይወት መስመር ለመምጣትና በቅድስና ኑሮ ለመግፋት ከክፉ ባልንጀሮች፣ ከክፉ ንባቦች፣ ከክፉ ቦታዎች መራቅ ይገባል፡፡ ይህንን ውሳኔ የምንወስነው በብርሃን ነው። ትርፉንና ኪሣራውን የሚያሳየን የማስተዋል ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር ሲሆን የሚበጀንን የመምረጥ አቅም እናገኛለን፡፡ አሊያ ለራሳችን ጠላት እንደሆንን እንቀጥላለን፡፡
የበጎ ነገር ተመልካች መሆን
በጎ ሥራ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው፡፡ ሁሉም ዛፍ ብርቱካን ያፍራ አይባልም፣ የብርቱካን ዛፍ ግን ብርቱካን ማፍራት ይገባዋል፡፡ ውበቱም፣ ተፈላጊነቱም ያለው በፍሬው ላይ ነው፡፡ ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት የጸጋ ስጦታ ይኑረው አይባልም፡፡ ክርስቲያን ግን የጽድቅ ተክል ነውና፣ የጽድቅ ፍሬ ይጠበቅበታል፡፡ የበጎ ነገር ተመልካች መሆን ከበጎ ነገር ማዶ መኖር እንኳን ለክርስቲያን በሰው አቋም ለተገኘም የማይገባ ነገር ነው፡፡
እውነተኛ ቅድስና ክፉ አለማድረግ ብቻ አይደለም፣ በጎ ማድረግም ነው፡፡ ክፉ አለማድረግ ከግብፅ መውጣት ነው፣ መልካም ማድረግ ግን ከነዓን መግባት ነው፡፡ ቅድስና የሚሟላው በበጎ ሥራም ነው፡፡ ክፉ አለማድረግ ጨዋነት ነው፣ መልካም ማድረግ መንፈሳዊነት ነው፡፡ ክፉ አለማድረግ መልካም ዜግነት ነው፣ መልካም ማድረግ ግን ክርስቲያንነት ነው፡፡ ይልቁንም ክርስቲያኖች ምቹ ቦታን የሚፈጥሩ እንጂ ምቹ ቦታን የሚጠብቁ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ከመልካም ነገር ጋር መተባበር፣ መልካም ነገርን በማድረግም መገለጥ ይጠበቅብናል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ነው፡፡ ሕይወትም ፍሬ ነው፡፡ ከጨዋነት ፍልስፍና ማንንም ላለመንካት ከመጠንቀቅ ርእዮተ ዓለም ሌሎችን በበረከት ወደ መንካት ክርስትና እንድንመጣ የክርስቶስ ብርሃን ያስፈልገናል፡፡
የተቀላቀለ ማንነት
ከጨለማ መገለጫዎች አንዱ የተቀላቀለ ማንነት ነው። ድፍርስ ቡና የሚጠጣው ሲሰክን ነው። የተቀላቀለ ማንነትም ድፍርስ በመሆኑ እርካታ የለውም። ሕይወት በዓላማ የተገኘች ስትሆን የምትቀጥለውም በውሳኔ ነው። ሕይወት የምትከብረው ፍጻሜዋ እግዚአብሔር ሲሆን ብቻ ነው። እግዚአብሔር የሚረዳው አሳባችንን ሳይሆን ውሳኔአችንን ነው። ያለ ውሳኔ በዚህ ዓለም ላይ መንቀዋለል ይቻላል፣ መጓዝ ግን በፍጹም አይቻልም። ብዙ ሰዎች የድንበር ነዋሪዎች ናቸው። የሁለት አገር ቋንቋ ይናገራሉ፣ የሁለት አገር ዜግነት ይቀበላሉ። ላሸነፈው እየዘፈኑ ይኖራሉ። አድራሻቸውን መናገር እስኪያቅት እንደ ጦጣ እየዘለሉ የሚኖሩ ናቸው። በመጨረሻ ሁሉም ነገር ግራ ያጋባቸውና ሕይወትን መጥላት ይጀምራሉ። ሕይወት በራሷ ክፉ አይደለችም። ውሳኔ ከሌለን ግን ሕይወት ኃይል ያጥራታል።
ብዙ ነገሮች የተቀላቀሉባቸው ሰዎች አሉ። ይህንን የተምታታ ማንነት ወደ አንድ አቅጣጫ ለማምጣት ቢያስቡም አቅም ያጥራቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን ሲሆንላቸው ግን ወደ ጠራ ማንነት ይደርሳሉ። እምነት የውሳኔ ኃይል ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን በሕይወት ላይ ለአስደናቂ ውሳኔ መድረስ ነው። በውሳኔ የተከተልነው ጌታ ወሳኞች ያደርገናል። የእግዚአብሔር ሰው እያባበለ የሚጓዝ አይደለም። ከእውነት መንገድ የሚያደናቅፈው ከሆነ ሥልጣንን እንዲሁም ሀብትን ለመተውም ቆራጥ ነው። እየዘፈኑ አንድ መዝሙር ጣል የሚያደርጉ የተቀላቀለ ማንነት ያላቸው ሰዎች ናቸው። በውስጣቸው እውነት እየደወለች ኃጢአትን በልበ ሙሉነት መፈጸም አልቻሉም። የእግዚአብሔርን መንግሥት ይፈልጋሉ እንዲሁም ዝናንና የሰውን ከበሬታ ይሻሉ። ፖለቲካና ሃይማኖት የተቀላቀለባቸው፣ መስቀልና የጦር መሣሪያ የጨበጡ ብዙዎች ናቸው። መወሰን ብቻ ከእግዚአብሔር ጋር ያገናኛል። እግዚአብሔር ልፍስፍስ ልጆች የሉትም። ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ሰማዕታት መታወቂያቸው ቆራጥነት ነው። የተኛው ሰው ከእንቅልፉ የሚነቃው ብርሃን ሲበራ ነው። የእንቅልፍን ዘመን የሚያቋርጠው ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ወገኖቼ ወደ እርሱ በእምነትና በንስሐ እንቅረብ። እርሱም መንገዱን ይመራናል።
                                                     ይቀጥላል

ያጋሩ

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።