የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ብርቱ ሰልፍ

“በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን ? ወራቱም እንደ ምንደኛ ወራት አይደለምን ?” ኢዮብ. 7 ፡ 1 ።

ነገር ነገርን እያነሣው የፍቅር ወሬ ወደ ጠብ የሚቀየርባት ፣ አዲሱ ቂም የቆየውን በቀል የሚቀሰቅስባት ሕይወት በምድር ላይ ብርቱ ሰልፍ ናት ። ይቅር ለማለት የሚታገሉባት ፣ ይቅር ያሉትን መልሰው የሚያቄሙባት ፣ ከባዱ ሰው የሚቀልባት ፣ ትልቁ ትንሽ የሚሆንባት ሕይወት በምድር ላይ ብርቱ ውጣ-ውረድ ናት ። “አገሩ ነው ችግሩ አገር እንለውጥ” እያሉ ሲያወጉ ቆይተው መልሰው “ዘመኑ ነው የሚባልባት” የራስን ችግር ለአገሩና ለዘመኑ እየሰጡ የሚቃዡባት ሕይወት በምድር ላይ ብርቱ ጥያቄ ናት ። በሽተኛው የሚያክምባት ፣ ወንጀለኛው ዳኛ የሚሆንባት ፣ መሃይም እየለፈለፈ ምሁር ጸጥ የሚልባት ሕይወት በምድር ላይ ብርቱ ወጀብ ናት ። ያጠኑት ምርምር ውሸት የሚሆንባት ፣ የናቁት ልማድ ክቡር ሁኖ የሚመጣባት ፣ ዓርብ ረቡዕ የሚገድፉባት ፣ እንደገና ጾም ጤና ነው የሚባልባት ፤ ማንም አያስፈልገኝም የሚሉባት ፣ መልሰው ያለ ሰው እንዴት እኖራለሁ? ብለው የሚያለቃቅሱባት ሕይወት በምድር ላይ ብርቱ ዕብደት ናት ። አያስፈልገኝም ብለው የሚኮሩባት ፣ የናቁትን መልሰው የሚከጅሉባት ፣ የሰሙትን የሚዘነጉባት ፣ ያልሰሙትን እንደ ሰሙ አድርገው የሚጣሉባት ሕይወት በምድር ላይ ብርቱ ስካር ናት ። መቆም ያልቻሉ ስለ አቋቋም የሚያሰለጥኑባት ፣ መራመድ ያልጀመሩ ስለ ግብ የሚጨፍሩባት ሕይወት በምድር ላይ ብርቱ ውጥን ናት ።

ነፍስ እያጠፉ ስለ እጽዋት የሚጨነቁባት ፣ የሰው ደም እንደ ቀይ ጽጌረዳ የሚታይባት ፣ ለራስ ሕይወት እየሰሰቱ “ያለ ደም ስርየት የለም” እያሉ በሌላው አንገት የሚፈርዱባት ሕይወት በምድር ላይ ፍርድ አልባ ናት ። ከራስና ከሰው አመል ጋር ትግል ፣ ከንጋትና ከምሽት ጋር ትግል ፣ ከደመናና ከፀሐይ ትኩሳት ጋር ትግል ፣ ከኑሮና ከሕመም ጋር ትግል ፣ ከረሀብና ከጥጋብ ጋር ትግል ያለባት ሕይወት በምድር ላይ መልከ ብዙ ናት ። የበለጸጉ በድሀ እንቅልፍ የሚቀኑባት ፣ ድሆች በባለጠጎች ኑሮ የሚመሰጡባት ፣ ምንም የሌላቸው የሌሎችን ገቢ የሚቆጥሩባት ፣ ያላቸው አልበቃ እያላቸው የሚጨነቁባት ፣ ሚሊየን የቸገረውና አንድ ብር የቸገረው እኩል የሚያምጡባት ሕይወት በምድር ላይ ብርቱ የቤት ሥራ ናት ።

ሕይወት በሰማይ ብርቱ ዕረፍት ናት ። ከቻሉ አለመቻል የሌለባት ፣ ከታመኑ ክዳት የማያገኛት ፣ ሥጋ የማይሟገትባት ፣ የሰዎች ክፋት የማይደርስባት ሕይወት በሰማይ ብርቱ ተድላ ናት ። የምድር መከራ በሰማይ እንኳን አለተከተለን ፤ የሰማይ ደስታም በሙላት እንኳን በምድር ላይ አለፈሰሰ ። አማኑኤል ሆይ! ይህን ያመጣጠነ እጅህ ቡሩክ ነው ። ረሀቡንም ጥጋቡንም እንችለው ዘንድ በትዕግሥት ባርከን ። ብርሃን በሚረጨው እጅህ ለዘላለሙ አሜን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 20 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ