የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ብቻዬን አይደለሁም

“ነገር ግን አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም።” ዮሐ. 16፡32 ።

እግዚአብሔር ተናገረ፡-

ልጄ ሆይ፣ የመሸበትን እንግዳ ማን ያሳድራል  ቀን ሲስቁ የቆዩ ፣ በር ከፍተው ፣ ወንበር ዘርግተው ያጫወቱ ፣ አትሂዱ ብለው የተማጸኑ ፣ ዕድሜ ማራዘሚያ የሚበላ የሚጠጣ ደጋግመው ያቀረቡ ሲመሽ በልባቸው ውጡ ይላሉ ። “የገና ጀንበር ቶሎ ይመሻል” እያሉ አስወጥቶ በር ለመቆለፍ ይቸኩላሉ ። የምሽት ወዳጅ እኔ ብቻ ነኝ ። ጨለማ ቢያስፈራም ሰው የሚተኛው በጨለማ ነው ። በአስፈሪው ጨለማ እንቅልፍ የምሰጥ ፣ በመዓቱ የምባርክ እኔ ነኝ ። ትላንት የወደደ ዛሬ ላይወድ ፣ ትላንት የተለመነ ዛሬ ሊጨክን ፣ ትላንት የመሰከረ ዛሬ ሊክድ ይችላል ። መውደዴን የማከብር ፣ መለመንን የምሻ ፣ ቅዱስ ብዬ ርኵስ የማልል እኔ ነኝ ። የወጣሁ ፀሐይ ይጠልቃል ፣ የጠለቀውም ጀንበር መልሶ ይወጣል ። እኔ ግን ካየሁ የማልጨፍን ፣ ካበራሁ የማልጨልም ፣ ከያዝሁ የማልጥል ነኝ ።

ልጄ ሆይ ፣
ይህ ሁሉ የልብ ማመንታት ፣ ይህ ሁሉ የማያልቅ የተኩስ ወረዳ ምንድነው  ወዳጅህ ምሎ ቢከዳህ ፣ “እግዜር ምስክሬ ነው አላውቀውም” ቢልህ ምዬ የወደድኩህ ፣ “መሐለ እግዚአብሔር ለዳዊት በጽድቅ ፤ ወኢይኔስሕ” የተባለልኝ እኔ ነኝ ። /መዝ. 131፡11/ ፍቅሬ ጸጸት የለበትም ። መሐላዬም የጸና ነው ። ቀኔ አይደለም ብለህ መሸማቀቅህ ትክክል አይደለም ። አንዳንዶች በቀን ፣ ሌሎች በዕድል ፣ ሌሎችም በጥንቆላ ፣ ጥቂቶችም ባጋጣሚ ቸርነት ያምናሉ ። ሰጪና ነሺ ግን እኔ ነኝ ። ቀን ሁሉ የእኔ ሎሌ ነውና ቀኔ ዛሬ ነው በል ። ወደ ወጣህበት ቤት መመለስ ብታፍር ፣ ወደተዳርክበት ቤት ፈት ሁነህ መገስገስ ቢያሸማቅቅህ ፣ ወልደህ ሌጣ ፣ አግብተህ ብቸኛ ብትሆንም እኔ ግን የማልተው እግዚአብሔር ነኝ ። ስለ አንተ ያለኝ አሳብ ከዓለማትና ከዘመናት ፣ ከዓመታትና ከጽርሐ አርያም በላይ ነው ። ስለ አንተ ፣ አንተ የምትለው ብዙ ቢሆንም እርሱ ላይ እኔ ባለሥልጣኑ አልፈርምበትም ። ሰዎች ያሉህም እርሱ ያንተ መልክ አይደለም ። መልክህ በፍቅር ልቤ ተሰውሯልና አትፍራ ። ተናግረህ የተናገርከውን የምታዳምጥ ፣ ቃላት ቆጥረህ አውርተህም ምን አስቀየምኩ የምትል ፣ በእብዶች የምትሰቀቅ ፣ እንዳሻቸው በሚራመዱ የምትገረም ፣ እኔ ነኝ የተሳሳትኩት ወይስ ሌላው እያልክ የምታመነታ ፣ መንገድ የጠፋህ ደንባራ መሆንህን አውቄአለሁ ። ትላንት ያየኸው ፍቅር የዛሬውን ወረት ለመቀበል ፣ ትላንት ያየኸው መልካም ሰው የዛሬውን እሾኽ እንዳትለምድ አድርጎሃል ። ግራ ስትጋባ ቀኙን ላሳይህ ሁልጊዜ አጠገብ ነኝ ።

ልጄ ሆይ ፣
ስሜ ቢጠራ አይታወቅ ፣ ስሜ ለእኔም የጠፋኝ ፣ ስሜ በወረቀት ላይ ብቻ የቀረ ፣ እንደ መጣሁ ልሄድ ነው ብለህ የምትፈራ ብትሆንም ባላለቀ ተስፋ ላስደስተህ መጥቻለሁና ደስ ይበልህ ። የመከራ ጽዋህን ወስጄ የደስታ ዘይት ልቀባህ ቆርጫለሁና የእኔ ሆይ አትደናገር ። ራስህን ፣ ደግነትህን ፣ መንገድህን ለማስተርጎም አትሻ ። በምናገርበት ዘመን ሳትሰማ ፣ በዝምታ ዘመን ሰማኸኝ ። እኔ በዝምታም እሠራለሁ ። ዓለም ግን በወሬም አይሠራም ። ስመክርህ ያልገባህን ስትኖረው ተረዳኸው ። ስጠራህ ሳትሰማ ስትጎሰም አቤት አልከኝ ። መምጣትህ እንጂ እንዴት መምጣትህ አያሳስበኝም ። ከትላንት ታሪክህ ፣ የነገ ተስፋህ ብቻ ያሳስበኛል ።

ልጄ ሆይ ፣
አባብለህም የሚቀየምህ ፣ ወደህም የሚጠላህ ሲጠፋ ተናዳፊ እንደሆንክ ፣ የተሰማህንም ያለ ማጥለያ ለማውራት እንደቆረጥህ አውቃለሁ ። መጠየቅን እንደ ጠላህ ፣ ማስረዳትም እንደ ደከመህ አይቻለሁ ። ቅንነትህም ጭካኔህም ሁለቱም ደጋፊ እንዳጣ አውቄአለሁ ። በእግዚአብሔር ተፈጥረህ ያለ እግዚአብሔር አትኑር ። ወደ መጣህበት ልትመለስ ዘመኑ ሩቅ አይደለም ። እየወደዱህ ትሞታለህ ፣ እየጠሉህ ትኖራለህ ። ገንዘብም የመኖር ዋስትና አይሆንም ። ካንተ ጋር ነኝ ያሉት ከጠላት ጋር ይሆናሉ ። ልብህን የሰጠሃቸው ድንጋይ ይወረውራሉ ። የውስጤ ያልካቸው የውስጥ በሽታ ይሆናሉ ። ሰማይም ሊጠቁር ፣ ምድርም ልትከዳህ ፣ ቀትርም ሊጨልም ፣ ወዳጅም ሊበተን ፣ ያመሰገነም ሊረግም ይችላል ። እኔ ግን ካንተ ጋር ነኝና ብቻህን አይደለህም ።

ልጄ ሆይ፣
የሰውን ሥጋ ለብሼ ፣ በድንግል እናቴ ሥጋ ለባሽን ተዛምጄ መጥቻለሁ ። ደቀ መዝሙር ሁሉ ለምኖ መምህሩን ያበላል ፣ እኔ ግን ደቀ መዛሙርቴን ሁለት ዓሣና አምስት እንጀራ አበርክቼ ያበላሁ ነኝ ። መምህር ሁሉ ይፈለጋል ፣ እኔ ግን ጥብርያዶስ ድረስ ሄጄ የፈለግሁ ነኝ ። መምህር ሁሉ እግሩን ያጥቡታል ፣ እኔ ግን የደቀ መዛሙርቴን እግር አጥቤአለሁ ። መምህር ሁሉ ተማሪዎቹ ቀድመው ይሞቱለታል ፣ እኔ ግን ሞቼላቸዋለሁ ። መምህር በተማሪው ስሙ ይጠራል ። እኔ ግን ለደቀ መዛሙርቴ ስሜን ሰጥቻቸዋለሁ ። በወልድ ውሉድ ፣ በክርስቶስ ክርስቲያን ፣ በመንፈስ ቅዱስ መንፈሳውያን ተብለዋል ። እነዚህ ሁሉ ወዳጆቼ ግን ሐሙስ ምሽት ብቻዬን ትተውኝ ሂደዋል ። ስነሣ ግን ፈለኳቸው ። አንተም ስትነሣ ለገደሉህ ይቅርታ አድርግ ። እኔ ከካስኩ ሰውን መቀየም ከንቱ ነው ።

ምእመኑ መለሰ፡-

ጌታዬ ሆይ ፣ የተደናገረውን መንገድ የምትመራ ፣ ሕመምተኛውንና አስታማሚውን አብረህ የምትፈውስ ፣ በመሪዎች ጀርባ የምትመራ ፣ ማንም ሳይጠቁምህ ድሀን የምትረዳ ፣ ለችግረኛ ያለ ማስታወቂያ የምትሰጥ አምላክ ነህ ። ሁሉም ነገር ጥያቄ ሲሆንብኝ የሁሉም ነገር መልሴ አንተ ነህ ። ሰባራ በሰንጣራ በሚስቅበት ዓለም አዝነህ ሁላችንን ትሰበስበናለህ ። በተሻለ ደግነት ሳይሆን በተሻለ ክፋት ስንጽናና ታርመናለህ ። ልበ ሙሉ ሆኜ ለመበደል አምላክ የለም አልኩኝ ። ሰነፍ ከሚሠራ ምነው ጉንድሽ በሆንኩኝ ይላል ። እግዚአብሔር የለም ያልኩህ ለመታዘዝ ሰንፌ ነው ። ሱሰኛ ከሀዲ ነው ። ከሕሊና ጸጸት የዳንኩ እየመሰለኝም አባቶቼም እንደ እኔ ናቸው እላለሁ ። ራሴ ራሴን ሊሰናበተው ሲል ወዴት ነህ እልሃለሁ ። አለሁ ትለኛለህ ። እንደ ካድሁህ ያልካድከኝ ፣ ጀርባዬን ስሰጥህ ፊትህን ያሳየኸኝ አንተ ነህ ። መስጠም ስጀምር ፣ የማየው ሲሰወር ፣ የረገጥኩት ሲከዳኝ ፣ የምጨብጠው ምሰሶ ሲሰወርብኝ ጌታ ሆይ አድነኝ እልሃለሁ ። የጠራኸኝ አንተ ዓይንህን ከእኔ አታነሣም ። ያስጀመርከኝ ልታስፈጽመኝ ትተጋለህ ።

አምላኬ ሆይ ፣ የክፍል ትምህርት ደስ ይላል ። ፀሐይና ሩጫ የለውም ። ተቀምጦ ዓለምን ማሰስ ፣ ወንበር ተደግፎ መብረር ነው ። መምህሩ ካፒቴን ተማሪው የአሳብ ተሳፋሪ ሆነው የሚገሰግሱበት ነው ። የመስክ ትምህርት ግን ያወቅሁ የመሰለኝን እንዳላወቅሁት ፣ ሳይገባኝ ገባኝ ያልኩህን እንዳፍርበት ያደርገኛል ። ካልጨለመ ከዋክብት አይፈኩም ፣ አንዳንድ ሰዎችም ያለ ፈተና አያበሩም ። ከጠባብ ክፍል አውጥተህ ፣ ሰማይን ጠፈር ፣ ምድርን ሜዳ ፣ አድማሳትን ግዛት አድርገህ ስታስተምረኝ የመስኩ ስልጠና ከበደኝ ። የተጨበጠ እውቀት አገኝ ዘንድ ለጊዜው ጨከንክብኝ ። መስቀሌ ያሸሻቸውን ትተህ ፣ የመስቀል ወዳጆች ሰጠኸኝ ።

አዎን ጌታዬ ፣
ቀኑ ቢሻል ቢከፋ ፣ ዘመኑ ቢሮጥ ቢመጣ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ብቻዬን አይደለሁም ። የተሰበሰበ ቢበተን ፣ የተካበ ቢናድ ፣ ፍርድ ከፍርድ አደባባይ ቢታጣ ፣ የነገው ስጋት ከዛሬው ችግር ቢከፋ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ብቻዬን አይደለሁም ። ትንተናው ቢያስፈራ ፣ ኢኮኖሚው ቢመታ ፣ የሰው ዘር በስምምነት ሰውነቱን ቢከዳ ፤ ኪዳን ቢፈርስ ፣ መሐላ ቢታጠፍ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ብቻዬን አይደለሁም ። የሠራሁት ቢፈርስ ፣ ያሳደኩት እሾህ ሁኖ ቢወጋኝ ፣ ያከበርኩት ዝቅ ሊያደርገኝ ሽቅብ ቁልቁል ቢል አንተ ከእኔ ጋር ነህና ብቻዬን አይደለሁም ። የለመንኩት ባይመጣ ፣ የጸለይኩበት መልሱ ቢዘገይ መላሹ ጌታ ግን አንተ ከእኔ ጋር ነህና ብቻዬን አይደለሁም ። የማይሸበር ልብ ፣ የማይዛነፍ እግር ፣ የተፈተነ ሕይወት ስጠኝ ። ለዘላለሙ አሜን ። የሚሰማህ አሜን ይበል ። ዕድሌ ተወሰደብኝ የሚል ይህም ዕድሉ ነውና አሜን ይበልህ ።

የፍቅር ጥሪ /2
ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኮንን

https://t.me/Nolawii

እባክዎ ይህን ቻናል ይቀላቀሉ፣  ለሌሎች ወገኖቻችንም ያስተዋውቁ

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ