የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ብቻ ወጣ ብለህ ና ! ክፍል 1

አገርህን መውደድህ ፣ አገርህን መጠበቅህ ፣ የአገር መከራ ተካፋይ መሆንህ ዋጋ አይሰጠውም ። ብቻ ወጣ ብለህ ና ፣ ዲያስፖራ ተብለህ መንግሥታዊ አቀባበል ታገኛለህ ። በቤተ ክርስቲያን ጥላ ተዘርግቶልህ የክብር ወንበር ላይ ትፈናጠጣለህ ።  አባም ብትሆን መምህር ወደ ገዳም ፣ ወደ ደብር ሳይሆን ወደ ቅርቡ ወደ ሱዳን ፣ ወደ ጦርነቱ አገር ደርሰህ ና ። እርሳቸው እኮ ሁሉን ትተው የመጡ ናቸው ይሉሃል ። በምንኵስና ስምህ እንደ ተለወጠልህ ወጣ ብለህ ስትመጣ ከጀርመን ከሆነ “አባ ጀርመን” ፣ ከቅርቡ ከሆነ “አባ ኬንያ” ትባላለህ ። አንተም እንዲህ ብለው ሲጠሩህ በብርዱ ይሞቅሃል ።

ብቻ ወጣ ብለህ ና ! እንዳንተ ጋምቤላ የሄደ ሰው በአራት ዓመቱ ቢመጣ እርሱን የሚጋብዙት የሉም ፤ የአንተ የግብዣ ፕሮግራም ግን አንድ ወር ሙሉ ተይዟል ፤ የሚጋብዙት ፍቅርን ፣ የሚጋብዙት ናፍቆትን ሳይሆን የመጣህበትን አገር ነው ። ብቻ ወጣ ብለህ ና ፣ ያወቅኸው ጠፍቶህ ሳለ ፣ ዶክተር ሆኛለሁ ብትል ያምኑሃል ። ለነገሩ የግሪክንና የአውሮፓን ፎቅ ማየት በራሱ ዶክትሬት ያሰጣል እያሉ ስንቱን ባለ ወረቀት አድርገውት ሲያታግሉን ኖረዋል ። የምመክርህ ወጣ ብለህ ና ፤ ሰዎች ሳይጠጡ ሰክረው ፣ ሳይቅሙ ነቅተው አንተ እኮ ይሉሃል ።

ወጣ ብለህ ና ፤ አማርኛ ሲጠፋህ እንደ ክብር ይቆጠርልሃል ። እዚህ ሰዋስዉ አልጠበቀም ተብሎ ስንቱ ከመድረክ ይባረራል ፣ አንተ ግን በአዛጦናዊ ቋንቋ በድብልቅልቁ ሁሉ ፈገግ ብሎ እንደ ኮልታፋ ሕፃን ይሰማሃል ። ወዳጄ ወጣ ብል ና ! እኔም በአገሬ ስላለሁ አትሰማኝም ። የአገር ምክር አይሰማምና ። የአገር ልጅ ታረቁ ሲል ባንዳ ነው ፣ የውጩ ታረቁ ሲል ብእሴ ሰላም ነው።

ወጣ ሳንል ቀርተን ስም ተሰጥቶን ፣ መናፍቅ ተብለን እንወገዛለን ። አገሪቱ ደርሶ ለመጣ እንጂ ለነዋሪው አትሆንምና ወጣ ብለህ ና ። ወጣ ብለህ ስትመጣ ዲያስፖራ መንደር ተብሎ መሬት ይሰጥሃል ። አገሩን የጠበቀው ድሀ የጨረቃ ቤት ተብሎ ይፈርስበታል ። ወጣ ብለህ ስትመጣ አገርህ ላንተ የሚሆን ሀብት አታጣም ። አንድ ዶላር አልሰጥም ብለህ ማንም አይቀየምህም ፣ እኔ ሕይወቴን ብሰጥ ማንም አይምረኝም ። ወጣ ብለህ ስትናገር ሁሉ ይሰማሃል ። አንዳንዴ ሰልፍ የምትወጣው ጭንቀትህን ፣ የቢል ጣጣህን ለመርሳት መሆኑን ማንም አያውቀውምና አክቲቪስት ብሎ ሁሉ ያወድስሃል ። ኧረ ወጣ ብለህ “ስንታገል ነበር” ብለህ ስታወራ ያጨበጭቡልሃል ። መድረክ ይለቁልሃል ። የድሀ ምክር አትሰማም እንጂ ወጣ ብለህ ና ።

ከቀሃ ወንዝ ማዶ ግጥም ብትገጥም ማንም ከቁብ አይቆጥርህም ፤ ከእንትን ወንዝ ማዶ ብለህ የፈረንጅን ወንዝ ስትጠቅስ ሁሉ እንደ ጋዜጠኛ ይስልሃል ። ወንዞች ለሚያያቸው ሰው የጋዜጠኝነት የምስክር ወረቀት መስጠት መጀመራቸውን የሰማሁት በቅርብ ነው ። ከጋምቤላው የባሮ ወንዝ ማዶ ቅኔ ብትቀኝ ማንም አይሰማህም ። ከፈረንጅ ወንዝ ማዶ ብቸኝነት ተሰምቶህ ስትቀመጥ ግን የዓለም ሰብአዊ መብት ተሟጋች ትባላለህ ። በአገርህ ሺህ መጽሐፍ ብትጽፍ የሚገዛህ ጠፍቶ በክረምት እሳት እያነደድህ ትሞቀዋለህ ። ወጣ ብለህ አንድ የሞኝ ንግግር ስትናገር ሊቅ ትባላለህ ። ስትሳደብ የአገሩ ቅንዓት በልቶት ነው ተብሎ ይታረምልሃል ። ብቻ ወጣ በል ፣ ደምህ መራራ እንዳይሆን ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ተጻፈ ሚያዝያ 20 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ