የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ፓትሪያሪክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ዜና እረፍት!

ጥንታዊትና ሐዋርያዊት፣ በአፍሪካ እና በመላው ጥቁር ዓለም የነፃነት ቀንዲልና ተስፋ ተደርጋ የምትታየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከ1600 ዓመታት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጥገኝነት ከወጣች በኋላ አምስተኛ ፓትሪያሪክ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በትግራይ ሀገር የአፍሪካና የመላው ጥቁር ሕዝብ የነፃነት ፋና ደምቆና ፈክቶ በታየበት፣ የቀደሙ አባቶቻችን ዘር፣ ሃይማኖት፣ ጎሳ፣ ወንድ፣ ሴት…ወዘተ ሳይሉ ለሀገራቸው ለኢትዮጵያ ነፃነት ደማቸውን በማፍሰስ የነፃነት ታሪካችንን በክቡር ደማቸው በፃፉባት በታሪካይቷ በአድዋ ከተማ እ.ኤ.አ በ1928 ዓ.ም ነው የተወለዱት፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥንታዊ ትምህርት በአባ ገሪማ ገዳም የጀመሩት ፓትሪያሪክ አቡነ ጳውሎስ በትግራይና በአካባቢዋ በሚገኙ ገዳማትና አድባራት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ብቁ የሚያደርጋቸውን ትምህርት በሚገባ ተከታትለዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ወደ አዲስ አበባ ከመጡም በኋላ በወቅቱ የኢትዮጵያ ፓትሪያሪክ በነበሩት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ መልካም ፈቃድና እርዳታ በቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ የሥነ መለኮት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡

በመቀጠልም የከፍተኛ የሥነ መለኮት ትምህርታቸውን አሜሪካ በሚገኘው በሴንት ቭላድሚር ቲሎጂካል ሴሚናሪ የተከታተሉ ሲሆን በዛው በአሜሪካ በፕሪንስተን ቲሎጂካል ሴሚናሪ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በመስራት ተመርቀዋል፤ ይኸው የአቡነ ጳውሎስ የዶክትሬት ዲግሪ መመረቂያ የጥናት ጹሑፋቸው በአንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም አስተባባሪነት ታትሞ ለከፍተኛ የሥነ መለኮት ተቋማትና ተማሪዎችና ተመራማሪዎች ለንባብ የቀረበው ከሁለት ሳምንት በፊት እንደነበር ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ ቤ/ን ታሪክ ቤተ ክርስቲያኒቱን ካስተዳደሩ አባቶች መካከል እጅግ አነጋጋሪና አከራካሪ የነበሩ ሰው ቢሆንም በፓትሪያሪክነት ስልጣን ከመጡ ጀምሮ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንኙነቷንና ተሰሚነቷን በማሳደግ ከፍተኛ የሆነ አስተዋእፆ የነበራቸው አባት እንደነበሩ በብዙዎች ዘንድ ይነገርላቸዋል፡፡ ፓትሪያሪክ አቡነ ጳውሎስ በዓለም አቀፍ በሆኑ ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ስለ ዓለም ሰላም፣ ስለ ሴቶች መብትና የትምህርት ዕድል፣ ስለ ሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ፣ በHIV/AIDS በመሳሰሉት የዓለማችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተግዳሮቶች ላይ በአፍሪካና ዓለም አቀፍ ደረጃ ድምፃቸውን በማሰማትና የላቀ አስተዋዕፆ በማበርከት ትልቅ ድርሻ የነበራቸው፣ በተባበሩት መንግሥታት፣ በወርልድ ኢኮኖሚ ፎረም፣ በዓለም ሃይማኖቶች መሪዎች ስብሰባ ላይ በመገኘት በሚያደርጓቸው ንግግሮችና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ትልቅ ስምንና ዝናን ያተረፉ አባት ናቸው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽንም ፓትሪያሪክ አቡነ ጳውሎስ ለዓለም ስደተኞች ባደረጓቸው የላቀ እንቅስቃሴና አስተዋዕፆ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ የናሰን ሜዳሊያ እ.ኤ.አ 2000ዓ.ም ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
እ.ኤ.አ 2006 ዓ.ም የዓለም አብያተ ክርስቲያነት ኅብረት ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጣቸው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅበረት የሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪ የሆነው አሌክሳንደር ብሎፖስኪይ ባደርገላቸው ቃለ መጠይቅ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅበረት ፕሬዝዳንት እንደመሆኖ መጠን ምን መልእክት ያስተላልፋሉ ተብለው የተጠየቁት ፓትሪያሪክ አቡነ ጳውሎስ በርቱዕ አንደበታቸውና እጅግ በተካኑበት የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታቸው እንዲህ በማለት ነበር መልስ የሰጡት ፡-
As WCC president, what is your message to the churches?
I believe that we all have to be true representatives of our own churches, and that we all have to do our part to serve and contribute, through our communities, the whole world. We in the ecumenical movement are not here to make one part of the world better than the others, but, rather, we are here to serve all people.
            ፓትሪያሪክ አቡነ ጳውሎስ በቃለ መጠይቃቸው ዓላማችን በዚህ ኅበረት ውስጥ ያለነው የክርስቲያኑን ዓለምና የተወሰነ የኅብረተስብ ክፍል ብቻ ለማግልገል ሳይሆን መላውን ዓለም ለማገልገል ነው  በማለት ነበር የገለጹት፡፡ ዓለም አቀፍ የሆነ ሰብእናን የገነቡት አቡነ ጳውሎስ በሀገራችን፣ በአፍሪካ ቀንድና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምና እድገት ይሰፍን ዘንድ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ጥረትን ያደረጉ አባት ናቸው፡፡
       

በተጨማሪም ፓትሪያሪክ አቡነ ጳውሎስ ለረጅም ዘመን በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል የዓባይን ወንዝ በተመለከተ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነትና በላይኛው የአባይ ተፋሰስ ሀገሮች ከግብጽና ከሱዳን እና ከታችኛው የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት መካከል የናይልን ወንዝ የውኃ ፍጆታ ከ80 በመቶ በላይ የምትሸፍነው ኢትዮጵያ በቅረቡ በዓባይ ወንዝ ላይ የጀመረችውን የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ግንባታ አስመልክቶ በቅርቡ በቀድሞ የግብጽ ፕሬዝዳንት ሆስኒ ሙባረክ የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው በኋላ ከረጅም ዓመታት በኋላ የግብጽ አዲሱ ፕሬዝዳንት የሆኑት መሀመድ ሙርሲ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ ከተገኙ በኋላ ፓትሪያሪክ አቡነ ጳውሎስን ማነጋገረቻው ቤተ ክርስቲያኒቱ በግብጻውያን ዘንድ ያላትን ትልቅ ድርሻ አመላካች እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

በሀገራችንም ሆነ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ላቀ አስተዋዕፆና ድርሻ የነበራቸው ፓትሪያሪክ አቡነ ጳውሎስ ዜና እረፍት አሰደንጋጭ የሚያደርገው ይኸው ፓትሪያሪክ አቡነ ጳውሎስ በሀገር አቀፍ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካላቸው ትልቅ አስተዋእፆ የተነሳ ነው፡፡ በቀጣይ በፓትሪያሪክ አቡነ ጳውሎስ የሕይወት ታሪክ ዙሪያና በዜና እረፍታቸው ላይ ሰፋ ያለ ዘገባ እናቀርባለን፡፡
የአባታችንን ነፍስ እግዚአብሔር በሰላም ያሳርፍልን! 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ