የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ተማር ልጄ

“መማር የሚፈልግ ከእረኛም ይማራል ፤ መማር የማይፈልግ ከመምህሩም አይማርም፤” /ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ/

የሰው ልጆች እውቀትን በተፈጥሮ ፣ በልምድ ፣ በትምህርት ፣ በጉዳት ያገኛሉ ። እግዚአብሔር አእምሮን የፈጠረው እንድናውቅ ስለፈለገ ነው ። እውቀትን መጥላት አእምሮ የተባለው ትልቅ መሣሪያ ያለ ሥራ እንዲሆን ማድረግ ነው ። ጡንቻ ያለ ሥራ እንደሚሟሽሽ አእምሮም ያለ እውቀት እየሟሸሸ ይመጣል ። ሰዎች መልካሙን ነገር ለማወቅ ካልፈለጉ በክፉ እውቀት እየሰለጠኑ ይመጣሉ ። የመስጠትን እውቀት ያልተለማመዱ የስስትና የስርቆትን እውቀት እያጠኑ ይመጣሉ ። መልካሙን ማወቅ ክፉውን በተግባር ላለማወቅ ይረዳል ። እውቀት ተግባር የሚፈልግ ነው ። ተግባርም መነሻው እውቀት ነው ። ያለ እውቀት የሚደረግ ነገር ሦስት ነገር የለውም ። ደስታ ፣ ጥቅምና ዋጋ የለውም ። ያለ እውቀት የሚያደርጉ ሰዎች ተግባራቸው ምንም መልካም ቢሆን አይደሰቱም ። ዓይናቸውን ጨፍነው የሚተኩሱ ዒላማ የለሽ በመሆናቸውም ሌላውን አይጠቅሙም ። ጌታችን፡- “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” እንዳለ የሚያደርጉትን መልካም ነገር የማያውቁ ዋጋ አያገኙም ። ሞኝ ደግነቱም ክፋቱም ቦታ የማይሰጠው የሚያደርገውን ባለማወቁ ነው ።

እውቀት የእግዚአብሔር ብቸኛ አምላክነት ፣ የሥልጣንን አስፈላጊነት ፣ የሚመጣው ሕይወትና ፍርድ ፣ የነገ ተስፋ ፣ የፍጥረት ዘመድነት ፣ የሞራል ልዕልና ፣ ለተፈጠሩበት ዘመንና ምድር ስለሚደረገው አበርክቶ ፣ የማኅበራዊ ኑሮ ፈዋሽነት ፣ በአጋጣሚ ሳይሆን በዓላማ ስለ ተበጀው ዓለም ይተነትናል ። ቀኑን አዲስ የሚያደርገው ትላንት የማናውቀውን ዛሬ በማወቃችን ነው ። ሰው መኖሩን የሚወደው በአዲስ እውቀት ቀኑን እስከ ጀመረ ድረስ ነው ። የዓለማችን ትልልቅ ፈላስፎችና አዋቂዎች አእምሮአቸውን ከመቶ ሁለት እጅ ብቻ ተጠቅመዋል ። አእምሮ ብዙ ልናውቅበት የሚያስችል መሣሪያ ነው ። ታዲያ በዝግንና በእፍኝ እውቀት አእምሮአችን የሞላ የሚመስለን እኛ የምንገርም ነን ። እውቀት በረከትና ዕዳ ነው ። በረከትነቱ ለባለቤቱ ሲሆን ዕዳነቱ ደግሞ ያላወቁትን ሰዎች መሸከም የሚጠይቅ ነው ። በርግጥም እውቀታችንን አስፈላጊ ያደረገው የሌሎች አለማወቅ ነው ። እንጀራ የምንበላው ሌሎች የማያውቁትና የማይችሉት ነገር ስላለ ነው ። የማያውቁትን የማያከብር እውቀት አለማወቅ ነው ። ማወቅ ወደ ብርሃን መውጣት ነው ። ስናውቅ ከዚህ በፊት ዓለምን እንደምናያት አድርገን አናይም ።

እውቀት መነጽር መለወጥ ነው ። ስናውቅ በአስደናቂ ፍጥረታት መካከል እንደ ተቀመጥን ይገባናል ። በማወቅ ውስጥ ለእግዚአብሔር ምስጋና እናበዛለን ። በርግጥ ሰዎች በተለያየ መንገድ ቢያውቁም መምህር የሌለው እውቀት የሙት ልጅ ነው ። ማደግ አይችልም ። ራስ ተማሪ ፣ ራስ መምህር መሆን ከባድ ነው ። ራስ ተማሪ ራስ መምህር የሚሆን ጊዜውን ያቃጥላል ። ለእውቀቱም እርግጠኛነት አይሰማውም ። ያልተፈተነ እውቀት አደባባይ አይውልም ። መምህር እውቀትን የሚሰጥና የሚፈትን ነው ። ያወቁ የሚመስላቸው ግን ያላወቁ ሰዎች በምድር ላይ አሉ ። እውቀት ራስን በፍቅርና በቸርነት የሚገልጥ ነው ። ቃላትን ማራቀቅ ፣ አማርኛን መሰንጠቅ እውቀት አይደለም ። ለዚህ ነገረኛ ሰዎች የሚያህላቸው የለም ። ቃላትን መደርደር ቢያስከብር መንደርተኛና በቅኔ ሲወጋጉ የሚውሉ ሰዎች ክብር ያገኙ ነበር ። እውቀት ስለ መፍትሔ የሚያስብ ነው ። መፍትሔው ያለው ችግሩን በደንብ በማወቅ ውስጥ ነው ። አዋቂ ሰው ሁሉን እንዳላወቀ ይገባዋል ። እውቀት የማይገኝበት ነጻ ፍጡር የለም ብሎም ያምናል ። ብልህ ከእንስሳትና ከእጽዋትም ይማራል ።

መማር አስፈላጊ ነው ። መማር አስፈላጊ ቢሆንም ሰው መፈለግ አለበት ። የሚያስፈልጉ ነገሮችን የማይፈልጉ ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች ጥበብ የራቃቸው ሰዎች ናቸው ። ሁሉን ማጣጣል ፣ ሳያዳምጡ መልስ መስጠት ፣ ያልገባቸውን ነገር እንደ ገባቸው አድርገው አዎ አዎ ማለት የጥበብ የለሾች መለያ ነው ። መማር የጊዜ ገደብ የለውም ። በሰማይ የምንሄደውም የማይታወቀውን እግዚአብሔር ለዘላለም ለማወቅ ነው ። እረኛ የተናቀ ፣ ድሀ ፣ ከሰው ተገልሎ ከበጎች ጋር የሚውል ነው ። አስተዋይ ሰው ግን እረኛም የራሱ እውቀት እንዳለው ይረዳል ። የጥንት ነገሥታት እረኛ ምን አለ ? ይላሉ ። እረኛ ከዓለሙ ወጣ ብሎ የሚኖር ነው ። ዓለም የሚታየው በመካከሉ ሳይሆን ወጣ ሲሉ ነው ። ስለዚህ እረኛ ምን አለ ? ማለት አስተዋይነት ነው ። መማር የሚፈልግ ሰው ከእረኛም ይማራል ። መማር የማይፈልግ ከመምህሩም አይማርም ። “ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” እንዲሉ ከመምህሩ የማይማር ሞኝ ነው ።

መማር አለመፈለግ መማር ከሃይማኖት ያወጣኛል ብሎ መፍራት ሊሆን ይችላል ። ደግሞም ያወቅሁት በቂ ነው ብሎ ማሰብ ከመማር ይከለክላል ። እነ ሶቅራጥስ በእውቀታቸው ያወቁት አለማወቃቸውን ከሆነ ትክክለኛው እውቀት ገና አልተጀመረው ማለት ነው ። እውቀት በመጀመሪያ የሰውዬውን የትዕቢት ቀንድ ይሰብራል ። ትሑት ሰው በትክክል ያወቀ ነው ። መማር የማይፈልጉ ሰዎች የእውቀት ግቡ ገንዘብ ነው ፣ ስለዚህ ሀብት አለኝ ብለው የሚያስቡ ናቸው ። ሞኝ ባለጠጎች በአእምሮአቸው ሳይሆን በኪሳቸው ያስባሉ ። አዋቂን እየሸሹ አጫዋች ይዘው ይዞራሉ ። እውቀትን አለመፈለግ ሌላው ምክንያት መሞኘት ነው ። ድንቁርና ገዥ በመሆኑ አትወጡም ብሎ ይይዛል ። መማር የሰው ልጆች መብት ነው ። አለመማርም መብት ነው ። የተማሩ ሰዎች የሠሩትን እየተጠቀምን እውቀትን መጥላት ግን ተገቢ አይደለም ።

መማር የማይፈልግ በሥልጣን ልቡ የተመካ ሰው ነው ። አዋቂውንም ባለጠጋውንም ማሰር ሲችል ከእነርሱ የበለጠ ያወቀ ይመስለዋል ። ነገር ግን የመፍታት ጥበብ እንጂ የማሰር ችሎታ አያስደንቅም ። ቄስ የሚማረው “እግዚአብሔር ይፍታህ” ለማለት ነው ። መማር የማይፈልጉ ሰዎች ሌላው ምክንያታቸው ኑሮዬ አልተሟላም ብለው የሚያስቡ ናቸው ። ለትምህርት ተብሎ የሚበላ ምግብና ልብስ የለም ። ለመኖር በምንበላው ምግብና በምንለብሰው ልብስ መማር ይቻላል ። ደግሞም የቆሎ ተማሪ ለምኖ እንጂ ተለምኖ እንዳልተማረ ማሰብ ይገባል ። ስንፍና የመማር ጠላት ነው ። ትምህርት ዋጋ ያስከፍላል ። በዚህ ዓለም ላይ እንጀራ የሚያበሉ እውቀቶች አሉ ። እግዚአብሔርን ማወቅ ግን ከሁሉ የሚበልጥ የሚያስመካም ነው ። መልካም ነገርን በትምህርት ሳይሆን በተግባር ማወቅ ሕይወትን አስደሳች ያደርጋል ። ስለ ፍቅር መማር ተገቢ ነው ፣ ሲማሩት ያስደሰተ ሲኖሩት የበለጠ ያስደስታል ።

ፍላጎት የትምህርት ገበታን ያጠግባል ።

እንማር ።

የብርሃን ጠብታ 6

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መስከረም 2 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ