የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ተስፋችን ማን ነው ?

“መድኃኒታችን እግዚአብሔር ተስፋችንም ኢየሱስ ክርስቶስ”
                                                 1ጢሞ. 1፡1/
         ሐዋርያው ጳውሎስ በኢየሩሳሌም በ50 ዓ.ም ከተደረገው የመጀመሪያው የሐዋርያት ጉባዔ በኋላ ደግሞም በሁለተኛው ሐዋርያዊ ጉዞው ወጣቱን ጢሞቴዎስን አግኝቶ አስከተለው ። ጢሞቴዎስ ወደ ክርስትና የመጣው በ50 ዓ.ም. ሲሆን ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን የመጀመሪያይቱን የጢሞቴዎስን መልእክት የጻፈለትም በ63 ዓ.ም. ገደማ ነው ። በዚህ ጊዜ ጢሞቴዎስ በክርስትናና በአገልግሎት 13 ዓመታት ያህል ያሳለፈ ነው ። 13 ዓመት የሆነውም አማኝና አገልጋይ ምክር ያስፈልገዋል ። የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተች ቢያንስ 8 ዓመት ይሆናታል ። ጢሞቴዎስ የዚህች ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ሁኖ ነበር ። ሐዋርያው ጳውሎስ ወጣቱን መሪ እንዴት በአገልግሎቱ ውጤታማ እንደሚሆን የሚያሳይ የመጀመሪያውን መልእክቱን ጻፈለት ። ይህ ነገር ዛሬ ያሉት አባቶች ከበታች ላለው አስተዳዳሪ የማጽናኛና የጥበብ መልእክት ቢልኩ ታላቅ ደስታ ይሆን ነበር ። ጢሞቴዎስም በዚህ መልእክት እንደ ተደሰተ እርግጠኞች ነን ።

 ሐዋርያው ጳውሎስ ልጅነት የተጫነውን ማርቆስን ቢያጣም እግዚአብሔር ጢሞቴዎስን አዘጋጀለት /የሐዋ. 15፡36-41፤ 16፡1-3/። በማጣት ውስጥ ማግኘት አለ ። በማጣት ውስጥ ያለውን ማግኘት አስቦ ሥራውን የቀጠለ ሰው ያጣውን ቆይቶ ያገኛል ። ምክንያቱም ሐዋርያው ጳውሎስ በኋላ ለዚሁ ለጢሞቴዎስ እንዲህ ብሎታልና፡- “ማርቆስ ለአገልግሎት ብዙ ይጠቅመኛልና ይዘኸው ከአንተ ጋር አምጣው ።” /2ጢሞ. 4፡11/ ። ስለሄዱት ሳይሆን ስለሚመጡት ማሰብ ደስ ይላል ። ሐዋርያው ጳውሎስ በደቀ መዝሙሩ አዝኖ ቢቀር ኑሮ ጢሞቴዎስን አያተርፍም ነበር ። ጢሞቴዎስ እናቱ አይሁዳዊት ፣ አባቱ ግሪካዊ ነው ። ከልጅነቱ ጀምሮ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን በማንበብ ያደገ ፣ የክርስቶስንም መገለጥ የሚጠባበቅ ሰው ነበር ። እግዚአብሔር ለተጠሙት እርካታን ያዘጋጃልና ይኸው ጢሞቴዎስ አማኝም ጳጳስም ሆነ ። መካሪ መካሪ ፣ መሪው መሪ አያገኝምና ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ይህን መልእክት ጻፈለት ። ስለ ደከሙ ምእመናን እንጂ ስለ ደከሙ አገልጋዮች የሚያስብ የለምና ሐዋርያው የመጀመሪያውን መልእክት ጻፈለት ። ሳያስተምሩ መውቀስ ነውር ነውና ሐዋርያው ይህ ጦማረ ጽድቅ ሊጽፍለት ተጋ ።

 መልእክቱን የሚጀምረው በሰላምታ ነው ። ቤት ደጃፍ አለው ፣ ደብዳቤም ሰላምታ አለው ። ሰላምታ ልብን የሚያንኳኳ የፍቅር ምት ነው ። ሐዋርያው ሰላምታውን በስሙና በፍቅሩ ሳይሆን በእግዚአብሔር ስምና ፍቅር ይጀምራል ። የሰው ስም የሚሻር ፣ ፍቅሩም የማይቆይ ነውና ። ገና በሰላምታው ተስፋው ማን መሆን እንዳለበት ይነግረዋል ።
 ሐዋርያው ስለ ተስፋ መሠረት ለመናገር ምነው ተጣደፈ ? ከሰላምታው የተስፋው ድምፅ ምነው ቀደመ ? የሚል ካለ በአጉል ተስፋ ልብ እየተነነ እንደሆነ ስለ ተረዳ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ የሰውን ጉልበት ከሚጨርሱ ነገሮች አንዱ ያልተፈጸሙ ተስፋዎች ናቸው ። በዚህ ምክንያት ወዳጅ በወዳጁ ጽኑ ቅያሜ ያቄማል ፣ ሕዝብም በመሪዎቹ በብርቱ ያዝናል ። ሰዎች የሰጡትን ተስፋ ለመፈጸም የሚቸገሩት፡-
1-  ታማኝነትን በማጣት ፣
2-  አቅም በማጣትና
3-  ፍላጎት በማጣት ነው ።
ተስፋን መስጠትና መፈጸም ለራስ የሚደረግ ክብር ነው ። እግዚአብሔር ታማኝ ነው የምንለው ተስፋን ስለሚፈጽም ነው ።  አምስቱ ብሔረ ኦሪት የሚባሉት ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም ያሉት መጻሕፍት እግዚአብሔር ተስፋ የሰጠባቸው ሲሆኑ መጽሐፈ ኢያሱ ግን ተስፋው የተፈጸመበት ነው ። ዓመታት ቢረዝሙም እገዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ አይዘነጋም ።
ተስፋ ያደረግናቸው ነገሮች ብዙ ናቸው ። ተስፋ የሰጡን ሰዎች ግን የነፋስ ጭራ ሆነው የት እንዳሉም ማወቅ አልቻልንም ። ተስፋቸውን ታምነን የያዝነውን ጥለን የጠበቅናቸው ሕልም ሁነው ቀርተዋል ። ማፈር ደከመኝ እስክንል ተስፋዎቻችን ዱዳ አድርገውናል ። የዓመቱን በዕለት የዘመናቱን በዓመት እንደሚፈጽሙልን ቃል የገቡልን ያለንን ነገር ሲያሳጡን ተክዘናል ።መጽሐፍ ግን ተስፋችን ክርስቶስ መሆኑን ይነግረናል ። ዝለት በጽናት እንዲለወጥ ዛሬ ተስፋችንን ክርስቶስ ልናደርግ ይገባናል ። በመጀመሪያው ምጽአቱ የአዳምን ተስፋ የፈጸመ ነው ። በሁለተኛው ምጽአቱ የቤተ ክርስቲያንን ተስፋ የሚፈጽም ነው ። ተስፋውን ለመፈጸም ከልካይ የለውም ። ምክንያትም ሳያቀርብ ከተፈጥሮ በላይ ይሠራል ። ትዝብትን ሳያስብ ለታማኝነቱ ይተጋል ። ተስፋችን ማን ነው ?
ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲአመ

ያጋሩ