መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » “ተነሥቶአል በዚህ ፣ የለም” ማር. 16፡6 ።

የትምህርቱ ርዕስ | “ተነሥቶአል በዚህ ፣ የለም” ማር. 16፡6 ።

እንኳን ለ2012 ዓ.ም. የጌታችንና የመድኃታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ በሰላም አደረሳችሁ !
“ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን
በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን
አሰሮ ለሰይጣን አግዐዞ ለአዳም
ሰላም እምይእዜሰ ኮነ ፍሥሐ ወሰላም ፤”
ትርጓሜ፡-
“ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ።
ዲያብሎስን አሰረው ፤ አዳምን ነጻ አወጣው ።
ሰላም ! ከዛሬ ጀምሮ ደስታና ሰላም ሆነ ።” /ኦርቶዶክሳዊ አዋጅ/
. . .
በዓለም ላይ አንድ መቃብር ብቻ ባዶ ነው ። በጠባቆች የሚጠበቁ ብዙ መቃብሮች አሉ ። መቃብሩ እየተጠበቀ ግን ከተማውን የሞላ አንድ ብቻ ነው ። ተነሥተው ሕያው የሆኑ ሰዎችን አናውቅም ፣ ዳግም ሞት ላይዘው የተነሣውን ጌታ ግን እናውቃለን ። መግነዙን ቢያልፍ ፣ የተዘጋውን ቋጥኝ አያልፍም ፤ ቋጥኙን ቢያልፍ ወታደሮችን አያልፍም ፤ ወታደሮችን ቢያልፍ ገንዘብ የሚያስለፈልፋቸውን እውነትን ሐሰት የሚሉትን ማለፍ አይችልም ተብሎ ሳለ ምድርን የሞላው አንድ ብቻ ነው ። የሥጋውያንና የረቂቃንን ምክር ፣ የሲኦልና የሮማ ቤተ መንግሥትን ትብብር ፣ የቤተ ክህነትና የቤተ መንግሥትን ሽርክና ፣ የሊቀ ካህናትና የንጉሠ ነገሥትን ፊርማ አሸንፎ ልብን ግዛቱ ያደረገ አንድ ብቻ ነው ። እርሱም ከሞት የተነሣው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ።

እንደ እርሱ ሞት ያስገረመ ፣ እንደ እርሱ ትንሣኤ ያስደመመ የለም ። የማይሞተው ሲሞት “የምትወዱት አልቅሱለት” ተባለ ፣ በራሱ ኃይልና ሥልጣን ሲነሣ “ክብርና በረከት ይገባዋል” ተባለ ። መቃብሮች ሁሉ አጽሞች እንዳይሰረቁ ይጠበቁ ይሆናል ፣ እንዳይነሣ የሚጠበቅ መቃብር ግን የለም ።ክርስቶስ ግን እንዳይነሣ መቃብሩ ዘብ ቆመበት ፤ ከወዳጆቹ ይልቅ መነሣቱ በጠላቶቹ የታመነ ነበር ። ጠላቶቹ መሞቱንና መነሣቱን  ቢያምኑም አልዳኑም ። ለመዳን ከእርሱ ጋር መሞትና መነሣት ያስፈልጋልና ። ገደልነው ብለው ደስ ይላቸዋል ፣ ወዲያው እነሣለሁ ብሏል እያሉ መረበሽ እንቅልፍ ይነሣቸዋል ። የማያስተኛ ሟች ፣ የማይያዝ የትንሣኤ ጌታ ነው ። መቅደስ እያከበሩ መቅደስ ሰውነቱን አፈረሱ ፣ የሦስት ቀን ድልን ፈቀደላቸው ። ያዘኑ ወዳጆቹ ይደሰቱ ዘንድ ፣ የተደሰቱ ጠላቶቹ ያፍሩ ዘንድ ክርስቶስ ተነሣ ። የእስራኤልን መነሣት ተስፋ እያደረጉ የሚያነሣትን ገደሉት ። እንደ አቅማቸው ከእንቅልፍ እየተነሡ እንደ አቅሙ ከሞት እንደሚነሣ ዘነጉ ። የኃጢአት አውራው ዝንጋዔ ነው ። አይቶ እንዳላየ መሆን ነውና ።
ወትሮም እነርሱ በመቅደስ ሆነው እርሱ በመንደር ሲያስተምር አላፈሩም ። ከመቅደስ ሳይሆን ከከተማው አውጥተው ሰቀሉት ። ዛሬም ክርስቶስ በደጅ ነው ፣ መቅደሱ በሰቃዮች ሲሞላ ክርስቶስ በደጅ ይኖራል ። በመቅደስ በአሮናዊ ሥልጣን ፣ በደጅ በሮማውያን ሥልጣን ከምድረ ገጽ ይጥፋ ብለው ተነሡ ። ከመቅደስ ቢያባርሩት መቅደሱ ፈረሰ ፣ ከከተማ ቢያባርሩት ኢየሩሳሌም ተደመሰሰች ። ከዓለም ቢያባርሩት ዓለም ምጥ ያዘው ። እውቀቱ ወደ አለማወቅ ተለወጠ ። የመግደል እውቀት የማዳን እውቀት መሆን አቃተው ። እርሱ ግን ሰማይ ቤቱ ፣ ምድር ግዛቱ ፣ ምእመን ርስቱ ነው ።
ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀን እንደ ቆየና ሕያው እንደ ነበረ ክርስቶስም በሙታን መንደር ሙታንን እየፈለገ ሕያው ነበር ። ዮናስን የጣሉ እንደ ሞተ ያውቃሉ ፣ የጣሉት ሳያዩት ንስሐ የገቡ አዩት ። ክርስቶስም ያረዱት ሳይበሉት ፣ ኃጢአተኛ ነን ያሉ ጠገቡት ። ዮናስ ከሦስት ቀን በኋላ ወደ ነነዌ በንስሐ ድምፅ መጣ ፣ ጌታም ወደ ነነዌ ዓለም “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያሉ ወደሚሄዱት ደቀ መዛሙርት መጣ ። ከትንሣኤ በኋላ ቂምና መተዛዘብ የለም ፣ ለካደው ጴጥሮስ ቅድሚያ ተገለጠ ፣ አፍሮ እንዳይጠፋበት ። ለማናፍረው እያፈረ ስንት ዘመን አባበለን ። የሸሹትን ደቀ መዛሙርት ሳይታዘብ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አለ ። እርሱ “የሰውን ድካም ያውቀዋልና” ። ሞት ፍቅሩን አልገደለበትም ። እኛ ጭረት ፣ ትንሽ ቍስል ፍቅራችንን ገድላብን ይኸው ተስፋ ቢስነት ያሰቃየናል ። ለይቅርታ ካልተነሣን ሳንነሣ እንቅር ። መነሣት ብቻ በቂ አይደለም ፣ ለምንድነው የተነሣነው ማለት ያስፈልጋል ። ጌታ ለይቅርታ ፣ ብዙዎች ለበቀል ተነሡ ።
ክርስቶስ ጊዜ ሰጥቶት አልተነሣም ፣ በራሱ ኃይል ተነሣ ። በእግዚአብሔር መንግሥት ጊዜ የሚባል ቸር የለም ፣ ሁሉን የሚያደላድል የመለኮት እጅ ነው ። ሰዎች ማደሪያ ከልክለውት በደብረ ዘይት ጫካ ያድር የነበረው ምድር ግን ለሦስት ቀን ሸሸገችው ። ገጣሚው፡-
“ሞት ይቅር ይላሉ ፣
ሞት ቢቀር አልወድም ፤
አፈሩም ድንጋዩም ከሰው ፊት አይከብድም” ያለው ለዚህ ነው ።
እርሱ በሥጋ ሞተ ፣ በመለኮቱ ግን ሕያው ነው ። ሰንበትን በመቃብር አከበረ ። የሕይወት ሰንበታችን ነውና ልናከብረው እንደሚገባን አስተማረን ። መነሣቱን አይሁድም ይጠብቃሉ ጦር ይዘው ፣ ቅድስት እናቱም ትጠብቃለች ምስጋና ይዛ ። አጠባበቃችን እንጂ መጠበቃችን ዋጋ አይሰጠውም ። እግዚአብሔር ወራጁን ትቶ ምንጩን ያያል ። ሰው ግብዝ ነውና ወራጁን እያየ ያብዳል ። የእግዚአብሔር ልጅን መቃብር ከሦስት ቀን በላይ አልቻለውም ። በፈቃዱ ሞተ ፣ ተቀበረ ። ጠባቂዎቹ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ብቻ እንዲጠብቁ ታዘዙ ። በአይሁድ ልማድ ሦስተኛው ቀን ሞት እርግጥ የሚሆንበት ነው ። ጌታችን ግን ሞት እርግጥ በሚሆንበት ቀን ትንሣኤውን እርግጥ አደረገ ። እርሱ ባይነሣ ኑሮ ሐዋርያት አፍረው ወደ ገሊላ ይመለሱ ነበር ። እርሱ ባይነሣ ኑሮ ሐዋርያት ተነሣ በማለታቸው ወንጀለኛ ተብለው መከሰስ ሳይሆን አበዱ ተብለው መታከም ይኖርባቸው ነበር ። የሚከሰስም ጤነኛ ነውና ።
የምታምኑት እስኪ እልል በሉለት ። ምንድነው ዝምታው ? ስለ ሞት እያወራችሁ ስለ ሕያው ጌታ ምነው ዝም አላችሁ ? ጌታ ሆይ ተነሥተሃል አምናለሁ ። አይሁድ በጥፊ የመቱትን ጉንጭህን እስመው ዘንድ ወዴት አገኘዋለሁ ? ከበው ርኩስ ምራቃቸውን የተፉብህ ከብቦ የሚያስጨንቀንን በትንሣኤህ ጉልበት በትነው ።
ጸሎት
ቅድስት ሞትህን ቡርክት ትንሣኤህን አምናለሁ ፣ እባክህ ጽድቄን ይቅር በለው ። ፎቶ የሚያነሣ ይዤ እመጸውታለሁ ፣ መልክ ቀራጭ አቁሜ ስግደት እሰግዳለሁ ። ለዝና ደግ ነኝ ፣ ለወሬ ሰጪ ነኝ ። ዛሬ ኃጢአቴን ሳይሆን ጽድቄን ይቅር በለው ። ክፉ መስሎ የሚከፋውን ሁሉ ይጠላዋል ፣ ደግ መስሎ መክፋትን አንተ ትጠላዋለህ ። እባክህን ግብዝነት ያሸተተውን ይህን ሁሉ ሬሣ አንሣው ። አደራህን ብቻህን እንዳትነሣ የሞተ ወገንህን ይዘህ ተነሣ ። ታርደህ በጽዮን ለቆምከው በግ ምስጋና አቀርባለሁ ። በማይፈጸም ዘመን ለዘላለሙ አሜን ።
የመስቀሉ ገጽ 4
ሚያዝያ 11 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም