የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ተንሥኡ ለንባብ

“አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍሁ፥ ይህን ምሥጢር በመግለጥ አስታወቀኝ ፤ ይህንም ስታነቡ የክርስቶስን ምሥጢር እንዴት እንደማስተውል ልትመለከቱ ትችላላችሁ ፤” ኤፌ. 3፡3-4 ።

ሐዋርያው በአካል ተገኝቶ ለመሠረተው ፣ በቃል ላስተማረበት የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን አሁን ደግሞ ይጽፍላቸዋል ። በቃል ያለ ይረሳልና ይኸው በመጽሐፍ ያለውን ወረስነው ። ሐዋርያው የሚጽፉ እጆች ሲኖሩት የኤፌሶን ምእመናን ደግሞ የሚያነቡ ዓይኖች ነበሩአቸው ። በጽሑፍ የሚለዋወጡት ደግሞ የክርስቶስን ምሥጢር ነው ። መንግሥታዊ የሆነ ደብዳቤ ፣ ጥብቅ ምሥጢር የሆነ መልእክት ፣ ነገር ግን ሁሉ እንዲያነበው የተፈቀደ ጦማር ነገረ ክርስቶስ ነው ። ረጅም መልእክት እስኪጽፍ ድረስ በአጭሩ ይጽፍላቸው ነበር ። ጊዜ ሲገኝ ረጅሙን መልእክት መጻፍ ፣ ዛሬ ግን በአጭሩ መጻፍ ይገባል ። አጫጭሩ ጽሑፍ ሲቀጣጠል ትልቅ መጽሐፍ ይወጣዋል ። “በአፍሪካ የአንድ ሽማግሌ ሞት የአንድ ትልቅ ቤተ መጻሕፍት መቃጠል ነው” ይባላል ። ምክንያቱም እውቀቱን በጽሑፍ አያስቀርምና ። ከብዙ እውቀታቸው ጋር መቃብር የወረዱ ስንት ሊቃውንትና አባቶችን እናውቃለን ። ቅዱስ ጳውሎስ የዓይን ሕመሙ ሲታገሥለት ራሱ እየጻፈ ፣ ሕመም ሲጸናበት ጸሐፊ አስቀምጦ እያጻፈ ፣ በመጨረሻ ላይ ይፈርምበትና ይልክ ነበር ።

“እንግዲህ መቃብር ጠንክረህ ተማር ፣
ድጓ ተሸክሞ መጣልህ መምህር፤” ተብሏል ። መቃብር ግን አይማርም ፣ ሙትም አያነብም ። በአካል ተገኝቶ ቤተ ክርስቲያን መትከል ፣ በቃል ማስተማር የመሠረት ሥራ ነው ። ሕንፃው እስኪያድግ ድረስ በደብዳቤ መልእክትን ማስተላለፍ የአንድ መንፈሳዊ አባት ድርሻ ነው ። ሁልጊዜ በአካል መገናኘት አይቻልም ። ደብዳቤ ግን አካላዊ ግንኙነትን ወክሎ ልብ ለልብ ለመተያየት ያበቃል ። በደብዳቤ ላይ የጸሐፊው ውጫዊ መልክ የለም ። ውስጣዊ አሳቡ ግን አለ ። አንድን መጽሐፍ ስናነብ የጸሐፊውን ልቡን እያየን ነው ። የቀረን ትንሹ ይኸውም መልኩ ነው ። በዛሬ ዘመን የሃይማኖት አባቶች በርቀት ሁነው ለምእመናን የማጽናኛ ደብዳቤ ፣ የፍቅር መልእክት ፣ የሃይማኖት ትምህርት ይልኩ ይሆን ወይ ? ብለን ስንጠይቅ መልሳችን አጠራጣሪ ነው ። ደብዳቤ አለመረሳሳትን ያሳያል ። ደብዳቤ እስኪገናኙ መቆያ ይሆናል ። ደብዳቤ ፍቅርን ሕያው አድርጎ ይጠብቃል ። ደብዳቤ መላልሰው የሚያነቡት ነውና አሳብን ለማስረጽ ይረዳል ። ደብዳቤ ከተጨመቀ ልብ የወጣ ፣ አሳብ የገዘፈበት ነውና በክብር ሊያዝ ይገባዋል ። መንፈሳውያን አባቶችም ከቅዳሴ በኋላ ፣ ከጉባዔ በፊት ይህን ደብዳቤ አንብቡልኝ ብለው ቢልኩ ትልቅ የፍቅር መግለጫ ፣ የደስታ መነሻ ይሆን ነበር ። ወልዶ መጣልና መካድ በመንፈሳዊ ዓለም እንዳይበዛ ደግመን ማሰብ ያስፈልገናል ።

ጸሐፊው ቢጽፍ ምእመናን ካላነበቡ ድካሙ ከንቱ ሁኖ ይቀራል ። መጽሐፍ አለማንበብ ጸሐፊዎችን ለማጥፋት የሚደረግ አረመኔያዊ ድርጊት ነው ። የማያነቡ ሰዎች የአሳብ ጠላቶች ናቸው ። በምድር የተነሡ ክፉ ነገሥታት መጽሐፍን የማይወዱ ፣ ጸሐፊዎችን የሚያሰቃዩ ፣ የተጻፈውንም የሚያቃጥሉ ነበሩ ። የተለያዩ ዘመኖች የሳንሱር ሕጎች ፣ ለመጽሐፍ ድጎማ እንዳይደረግ መከልከል የአምባገነን መሪዎች ጠባይ ነው ። የአልኮል መጠጦች በቀላሉ በሚገቡበት አገር ፣ ወረቀት ግን በቀላሉ ካልገባ አሳብን ለማጥፋት ፣ ትውልድን እንደ ሄሮድስ ለመፍጀት ማቀድ ነው ። የማያነብ ሰውም ግላዊ አምባገነን ፣ የአሳብ ባላጋራ ነው ። በራሱ ላይ መብራት አጥፍቶ የተቀመጠ ነው ። መጽሐፍ ጨርሶ ማየት የማይፈልጉ ጽኑ ሕሙማን አሉ ። የቀልድ እንኳ መጽሐፍን መጠየቅ አይፈልጉም ። አዲስ ፋሽንና አዲስ ምግብ ቤት የሚያሳድዱ ለመንፈሳቸው ምግብ እንዲሆን መጽሐፍ የማይገዙ አያሌ ናቸው ። የሺህ ብር ሥጋ እየቆረጡ የአምሳ ብር መጽሐፍ ተወደደ የሚሉ በዚህ ዘመን ብዙዎች ናቸው ። በውጭ አገር አንድ ስፍራ ላይ ሰልፍ ከታየ አዲስ መጽሐፍ ወጥቷል ማለት ነው ። እኛ ጋ ሰልፍ ከታየ አዲስ ምግብ ቤት ተከፍቷል ወይም በዘንድሮ ሁኔታችን ዘይት መጥቷል ማለት ነው ። መጽሐፍ ገዝተው ደግሞ የማያነቡ ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች ጓደኛን እቤታቸው ጋብዘው የሚያኮርፉ ናቸው ። ሃያ አራት ሰዓት ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ሲውሉ ዓይናቸው ጤነኛ ነው ። መጽሐፍ ለማንበብ ሲጠየቁ ግን ዓይኔን እያመመኝ ይላሉ ። ለማንበብ የሚያስችል እውቀትና ዓይን ይዘው የማያነቡ ከሆነ ያልተማሩትና ማንበብ የማይችሉት ደግሞም የዓይን ብርሃን የሌላቸው እንዴት ይታዘቡአቸው ይሆን ? አንብበው ደግሞ ምላሰኛ የሚሆኑ ንባብን ለማውራት ብቃት የሚጠቀሙበት አሉ ። በእነዚህ ሁሉ መጽሐፍ ጥቃት ሲደርስበት አንብበው ራሳቸውን በሚያዩ ሰዎች ደግሞ መጽሐፍ ይከብራል ።

የምንጽፈው ምንድነው ? የምናነበውስ ምንድነው ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ። መጽሐፍ ምሥጢር ማስተላለፊያ ነው ። መጽሐፍ የአሳብ ቦይ ነው ። መጽሐፍ የጽንሰት ፣ የእርግዝና ፣ የምጥና የልደት ዘመን አለው ። የወለድነው ነፋስ ነው ወይስ ልጅ ነው ? ብለን መጠየቅ ያስፈልገናል ። ቂምና በቀልን የሚጽፉ ፣ ነውርና ውድቀትን የሚከትቡ ኃጢአታቸውን በዓለት ላይ የሚቀርጹ ናቸው ። እነርሱ ሊመለሱ ይችላሉ ፣ የረጩት መርዝ ግን ሊሰበሰብ አይችልም ። የምናነበውስ ምንድነው  ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል ። ሐዋርያው የክርስቶስን ምሥጢር እጽፋለሁ አለ ። በዚህም በልቤ ውስጥ ያለውን ጌታ ታስተውሉታላችሁ እያለ ነው ። ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ መከራ መስቀሉን ያነብ ነበር ። ታማኝ አንባቢ ጥሩ ተርጓሚ ይላክለታል ። ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ብቻ ቅዱሳን መላእክት አብረውን ይሆናሉ ። መንፈሰ እግዚአብሔርም ያለመልመናል ። በማንበብ ብቻ ሰማያዊ ዋጋ እናገኛለን ። “የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።” ራእ. 1 ፡ 3 ። በማንበብ ብፅዕናን ለማግኘት ተነሡ ። ተንሥኡ ለጸሎት ብቻ ሳይሆን ተንሥኡ ለንባብ መታወጅ አለበት ። የሚገርመው የማይጽፉ ሰዎች የሚጽፉትን ሲተቹ ነው ። መጽሐፍን ጸንሶ ለመውለድ ያለውን ጭንቅ ጸሐፊው ብቻ ያውቀዋል ። መጽሐፍ ስትገዙ ለወረቀቱ ሒሳብ ከፈላችሁ እንጂ ለአሳቡ የከፈላችሁ መስሎ እንዳይሰማችሁ አደራ እንላለን ። አሳብ ከዋጋ በላይ ነውና ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ