ጥር 8/2004 ዓ.ም.
አይሁዳውያን መሢሑ እንደሚመጣ ያምኑ ነበር፡፡ መሢሑ ግን ይጠብቁት የነበረው ከቤተ መንግሥት ይወለዳል፣ የወርቅ ግምጃ ይነጠፍለታል፣ ባደገ ጊዜ የጦር ሰዎችን አሰባስቦ በቅኝ ከያዙን ከሮማውያን በጦርነት ነጻ ያወጣናል፣ በኢየሩሳሌም ነግሦ እኛ የእርሱ የቅርብ ባለሟሎች እንሆናለን ብለው ይጠብቁት ነበር፡፡ ጌታችንን ያልተቀበሉበት ዋነኛው ምክንያት እንደጠበቁት ስላልተገለጠ ነው፡፡ ከልዕልት ይወለዳል ሲሉ ከአንዲት ድሀ ድንግል ተወለደ፤ በቤተ መንግሥት ይወለዳል ሲሉ በበረት ተወለደ፤ ወርቀ ዘቦ ግምጃ ይነጠፍለታል ሲሉ በእንስሳት ሣር ላይ ተኛ፤ የጦር ሰዎችን ያሰባስባል ሲሉ ሰላማዊ ነበር፤ በኢየሩሳሌም ይነግሣል ሲሉ በኢየሩሳሌም የሚነግሠው በመስቀል ላይ ነበረ፡፡ እንደጠበቁት ስላልተገለጠ አልተቀበሉትም፡፡ ዛሬም እርሱን መቀበል የሚከብደን እንደምንጠብቀው ስለማይገለጥ ወይም ስለማይሠራ ነው፡፡ እኛ የምንጠብቀው ከመልካም ውስጥ መልካም ሲወጣ ለማየት ነው እግዚአብሔር ግን ክፉ ከሚመስለው ከበሽታ፣ ከመገፋት፣ ከድህነት ውስጥም መልካም ነገርን ማውጣት ይችላል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ዛሬም የምንናገኘው ባልተደራጁ ስፍራዎች ለዓይን በማይሞሉና አደራ ሊጣልባቸው በማያስተማምኑ ሰዎች ውስጥ ነው፡፡
ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣው ባለጠግነቱንና ኃያልነቱን ለመግለጥ አይደለም፡፡ ባለጠግነቱ በመፍጠሩ፣ ኃያልነቱ ባለመደፈሩ ተገልጦ ይኖራል፡፡ በፈራጅነቱና በጽንዐቱ ጉልበት ሲመለክ ኖሯል፡፡ እግዚአብሔር ግን ሊገለጥ የፈለገው በድህነትና በድካም ነበር፡፡ ሁሉ እያለው እንደ ሌለው ሆነ፡፡ እንኳን ከሰው ከእንስሳት እስትንፋስን ተቀበለ፡፡ የፍጥረት መጋቢው የእናቱን ድንግልናዊ ወተት እየጠጣ አደገ፡፡ በቤተ ልሔም እንደ ሕጻን የታየው የዘላለም አባት ነበረ፡፡ እንደ ደካማ በበረት የተጣለው ኃያል አምላክ ነበረ (ኢሳ. 9፡6)፡፡ እርሱ ከላይ ከሥላሴነቱ ሳይጎድል በበረት ተገኘ፤ እያለን እንደሌለን ሆነን እንኖር ዘንድ ኢየሱስ በከብቶች በረት ተጥሎ ምሳሌ ሆነልን፡፡
ለእናትነት የመረጣት አንዲት ብላቴና እስራኤላዊት ድንግልን ነው፡፡ እርሱ የሥጋ ብልጥግናን አያይም፤ ሁሉ የእርሱ ነውና፡፡ እግዚአብሔር ብልጥግና የሚለው እግዚአብሔርን መፈለግ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው ብልጥግና በድንግል ማርያም አገኘና ደስ አለው፡፡ “ጌታ ያለው ሁሉም አለው” እያልን እንዘምራለን፡፡ ሰላም ላጡ ሰላማቸው፣ በረከት ላጡ በረከታቸው፣ ዕረፍት ላጡ አማናዊው ሰንበታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በእርግጥም የፍላጎት ዝርዝራችንን ይዘን ከመኖር ጌታን መፈለግ ይበልጣል፡፡ እርሱን ያገኙ ምንጩን አገኙ፤ ጸጋውን ሳይሆን ባለጸጋውን የያዙ በእውነት ከበሩ፡፡ ጌታችን የሚያስፈራንን ከሰው ማነስ የሚባለውን ሰቀቀን ከንቱ ሊያደርግ በንብረት የምንወዳደረውን እንኳን በቊሳቁስ በጸጋ እግዚአብሔርም መወዳደር እንደማይገባ ሊገልጽልን ሁሉ የሌለው ድሀ ሆኖ መወለድን መረጠ፡፡ በእናቱ ድህነት አላፈረም በትሕትናዋ ግን ደስ ተሰኘ፡፡ ዛሬ የጠቆረች፣ የከሳች፣ መልኳ የረገፈውን እናታቸውን ለሚክዱ ተግሣጽ ሊሰጣቸው ከአንዲት ድሀ ድንግል ተወለደ፡፡ ለእርሱ በሚታሰብለት ሰዓትም በመስቀል ላይ ሆኖ ለእናቱ አሰበ (ዮሐ. 19፡26)፡፡
ጌታችን የተወለደው በግርግም ነው፡፡ የዚያ ዘመን በረቶች በአብዛኛው ዋሻዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ የተወለደውን ሕጻን ለማግኘት ሁሉም ወደ ዋሻው ዝቅ ብሎ መግባት ግዴታው ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ዝቅ ካላሉ አይገኝም፡፡ ድሮ ሰማይንና የሰማይን አምላክ ለማየት ቀና ማለት ግዴታ ነበር፤ አሁን ሰማይና የሰማይ አምላክ በበረት ወድቋልና ዝቅ ማለት ግዴታ ነው፡፡ በአደባባይ ጀብዳቸውን የሚያወሩ ሰባኪዎች ይህንን ጌታ እያጡት ነውና ያሳዝናል፡፡ እነዚያ ጠቢባን፣ ነገሥታትና ባለጠጎች የሆኑት ሰብአ ሰገል ኢየሱስን ለማግኘት ከዋሻው ዝቅ ብለው ገቡ፡፡ ዝቅ ካላሉ በቀር ክርስቶስ በጥበብ፣ በሥልጣንና በሀብት አይገኝም፡፡ ክርስቶስ በጥበብ በሥልጣንና በሀብት አይገኝም፡፡ የክርስቶስ መገኛው ትሕትና ብቻ ነው፡፡ ይህ ትሕትና በሰዎች ፊት መቅለስለስ ሳይሆን በኅሊናና በጌታ ፊት ራስን በልኩ ማየት ነው፡፡ ሰዎች ያላቸውን እሴት ታሳቢ አድርጎ ጌታ እንዲቀበላቸው ይፈልጋሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን የሚቀበለን በእግዚአብሔር ነው፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ከነመዐርጋችን ብንመጣ ጌታን አናገኘውም፡፡ ኒሻናችንን ስናወልቅ ብቻ የመዳን ኒሻኑን ያጠልቅልናል፡፡
ጌታችን የተወለደው እጅግ ቀዝቃዛ በነበረው ወራት ነው፡፡ በሌሊት ያውም በከብቶች በረት ውስጥ ቅዝቃዜውን መግለጥ በፍጹም አይቻልም፡፡ በእንስሳት መኖ ላይ መተኛቱ የአንስሳትንም እስትንፋስ መሞቁ አስደናቂ ነው! እኛ ለልጆቻችን የምናደርገውን እንክብካቤ ስናስበው ለዓለም ጌታ ግን አልሆነለትም፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ስንል በእርሱ ድህነት ባለጠጎች እንድንሆን ኢየሱስ ክርስቶስ በሁሉ ባዶ ሆነ፡፡
ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው መግቢያ ላይ ብቻ አይደለም በድህነት የኖረው፡፡ ዘመኑን በሙሉ በድህነት ኖሯል፡፡ አገር የለሽ ሆኖ መሰደዱ፣ በተውሶ ጀልባ መጓዙ፣ ከሰማይ ወፎች ከመሬት ቀበሮዎች ያነሰ ሆኖ ራሱን የሚያስጠጋበት፣ ቤት ማጣቱ፣ እርቃኑን መሰቀሉ፣ በተውሶ መቃብር መቀበሩ ይህ ሁሉ የማይነገር ድህነት ነው፡፡ ይህንን ፍቅርና ውለታ እንዴት እንመልሰዋለን! ሞቱ ብቻ ሳይሆን ኑሮውም ቤዛችን የሆነው የኢየሱስ ፍቅር እንዴት ድንቅ ነው!
ዛሬ ይህን ፍቅር መዘከር ሳይሆን መመለስ ይጠበቅብናል፡፡ ኢየሱስ ዛሬ በአካል የለም፤ እንዴት ውለታውን እንመልሰዋለን? ኢየሱስ ዛሬ ከስደተኞች ጋር እየተሰደደ፣ ከረሀብተኞች ጋር እየተራበ፣ ለልጆቻቸው የሚያበሉትና የሚያለብሱት አጥተው ከሚያዝኑ እናቶች ጋር እያዘነ ነው፡፡ ኢየሱስ ዛሬ ከቤት አልባዎች ከጎዳና ተዳዳሪዎች ጋር በብርድ እየተሰቃየ ነው፡፡ በየአገሩ በስደተኛ መጠለያ የሚጨነቀውን አንዱን ወገናችንን ዛሬ ነጻ ለማውጣት ከተነሣን ኢየሱስ ከግብፅ ስደቱ በእውነት ይመለሳል፡፡ አንዲት ድሀ እናትን ለልጆቿ ምግብ ዛሬ ብንሰፍርላት የድንግል ማርያምን መከራዋን ካስናት፡፡ በጎዳና ለወደቁት ዛሬ መጠለያ ብንሠራ ኢየሱስን ወደ ቤታችን አስገባነው፡፡ ልብ አድርጉ እርሱ በበዓል ድግስ አይገኝም፡፡ እርሱ በድሆች ውስጥ ይኖራል፡፡ እርሱ በቃል ፍቅር አይገኝም፣ በተግባራዊ ፍቅር ይረካል!
“ተወልዶላችኋል” ይህን ቃል የተናገረው መልአኩ ነው፡፡ በእርግጥም ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው ለመላእክት አይደለም፡፡ ለእኛ ነው፡፡ ስለ እኛ ተወልዶ ሌሎች ከዘመሩ እኛማ እንዴት እንዘምር ይሆን? ለዛሬም ጭንቀታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶልናል፣ ለዛሬም ስብራታችን ኢየሱስ ተወልዶልናል፣ ለዛሬው መከራችን ኢየሱስ ተወልዶልናል! አዎ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው መልስ ሊሆነን ነው!
ክብር ምስጋና ከምድር እስከ አርያም ለተወለደው መድኅን ለእርሱ ይሆን ለዘላለሙ አሜን!