የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ተጠየቅ እግዚአብሔር

ረገፈ እንደ ቅጠል ያ ሁሉ ትውልድ ፣ ያ ሁሉ ጠምበለል ። እንደ ወጣ አልተመለሰም ያ ሁሉ ወጣት ፣ የከፈተውን አልከደነም ያ ሁሉ ልጅ ። ሠርክ በጅምር ፣ በጥዋት ማታ የሆነበት ያ ሁሉ ጎበዝ ። በሜዳ የወደቀው ፣ አሞራ የበላው ያ ሁሉ ቡቃያ ። ተጠየቅ እግዚአብሔር ። እንዲህ ልታፈርሰው ለምን ገነባኸው ? እንዲህ ልትቀየመው ለምን አመጣኸው ? ተጠየቅ እግዚአብሔር ባንተ ቦታ እኔ ሳልመጣ ፣ በእኔ ቦታ አንተ ሳትቆም ተጠየቅ ባለ ዙፋኑ እግዚአብሔር ። መውለድ ቅጣት እስኪመስል ፣ ወገንን ለመጨረስ ገዥዎቻችን ሲታጠቁ ተጠየቅ እግዚአብሔር ሰው ሰውን ስለበላባት ስለእኛ ምድር ። እንደ እስራኤል አርባ ዓመት ቢሞላንም አልገባንም ከነዓን ። በተስፋ ያወጡን በረሃ ቀርተዋል ፣ የሰበኩን ሊቃነ ካህናትም ጥርኝ አፈር ሁነዋል ። እኛ ግን ገና ተስፋ ይዘን በቃዴስ በርኔ እንማስናለን ። እኮ ተጠየቅ እግዚአብሔር ። የረገጥነውን እንረግጣለን ፣ የሄድንበት ላይ እንመለሳለን ፣ የመጣው ክፉ ሲጣበቀን ፣ ደጉ ግን አይበረክትልንም ፤ የምንኖርበትን ከተማ መንገድ አጥተን ይህ ሁሉ ዘመን ለምንንከራተት ተጠየቅ እግዚአብሔር ።

ያ ሁሉ ሽበት ሲዋረድ ፣ ያ ሁሉ አእምሮ አደባባይ ሲወድቅ ። ዕድሜና እውቀት ወንጀል ሲሆን ለምን ዝም አልህ ተጠየቅ እግዚአብሔር ። የቅጣት ደረጃ የሌለን የመጀሪያውም የመጨረሻውም ቅጣታችን ሞት የሆነውን እኛን ለእኛ ስለተውከን ተጠየቅ እግዚአብሔር ። ብሶት ወልዶን ብሶት የምናስወልደውን ፣ ያለ ምንም ደም ብለን ደም ጨርሰን የምንወርደውን ፣ ለሰፊ ሕዝብ ብለን ለግለሰብ የምንኖረውን ፣ ለግፍ ተዋግተን ግፈኛ የምንሆነውን እኛን ስናብድ ስላላቆምከን ተጠየቅ እግዚአብሔር ። ስንጮህ የሚደርስልን ፣ ስንጣራ አቤት የሚልልን የሌለን ሕዝቦች ስንሆን ፣ ጥዋት ያበላነውን ከሰዓት ስንሰቅለው ፣ ሰውነትና ሰይጣንነት ሲቀላቀልብን ለፈቃዳችን ስለተውከን ተጠየቅ እግዚአብሔር ። የደም ምንጫችንን የሚዘጋው ሲጠፋ ፣ የምንታጠበው በሕፃናት ደም ሲሆን ይህንን ክፉ ግብር ዝም ስላልከው ተጠየቅ እግዚአብሔር ። ገደቤ እስከዚህ ነው ብለን ራሳችንን በመንደራችን ለማሰር እንደ ባቢሎን ሰዎች ግንብ ስንገነባ ፣ ግንቡን ለማፍረስ ስላልወረድህ ፣ ክፋታቸውን ይጨርሱት ብለህ ስለተውከን ተጠየቅ እግዚአብሔር ። ነጻ የሚያወጣን ነጻ የወጣ ስናጣ ፣ ቀኝ እጃችን ግራ እጃችንን ለዘመናት ሲቀጣ ፣ በመሳሪያ ተገደን ስንዘፍን በመሳሪያ ስናለቅስ የኖርነውን ፣ ለመሞት እንኳ ፈቃድ የተከለከልነውን እኛን ዝም ስላልህ ተጠየቅ እግዚአብሔር።
ትውልድ ግራ ሲጋባ ፣ ሊጫወት የሚገባው ሕፃን ስለ ምሳው አሳብ ሲያንገላታው ፣ የኑሮ ደረጃው አርያምና እንጦሮጦስ ሲሆን ፣ የከፋው በደንብ ሲከፋው ፣ ያገኘው በጣም ሲያገኝ ይህን ሚዛን አልባ ኑሮ ዝም ስላልከው ተጠየቅ እግዚአብሔር ። የሚመራን አጥተን ወደ ጉድጓድ ስንጓዝ ፣ በእሳት ወላፈን ስንጫወት ፣ ኪዳንን አፍርሰን ወንድማችንን ስንሸጥ ፣ ትዳር አቃለን ቤትን ስንንድ ዝም ስላልከን ተጠየቅ እግዚአብሔር ። ምኞታችን ሲጋልበን ፣ ለእውነት ሳይሆን ለስሜት ስንኖር ፣ ተዋርደን አላበቃ ስንል ፣ አንዱ ባንዱ ጣቱን ሲቀስር ፣ መንገድ የጠፋውን ስናደናብር ፣ የወደቀው ላይ መጥረቢያ ስናበዛ ፣ የሳተው ላይ ስላቅ ስናመርት ፣ የሄደውን አበሳውን ስናበዛ ፣ ላለው ስንዘፍን ፣ የሌለው የለውም ስንል ዝም ብለኸናል ተጠየቅ እግዚአብሔር ።
የተከፋ ብዙ ፣ የሚቅበዘበዝ ቊጥር የለሽ ነው ። የሚያጽናና አባት ፣ የሚሰበስብ እረኛ አጥተን ፣ በሞታችን የሚቀልዱ ፣ ለተዝካር ያገናኘን የሚሉ ሲገዙን ዝም ብለኸናል ፣ ስለዚህ እግዚአብሔር ተጠየቅ ። ሰው እኮ ያንተ ነው ። አንተ ጻድቅ ነህ ፣ ሰው ግን አፈር ነውና ቢያጥቡት የማይጠራ ነው ። ግድ አይልህም ወይ ? የፈጠርከው መጫወቻ ሲሆን አታዝንም ወይ ? ደግሞስ እንደ ሞኝ እንዴት ንብረትህን ትጥለዋለህ ? ነጻ ፈቃድ ብትሰጥስ ሁሉም ነገር ፀጥ ይበል ብለህ ልጆችህን አትሰበስብም ወይ ? ራሳችንን እንዳንጠይቅ የምንጠየቅበት በዝቶ እየረሳነው ነው ። እኛ ብንጠየቅም ጥቅም የለውም ። በዚያ ዓርብ በርባን ቢጠየቅ ዓለም አይድንም ነበረ ። መጠየቅ የነበረበት ወንጀለኛ ነው ። ነገር ግን በርባን ቢጠየቅ ሞት አይሞትም ። ወልድ ሆይ ዛሬም አንተ ተጠየቅና ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን አድን !!!   
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ