“ይኸውም፥ በክርስቶስ አስቀድመን ተስፋ ያደረግን እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው ።” ኤፌ. 1፡12።
ወጣቶች ሙሉ ብርሃን ላይ የቆሙ ፣ የዛሬ ጀግኖች ፣ የነገ ወራሾች ተደርገው ይታሰባሉ ። ወጣትነት ሁሉን እችላለሁ ባይነት የሚንጸባረቅበት የዕድሜ ግለት ነው ። ወጣቶች ብዙ ውጥኖችን ይጀምራሉ ፣ አንዱ አልሳካ ሲል ሁሉንም ለመጣል ሊሰናዱ ይችላሉ ። ኑሮ ከኃይል ይልቅ ለጥበብ ያደላች መሆኑን ፣ ዛሬ ሁሉንም ነገር ከፈጸሙት ነገ የሚሠራ ነገር እንደሌለ ወጣቶች አይገነዘቡም ። ወጣቶች በዚህ ዘመን አገርና ራሳቸው የከዳቸው መስሎ እየተሰማቸው ተስፋቸው ሲላላ እያየን ነው ። ወጣቶችዋ ተስፋ የቆረጡባት አገር ዛሬ ድል ፣ ነገ ግብ የላትም ። ብዙ ወጣቶች ባይማሩም በጉልበታቸው ፣ ቢማሩም በእውቀታቸው እንዲሠሩ ሊመከርላቸው ይገባል ። ሥራ ለመቀጠር ከቀጣሪዎቻቸው ሴቶች የዝሙት ጥያቄ ፣ ወንዶች የገንዘብ እጅ መንሻ ሲጠየቁ ወጣቶች ኀዘን ውስጥ ይገባሉ ። ሠላሳ ሠራተኞችን ለመቅጠር በወጣው ማስታወቂያ ሠላሳ ሺህ ለውድድር ሲመጣ ሲታይ ፣ ወጣቶች በእውቀት ቀርቶ በጎሣ መታጨትን ሲያዩ ቂምና በቀልን እንዲሁም ጭካኔን እያዳበሩ ይመጣሉ ። ስለ ራሳቸው ግድ የሌላቸው መሆናቸው ሊያስፈራን ይገባል ። ሰው ራሱን በቅጡ ካልወደደ ሌላውን መውደድ አይችልምና ። በየስፍራው ያለው ግጭት ሥሩ ድህነት ነው ። የብዙዎች ድርሻ በጥቂት ሰዎች እጅ ያለ አግባብ በመውደቁ ፣ ሰው በሙያው ሳይሆን ለዘመን በማርገዱ እንጀራ ሲበላ ሲያዩ ወጣቶች ተስፋቸው ይጨልማል ።
አንዱን እግዚአብሔር መፍራት ወይም ፈሪሀ እግዚአብሔር ወጣቶችን ከብዙ ፍርሃት የሚያድን ነው ። ያሉብን ብዙ ፍርሃቶች በአንድ ፍርሃት የሚወገዱ ናቸው ። እርሱም ፈሪሀ እግዘዚአብሔር ነው ። ወጣቶች የአንዲት አገር አቅም መለኪያዎች ናቸው ፣ ወጣቶች ያሉባት አገር አትደፈርም ። በከተማ ሠራተኞች ፣ በድንበር ጠባቂዎች ናቸው ። ይልቁንም በዚህ ዘመን ዓለም የወጣቶች እየሆነች ነው ። የአገርና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወጣቶች ናቸው ። ወጣቶች ላይ የምንሠራው በጎ ሥራ ለዛሬም ለነገም በጣም ይጠቅመናል ። እንኳን ሰው እንስሳም በወጣትነቱ ያምራል ። ወጣቶችም ስናያቸው የሚያስደስቱን ሊሆኑ ይገባል ። ወጣቶች ደጎች ለደግነት ካልፈለጉአቸው ክፉዎች ለክፋታቸው መጠቀሚያ ያደርጓቸዋል ። ወጣትነት ለምን ሳይል መጋደልን የሚያበዛ ነውና እግዚአብሔርን ማሰብ በጣም ያስፈልገዋል ። ወጣቶች የሞትን ትርጉም ፣ በዛሬና በነገ መካከል ልዩነት መኖሩን ፣ የዛሬ አለመሆን ለነገ መሆን መንገድ እንደሆነ አይረዱም ። ተስፋ ሲቆርጡም ከመሞከር ይልቅ ተጨብጦ መቀመጥን ፣ ከመኖር ይልቅ መሞትን እንደ አቋራጭ መንገድ ያዩታል ።
ወጣቶች ፍቅርን ሰጥተናቸው በአድናቆት ፈገግታ ከተቀበልናቸው ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ ። የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ዓለምን ከረሀብ አደጋ ታድጓል ። ነቢዩ ዳንኤልም ተማርኮ ገዥ ሁኗል ። ወጣትነት የብዙ ዕድል ባለቤት ነው ። ወጣቶች ፈሪሀ እግዚአብሔር ፣ የአባቶች ምክር ፣ የተቀደሱ መጻሕፍት ፣ ራእይ ያስፈልጋቸዋል ። ከሁሉ በላይ ወጣቶች ተስፋ መሰነቅ ያስፈልጋቸዋል ። ፍትሕ ሲጠፋ ፣ አገር በቡድን ሲዘረፍ ፣ ሙስና የብረት አጥር ሁኖ አላሳልፍ ሲል ፣ የማሰብና የመናገር መብት ሲታፈን ፣ ምድር የጥቂቶች ስትሆን ወጣቶች የተወለዱባትን አገር ለቀው መሰደድ ይጀምራሉ ። ነገ የሌላት አገር ወጣቶችዋን የማትንከባከብ አገር ናት ። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ውድቀት የወጣቶች ብስጭት ነው ። የደርግ ውድቀትም ወጣቶችን ማጣት ነው ። እስካሁን ድረስ ያሉ አለመረጋጋቶች ወጣቶች በቅጡ አለመያዛቸው የወለደው ነው ። ወጣቶች ተስፋ የሚያደርጉባት አገር መፍጠር ያስፈልጋል ። ዛሬ አቅርቦቱ ባይኖር ተስፋ ግን በሰላም ያሳድራል ።
ተስፋ እያደረግን ነው ወይ ? ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ ብዙ ነገሮች ልባችንን አድክመውታል ። ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ በዕድሜ የገፉትም ተስፋ እያጡ ፣ በብዙ መጠይቆች ውስጥ እየገቡ ነው ። ነገር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ይኸውም፥ በክርስቶስ አስቀድመን ተስፋ ያደረግን እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው” ይላል ። ኤፌ. 1፡12 ። ተስፋ ማድረግ የሚቻለው በክርስቶስ ነው ። በክርስቶስ ተስፋ ያደረግነው ደግሞ ለኃላፊው ኑሮ ሳይሆን ለዘላለም ሕይወት ነው ። ለዛሬ የሚያስተማምን ነገር ቢታጣ ለዘላለም ግን ተስፋ የሚሆን ነገር አለ ። ነገን የሚወርሱ ተስፋ ያደረጉ ናቸውና ተስፋ ማድረጋችንን መቀጠል ያስፈልገናል ። ተስፋ ማጣት ባይገድል እንኳ አጉል ነዋሪ ያደርጋልና ተስፋ ማድረግ አለብን ። ጠላቶቻችን ገንዘባችንን ይውሰዱት ፣ መኖሪያችንን ይንሡን ተስፋችንን ግን ሊያሳጡን አይገባም ። እግዚአብሔር ተስፋ ለሚያደርጉ ያዘጋጀውን ሽልማት በተስፋው ፍጻሜ ላይ ያስረክባል ። “እንጨት ካልጨሰ አይነድም” እንዲሉ ካላለቀሱና ካልተጎዱ የብርሃን ዘመን አይመጣም ።
ወገኖች በዚህ ቃል ተጽናኑ !
የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /21
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 8 ቀን 2014 ዓ.ም.