የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ተፈጥሮ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት

ዮሐንስ መጥምቅ እግዚአብሔር በተፈጥሮ አማካይነት ያስተማረው ነቢይ ነው ። ተፈጥሮ ስለ እግዚአብሔር ደግነት ፣ ጥበብና ኃይል ይናገራል ። ተፈጥሮ በዝምታ ስለ እግዚአብሔር መኖር/ሀልዎት ይጮኻል ። ታላላቅ የእግዚአብሔር ሰዎች በተፈጥሮ ተሰብከው ወደ አሚነ ሥላሴ ተመልሰዋል ። ዮሐንስ መጥምቅ እግዚአብሔር በተፈጥሮ ያስተማረውና እርሱም በተፈጥሮ መርጃነት ያስተማረ ነው ። በምሥራቅ ሲዞር የናባው ተራራ ይታየዋል ። ተራራው ይደልደል ብሎ ትዕቢትን ይገሥጻል ። በምዕራብ ሲዞር ጠመዝማዛውና የደጉ ሳምራዊ የቸርነት ቦታ የሆነው የኢያሪኮ ቁልቁለት ይታወሰዋል ፣ ጠማማው ይቅና በማለት ድብቆችን ፣ በፍቅር የቀረባቸውን በብልጠት የሚቀርቡትን ከንቱዎች ይመክርበታል ። ወደ ሰሜን ሲመለከት ሸካራው የገሊላ መንገድ ይታወሰዋል ፤ በቂም በበቀል ውስጣቸው የነኮረባቸውን ሰዎች ተመለሱ ይልበታል ። ወደ ደቡብ ሲያማትር የምድራችን ዝቅተኛ ቦታ የሆነውን ሙት ባሕር ይመለከትና የዝቅተኝነት ስሜት ፣ አልችልም ባይነት ፣ ራስን ከሌላው ጋር የማወዳደር ስቃይ ያለባቸውን ምስኪኖች አስታውሶ ፣ ሸለቆው ይሙላ በማለት ያስተምርበታል ። እንደ ዮሐንስ መጥምቅ ስብከት የዓለማችን ችግሮች አራት ናቸው ። እነርሱም ትዕቢት ፣ ሽምቅነት ፣ ቂም በቀል ፣ የበታችነት ስሜት ናቸው ። ጥምቀትን ስናስብ እነዚህን መሰናክሎች ለማንሣት በመጣር ሊሆን ይገባል ።

ተፈጥሮ የእግዚአብሔር የእጁ ሥራ ነው ፣ ልንጠብቀው ይገባል ። ተፈጥሮ ስጦታችን ነው ፣ ልንወደው ይገባል ። ተፈጥሮ ትምህርት ቤት ነው ፣ ልንማርበት ይገባል ። ተፈጥሮ ከተፈጥሮአችን ጋር የተያያዘ ነው ፣ ለመኖራችን አስተዋጽኦ ያደርጋል ። ተፈጥሮ እግዚአብሔር ለእኛ ፍቅሩን የገለጠበት ነው ፣ ልንከባከበው ይገባል ። ጻድቅ ለእንስሳ ነፍስ ይራራል ፣ እጽዋትን እንኳን ሊቆርጥ ቅጠላቸውን ለመበጠስ ይሳሳል ። ዛሬ ዓለም እየተጋረጠባት ያለው አደጋ የተፈጥሮ መጎዳት ነው ። ከሰው ብቻ ደስታ ስለምንጠብቅ እንከስራለን ። እንስሳቱን ፣ እጽዋቱን ባለማስተዋላችን በረከታችንን አጥተነዋል ። አፈሩን ለመንካት ተጸይፈን ለእግራችን ጫማ ፣ ለእጃችን መሸፈኛ አድርገናል ። አፈሩን በመርገጥና በመንካት የምናገኘው ፈውስ አለ ። ከተፈጥሮ ጋር በርቀት የሚኖሩ የሞት ጎረቤት ናቸው ። ጥምቀት በውኃ የሚከናወን ነው ። ውኃ ፣ ጅረት ፈልገን የምናከብረው ከሆነ የወንዞች ንጽሕና ወሳኝ ነው ። ወንዞችን ላለመበከል ምእመናን ቃል የሚገቡበት ቀን ሊሆን ይገባዋል ። የተሰበሰበ ሕዝብ አግኝቶ አለማስተማር ፣ የሚዘምት ሕዝብ ይዞ አገርን አለመቀደስ በእውነት ስንፍና ነው ። እያንዳንዱ ሰው አንድ አንድ ቆሻሻ ቢያነሣ አገር ይጸዳል ።

እግዚአብሔር ራሱ በተፈጥሮ የሚያስተምር ነው ። ስለ በለስ ፣ ስለ ወይን ብዙ ጊዜ ተናግሯል ። ተፈጥሮን መጉዳት መንፈሳዊ ትምህርት ቤትን ማውደም ነው ። በደርግ ዘመን መንግሥትን የጎዳ እየመሰለው ችግኝ ዘቅዝቆ ይተክል የነበረው ወገናችን ዛሬ በድርቅ ፣ በዝናብ እጦት ይሰቃያል ። ደግመን እንናገራለን ። አገሩ የእኛ ነው ፣ ሌላ አገር የለንም ። ልንንከባከበው ይገባል ። የምናወራውና የምንጋጭበት ነገር ፣ ሰው ጠግቦ የጥርስ መጎርጎሪያ ይዞ የሚያወራውን ነው ። ስንዴ እየለመንን መነካከስ አሳፋሪ ነው ። የልመና መስፈርት እንኳ አታሟሉም ተብለን ለብድርና ለምጽዋት ተባርረናል ። ይህ ማቅ የምንለብስበት ዘመናችን ነው ። ጥምቀት ዮሐንስ ንስሐን የሰበከበት ፣ ብዙዎች የተመለሱበት ነው ። በጥምቀት ቀን ስካርና ጭፈራ ሳይሆን እግዚኦታ ሊደርስ ይገባዋል ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ