የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ትሕትና

ትሕትና የትንሽት ምልክት አይምሰልህ ፡፡ ታላቁ መስፍን ሙሴ ፣ ታላቁ ጌታ ክርስቶስ ትሑታን ነበሩ ፡፡ ባለጠግነት ትሕትናን ሊያሳጣህ ሲሞክር ጻድቁ አብርሃምና ጻድቁ ኢዮብ ትሑታን እንደ ነበሩ አስብ ፡፡ ሥልጣን ልብህን ከፍ ሲያደርግብህ “ለንጉሥ በቀን ላይ ቀን ትጨምራለህ” በማለት የተናገረውን ዳዊትን አስብ ፡፡ ምንም ብትነግሥ ለራስህ አንድ ቀን መስጠት አትችልምና ፡፡ ደግሞም “ሁሉም ከንቱ” ያለውን ሽቅርቅሩን ንጉሥ ሰሎሞንን ፣ ጠቢቡን ንጉሥ ይዲድያ የተባለውን በማሰብ አለባበስንና እውቀትን ናቀው ፡፡ ጉልበትህ ሊያስታብይህ ሲሻ ሶምሶምን አስብ ፡፡ ኃይልህ ከኃያላን ፣ ሥልጣንህ ከሠለጠኑት ፣ እውቀትን ካወቁት ጋር ቢነጻጸር በጣም ትንሽ ነው ፡፡ በምድራዊ ነገር ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ጸጋም ልትመካ አይገባህም ፡፡ ትምክሕት እጄ ሀብትን ፣ ጽድቄ ጸጋን አመጣልኝ ማለት በመሆኑ ቁጥሩ ከክህደት ነው ፡፡ በጸጋ ሳይሆን በባለጠጋው መመካት ግን ተፈቅዷል ፡፡ ኃጢአትህ እየበዛ ሲመጣ የሌሎች ስህተት እየታየህ ይመጣል ፡፡ ጽድቅ በውስጥህ እየተስፋፋ ሲመጣ የራስህ ደካማነት ይታይሃል ፡፡
ትሕትና በአደባባይ እንደ ለበስከው ነጭ ሸማ ነው ፡፡ ታጌጥበታለህ ፡፡ ትዕቢት ግን ያዋርድሃል ፣ የማያውቅህ ሳይቀር አይቶ ይጸየፍሃል ፡፡ ቁመተ ረጅሞች ሲኮሩ ሰማይን የምታይ ይመስልሃል ፡፡ አጭሮች ሲልመጠመጡ መቃብር የገቡ ይመስላል፡፡ የረጅምነት ውበቱ ዝቅ ማለት ነው ፡፡ ትዕቢተኛ ስትሆን ሰዎች እንከን እንዲፈልጉብህ መንገድ ትከፍታለህ ፡፡ ትሕትና ራስን የማወቅ ውጤት ነው ፡፡ ራሱን በትክክል የሚያውቅ ሊታበይና በሌሎች ሊፈርድ በፍጹም አይችሉም ፡፡ ትሕትና የሌሎችን ክብር ማወቅ ነው ፡፡ ማክበር መከበር ነውና ሌሎችን ስናከብር ትሕትና ታስከብረናለች ፡፡ ትሕትና ሁልጊዜ እንደሚማሩ ሁኖ መኖር ነው ፡፡ ትሕትና በጠፋበት ዘመን ሁሉም ሰው አስተማሪ ይሆናል ፡፡ ሁሉም ሰው ቅዱስ ነኝ በማለት ሌሎችን ያጣጥላል ፡፡ ጆሮ ጠፍቶ አፍ ብቻ የበዛበት ዘመን ዘመነ ትዕቢት ነው ፡፡ እገሌ ክፉ ነው ማለት በተዘዋዋሪ እኔ መልካም ነኝ ማለት ነውና ትዕቢት ነው ፡፡ ትሕትና የሰዎችን ትልቅ ድካም አሳንሶ ፣ ትንሽ ብርታታቸውን አጉልቶ ያሳያል ፡፡ ትሕትና እንዳልኖሩ ሁኖ ከሌሎች ልምድን መቅሰም ነው ፡፡
ከፍ ላሉት ዝቅ ማለት ትሕትና አይደለም ፡፡ ከፍ ያሉትማ ግርማቸው በግድ ያሰግዳል ፡፡ ትሕትና ዝቅ ላሉት የምናሳየው ፍቅርና ክብር ነው ፡፡ ለእግረኛ ቅድሚያ ስትሰጥ አንድ ነገር አስብ ፡- “መኪና ለሰው እንጂ ሰው ለመኪና አልተፈጠረም፡፡” እውነተኛ ትሕትና ለሚያንሱን መታዘዝ ነው ፡፡ ሰው እንደዚህ ሁኖ እንደማይቀር ብናስብ ስንት ሕጻናትን ስንት ድሆችን ባከበርን ነበር ፡፡ ትሕትና የልብ መሰበር ያመጣልና ለዝማሬና ለንስሐ ያበቃል ፡፡ አበባ ካልታሸ አይሸትም ፣ ፍራፍሬ ካልተጨመቀ አይጠጣም ፡፡ ሰውም ትሑት ካልሆነ መልኩ አይወጣም ፡፡ ትሕትና ያወቁትን ያለ ትችት ማስተማር እንጂ አላውቅም ማለት አይደለም ፡፡ እያወቁ አላውቅም ማለት ልግመት ፣ ሳያውቁ አውቃለሁ ማለት ራስን አለማወቅ ነው ፡፡ ያወቁትን በትጋት ማስተላለፍ ትሕትና ነው ፡፡ የተማርከው ሌሎችን ደንቆሮ ብሎ ለመሳደብ ሳይሆን በጨለማ ላሉት ብርሃን ለማወጅ ነው ፡፡ የጋን ውስጥ መብራት ከመሆን የሚያድነው ትሕትና ነውና ስታውቅ ትሑት ሁን ፡፡ ፍሬ ያለው ዛፍ ዘንበል ይላል ፡፡ ቀና የሚሉት ዛፎች ግን ፍሬ የሌላቸው ናቸው ፡፡ በእውነት ካወቅህ ያላወቅከው ስለሚበዛብህ ትሑት ትሆናለህ ፡፡ በአንድ ጥቅስ ጫካ የሚገቡ የአቡጊዳ ሽፍቶች ግን ትዕቢተኞች ናቸው ፡፡ “ድምፅና ቁንጫ ባዶ ቤት ይወዳል” ይባላል ፡፡ ቁንጫም እንደ ልቡ ይዘላል ፣ ባዶ አዳራሽም ድምፅን ያስተጋባል ፡፡ ጩኸት ማብዛት የባዶ ቤት ምልክት ነው ፡፡ ባዶ ሰው ከቀድሞ የከፉ የሰባት ኣጋንንት ማደሪያ ይሆናልና እባክህ ባዶ አትሁን ፡፡
ትሕትና የልብ ነው ፡፡ የልብ ያልሆነ ትሕትና የአንገት መሰበር ፣ የጉልበት መሸብረክ ብቻ ነው ፡፡ በልብ እየናቁ በአፍ ማክበር እርሱ ትሕትና ማጣት ነው ፡፡ ይልቁንም ትልቁን መንግሥት ፣ መንግሥተ ሥላሴን እየሰበክህ ትሑት ልትሆን ይገባሃል ፡፡ ትልቁን ትሕትና ነገረ ሥጋዌን እየተናገርህ ትሑት መሆን ያስፈልግሃል ፡፡ ተዋሕዶ ማለት ትሕትና ማለት ነው ፡፡ ባለጠጋው መለኮት ከድሃው ሥጋ ጋር የተዋሐደበት ማለት ነው ፡፡ የሥጋ ድህነት ለመለኮት ፣ የመለኮት ብልጥግና ለሥጋ እንዲነገር የፈቀደው ትልቁ የትሕትና ትምህርት ቤት ምሥጢረ ሥጋዌ ነው ፡፡ ምስኪኖችና ጦም አዳሪዎችን ፣ ኃጢአተኞችንና መንገድ የጠፋባቸውን ካላዘንክላቸው በተዋሕዶ አታምንም ማለት ነው ፡፡ የተዋሕዶ ምሥጢር ሲገባህ በቀራጮችና በኃጢአተኞች አታፍርም ፡፡ የወደቀውን ለማንሣት ዝቅ ትላለህ ፣ ወደ ሐኪም ቤት ለማድረስ አህያህን እንደ ደጉ ሳምራዊ ለቀህ እግረኛ ትሆናለህ ፡፡
የስድብ አምሮትህን ለመወጣት “ውሾች” ይላል ቃሉ ፣ የነቀፋ ጥማትህን “ተኩላ” ይላል ወንጌሉ እያልህ ከተወጣኸው ኃጢአትና በቅዱሱ ነገር መበደልህ ነው ፡፡ ውሻ ፣ ተኩላ ያለው ጠባያቸውን ለመግለጥ እንጂ ላንተ ስድብ ለማበደር አይደለም ፡፡ ትሕትና ተፈትኜ አልጨረስኩም ብሎ በራሱ በጣም አይመካም ፡፡ ገና በፈተና ዓለም ያሉ ሰዎችንም በጣም አያመሰግንም ፡፡ እባክህ ወዳጄ ትሑት ሁን ፡፡ የበላይ የበታች ሁሉም ልቡ ጎረምሳ ሁኗልና የሚያስተነፍስ መዓት ሳይመጣ ትሕትናን ገንዘብ እናድርግ ፡፡ ትሕትናን በማጣት ያሳዘንከውን እግዚአብሔር በብዙ ትሩፋት አታስደስተውም ፡፡ ትሕትና የእምነት መጀመሪያ ነውና ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ