የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ትቀመጥ ዘንድ

 “ወደ መቄዶንያ በሄድሁ ጊዜ፥ አንዳንዶች ልዩ ትምህርትን እንዳያስተምሩና ወደ ተረት መጨረሻም ወደሌለው ወደ ትውልዶች ታሪክ እንዳያደምጡ ልታዛቸው በኤፌሶን ትቀመጥ ዘንድ ለመንሁህ ፤ እንደ እነዚህ ያሉ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉና በእምነት ግን ላለ ለእግዚአብሔር መጋቢነት አይጠቅሙም።” 1ጢሞ. 1፡3-4 ።
የሮም መንግሥት በሚገዛበት ዘመን እስያ እንደ አውራጃ ትቆጠር ነበር ። ይህችውም የዛሬዋ ቱርክ ናት ። በዛሬዋ ቱርክ በኤጂያን ባሕር ዳርቻ ላይ የተመሠረተችው የኤፌሶን ከተማ ተለይታ የምትታወቅባቸው ሁለት ነገሮች ነበሩአት ። የመጀመሪያው፡- ሠላሳ ሺህ ሰዎችን በወንበር የሚያስተናግድ ትልቅ የጨዋታ ስፍራ ሲሆን ሁለተኛው አርጤምስ ወይም ዲያና የተባለች ጣዖት የምትመለክበት ትልቅ መቅደስ ነው ። ለአርጤምስም አምልኮት ይፈጸም የነበረው በዝሙት ስለ ነበር ብዙ ሴቶች የነበሩባትና ርኩሰትም የበዛባት ከተማ ነበረች ። ዝነኛዋ የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በዚህች ከተማ ነው ። ቤተ ክርስቲያን በረከሰው ዓለም ላይ በቅድስና የምትኖር ፣ ኃጢአትን ማሸነፍ አይቻልም በሚል ማኅበረሰብ ዘንድ እንዴት ለእግዚአብሔር መኖር እንደሚቻል የምታሳይ የከተማ ገዳም ናት ። የቤተ ክርስቲያን ልጆችም የከተማ መናንያን ናቸው ። በኤፌሶን ከተማ ቤተ ክርስቲያን እንድትመሠረት ምክንያት የሆኑት አቂላና ጵርስቅላ የሚባሉ ባልና ሚስት ናቸው ። በኋላም ሐዋርያው ጳውሎስ አጠናክሯታል ። አዋቂው አጵሎስም አገልግሎባታል ። ጢሞቴዎስ ሐዋርያው ጳውሎስን ተክቶ ሲያገለግል ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም እስከ ዘመኑ ፍጻሜ ድረስ የዚህች ቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ ነበር ።

የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን በመመሥረቷ ምክንያት የከተማይቱ ብረት ቀጥቃጮችና ጣዖት ሠሪዎች ገቢያችን ቀነሰ በማለት በሐዋርያው ጳውሎስ ላይ ብዙ እንግልት አምጥተውበታል ። ጣዖታውያንና አላዋቂዎች ወንጌልን የሚቃወሙት ንግዳቸው እንዳይቀዘቅዝና አደንቊረው የሚገዙት ወገን እንዳይነቃ ብለው ነው ።
የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን የኤፌሶን መልእክት የተጻፈላት ፣ በወደቀው ከተማ ብትኖርም በሰማያዊ ስፍራ የተቀመጠች ፣ በመንፈሳዊ በረከትም የተባረከች አካለ ክርስቶስ ናት ። የስህተት ትምህርቶች ቆይተው ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር ያሳጡናል ። ይህች ቤተ ክርስቲያን ስህተት እያንዣበበባት መሆኑን ሐዋርያው ተረድቶ መሪዎቿን አስጠንቅቆ ነበር ። ቸልተኛ መሪዎች ለትጉ መናፍቃን ሕዝብን አሳልፈው ይሰጣሉ ። ለሦስት ዓመታት ያህል በታላቅ ትጋት ያገለገላት ሐዋርያው ጳውሎስ የኢየሩሳሌም እስራቱ እየተቃረበ ሲመጣ ለመሪዎቿ፡- በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ”  አላቸው ። /የሐዋ. 20፡28/ ።
ይህች ቤተ ክርስቲያን ለጣዖት የተሠዋ ነገርን እንዲበሉና እንዲሴስኑ የሚያበረታታውን የኒቆላውያንን ትምህርት ተቃውማለች ። ነገር ግን ከአባላቷ በዚህ ትምህርት የተሳቡ ሳይኖሩ አይቀሩም ። /ራእ. 2፡6፤ ቁ. 14/ ። በዚህ ምክንያት የቀደመ ትጋቷን በመቀነስዋ፡- ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና የሚል ወቀሳ ደርሶባታል ። /ራእ. 2፡4 ።/ ያንዣበባት ኑፋቄ ክርክርና ጥላቻን በመካከሏ አስነሥቶ ነበር ። ሐዋርያው ጳውሎስ ከእስራቱ በተፈታ ጊዜ ምናልባት በ62 ዓ.ም ገደማ ጢሞቴዎስ የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ እንዲሆን ልኮት ነበር ። የጢሞቴዎስን መልእክት እንዲጻፍ ያደረገውም በኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን የገባው የስህተት ትምህርትና የጢሞቴዎስ ወጣት የቤተ ክርስቲያን መሪነት ነው ።
ይህች ቤተ ክርስቲያን የዮሐንስ ራእይ በተጻፈበት በ95 ዓ.ም ገደማ መንፈሳዊ መቀዛቀዝ ታይቶባት ነበረ ። ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መልእክት ሲጻፍም የመጀመሪያው መልእክት የተጻፈው ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ነው ። /ራእ. 2፡1 ።/
መቄዶንያ ሰሜናዊ የግሪክ ግዛት ስትሆን ቱርክ ወይም ኤፌሶንም ለዚህች ግዛት ቅርብ ናት ። ሐዋርያው በሰሜናዊው በታላቁ እስክንድር መናገሻ ከተማ የማይፈርሰውን የክርስቶስን መንግሥት እየሰበከ ነበር ። የሚያያቸውን የመቄዶንያ ሰዎች ሲያገለግል በልቡ የሚመላለሱትን የኤፌሶን ሰዎችን እንዲያገለግል ጢሞቴዎስን ላከው ። ሐዋርያው፡- አንዳንዶች ልዩ ትምህርትን እንዳያስተምሩና ወደ ተረት መጨረሻም ወደሌለው ወደ ትውልዶች ታሪክ እንዳያደምጡ ልታዛቸው በኤፌሶን ትቀመጥ ዘንድ ለመንሁህ” ይለዋል ። የስህተት ትምህርቶች የፈጠራ ትምህርቶች እንጂ መለኮታዊ መገለጦች አይደሉም ። በጎችን የሚደፍር ተኩላ ፣ እረኛው ካለ ይፈራል ፣ እረኛው ሲዘናጋ ደግሞ ይደፍራል ። ትጉህ እረኛ የሆነው ጢሞቴዎስ የተላከው የስህተት አስተማሪዎች እንዲደነግጡ ነው ። የስህተት አስተማሪዎች በጎች አይደሉምና እረኛ አይወዱም ። መንጋውንም ለመስረቅ ከእረኛው ጋር እንዲጣላ ያደርጉታል ። ልዩ ትምህርቶች በየጊዜው ይፈጠራሉ ። እነርሱን ሁሉ በየጊዜው ማጥናት አይቻልም ። እውነቱን ማወቅ ግን እውነተኛ ያልሆነውን ለመለየት ያግዛል ።
ተረቶች ሁሉ ክፉ አይደሉም ። እውነትን ለማብራራት አጋዥ ማስተማሪዎች ናቸው ። ተረቶች እውነቱን ተክተው ሲቆሙ ግን ከባድ ነው ። የስህተት ትምህርት የሚባለው ይህ ነው ። መጨረሻም የሌለው የትውልዶች ታሪክ የተባለው ስለ ዓለምና ስለ ሰው አፈጣጠር የሚናገሩ የግሪክ አፈ ታሪኮችና ሐተታ አማልክት ናቸው ። ታሪኮችና የትውልዶች ታሪክ ዓለምን የፈጠረውንና ዘመንን ያስጀመረውን እግዚአብሔርን ማሳየት ካልቻሉ መቆሚያ የላቸውም ። የብዙ የጎሣ ግጭቶች መነሻ መጨረሻ የሌለው ሐተታ አማልክትና የትውልዶች ታሪክ ነው ። እነዚህ ተረቶችና የትውልድ ታሪኮች በመካከላቸው የጎሣና የቋንቋ ጠብ አሥነሥተው ይሆናል ። እስከ ዛሬ አማኝ የነበሩ አሁን ግን ጎሣቸው ውስጥ የተደበቁ በጣም ምስኪን ናቸው ። ከማይጠፋ ዘር ተወልደናል እያሉ ሲፎክሩ የነበሩ የሚጠፋ ዘርን ማቀንቀን ከጀመሩ የሚገርም ነው ። ትላንት ክርስቲያን ዛሬ ጎሠኛ የሆኑ ፣ የተራራቀውን የሚያገናኝ ድልድይ ከመሆን ተጨማሪ ግንብ የሚገነቡ በጣም ሊመከሩ ይገባል ። “ጊዜ የሰጠው ዘፈን እንቅርት ያፈርጣል” እንዲሉ የምንጮህበት ነገር ሁሉ በቃለ እግዚአብሔር መገምገም አለበት ። ትኩስን ቂም ተዉ በሚል ክርስትና የፈረሱ ቂሞችን ሕያው ማድረግና መጋደል ከአማንያን አይጠበቅም ። መምህራን ፈርተው ሊቀመጡ ሳይሆን ሊገሥጹ ይገባል ። ጢሞቴዎስ ወደ ኤፌሶን የተላከው ለዚህ ነበርና ። 
ሐዋርያው፡- “እንዳያደምጡ ልታዛቸው” ይላል ። ሰዎች እንዳይሰሙ ማዘዝ አንችልም ። እንዳያደምጡ ማለት በውስጣቸው እንዳይጽፉት ግን ማዘዝ አለብን ።
ሐዋርያው በመቀጠል፡- “ለመንሁህ”ይላል ። ሐዋርያው በዕድሜም ፣ በሥልጣንም ፣ በአባትነትም ማዘዝ ሲችል መለመኑ ትሕትናውን ያሳያል ። ትሕትና የሚያስፈልገው ከፍ ላለ ሰው ነው ። ዝቅ ያለውማ በግድ ትሑት ነው ። ትሕትና ያስፈለገው በከፍታ ላሉት ነው ።
ሐዋርያዊ መጻሕፍት የማጽናናት ብቻ ሳይሆን ከስህተት ትምህርት የመጠበቅ አደራ ያዘሉ ናቸው ። የስህተት ትምህርት እንክርዳድ በመሆኑ ስንዴውን ይጋፋል ። ነፍስን ያሰክራል ። ፍቅርን ያጠፋል ። ቁመት መለካካት ስለሚያመጣ በክርክር ምክንያት መናናቅና መነቃቀፍን ይከስታል ።
“በኤፌሶን ትቀመጥ ዘንድ” ይላል ። ይህ ጽሞና ለነበረው ለወጣቱ ጢሞቴዎስ ቀላል ትእዛዝ ሊሆን ይችላል ። ጽሞና የሌላቸው ወጣት አገልጋዮች ግን መቀመጥን አይወዱም ። ብክነት ትጋት ይመስላቸዋል ። መቀመጥን የማይወዱ ምእመናንም በሃይማኖት ቅምሻ አገሩን ሲያስሱት ይኖራሉ ። “ወጥን የሚያውቅ ቀላዋጭ ነው” እንዲሉ ስለ ሁሉም ቦታዎች ትንታኔ ያበዛሉ ። ብዙ ድስት የለመደ ተረጋግቶ መመገብ ፣ ከአንድ ስፍራ መማር አይሆንለትም ። የዘመኑ ሰማዕትነት መቀመጥ ነው ።
ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ፣ እባክህን ባስቀመጥከን ቦታ መገኘት ይሁንልን !!!
1ጢሞቴዎስ /8/
ኅዳር 12 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ