የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ትውልድ ሆይ ንቃ !

“ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን ።” ኤፌ. 1፡8 ።

እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ ፈጠረው ስንል በእውቀት ፈጠረው ማለታችንም ነው ። ይህ እውቀትም እግዚአብሔርንና ተግባሩን ተረድቶ ማመስገን ነው ። ይህ እውቀትም ከእግዚአብሔር ጋር በጽድቅ ፣ ከሰዎች ጋር በሰላም መኖር ነው ። ከእንስሳት እውቀት ፣ የሰዎች እውቀት ፣ ከሰዎች እውቀትም የመላእክት እውቀት ይበልጣል ። እውቀቱ ፍጹም የሆነ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። “ማስተዋሉ አይመረመርም” ተብሎ እንደ ተጻፈ ። ሰው ምድራዊ ሳለ ሰማያዊ ፣ እንጀራ ብቻ ሳይሆን አምልኮትን ፈላጊ የሆነው የእግዚአብሔርን መልክ ስለተሸከመ ነው ። የሰው ልጅ በበደል ምክንያት ካጣቸው ጸጋዎች አንዱ እውቀት ነው ። ነቢዩ ዳዊት እውቀት በማጣቱ ሰው እንስሳትን እንደ መሰለ ተናግሯል ። “አእምሮ የሌለው ክቡር ሰው እንደሚጠፋ እንስሶች መሰለ።” መዝ. 48፡20። የሰው ልጅ ከእንስሳት በላይ ነውና እንስሳት ወደ እርሱ እየመጡ እርሱም በአለቅነቱ ስም ያወጣላቸው ነበር ። ኋላ ተፈጥሮ ለእንስሳት ስም ማውጣቱ ባለቤትነቱን ያመለክታል ። ከአፈር በመገኘቱ ፣ በመብላት በመጠጣቱ ፣ በመዋለድ ሥርዓቱ እንስሳትን ይመስላል ። ፈጽመን እንስሳ እንዳንለው ደግሞ መልአካዊ ፍላጎት አለው ።

በበደል ምክንያት ግን አሳቡ ምድራዊ ፣ ግቡ ቁሳዊ ሲሆን እንስሳትን መሰለ ። እንስሳት ሳሉ ብቻ የሚኖሩ ፣ ከመሬት ተገኝተው መሬት ውስጥ የሚያበቁ ናቸው ። ሰውን ሰው የሚያደርገው ከሞት በኋላ ማየት መቻሉ ነው ። በዚህ ምክንያት ሰው እንስሳትን መሰለ ። እንስሳት አይጸጸቱም ፣ አራዊት ለመኖር ብለው በመግደላቸው የሚጠየቁበት ሕግ የለም ። የሰው ኑሮ በሌላው ሞት ላይ በመመሥረቱ እንስሳትን መሰለ ተባለ ።

ነቢዩ ኢሳይያስ ደግሞ ከነቢዩ ዳዊት ርቆ በመሄድ ሰው ከእንስሳትንም እንዳነሰ ይናገራል ። “በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ እስራኤል ግን አላወቀም ፥ ሕዝቤም አላስተዋለም ።” ኢሳ. 1፡3 ። እንስሳት ጌታቸውንና የጌታቸውን ቤት ያውቃሉ ። ሰው ግን እግዚአብሔርን የማያውቅ ፣ ማወቅም ያሳስታል ብሎ የሚያምን ፣ በሰንበት ወደ እግዚአብሔር ቤት ከመሄድ ጀርባው እስኪላጥ የሚተኛ በመሆኑ ከእንስሳት አነሰ ተባለ ።

በበደል ምክንያት እውቀቱ ቢጨልምም የሰው ልጅ መልኩ ፈጽሞ የጠፋ አልነበረም ። አዳም ነቢይ ፣ ካህንና ንጉሥ ሁኖ በሦስት ማዕረጋት ከብሮ ተፈጥሯል ። ይህ ማዕረግ ጨርሶ እንዳልጠፋ እንደ ነቢይ ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገሩ ቅዱሳን ፣ እንደ ካህን የተገለጡ መልከ ጼዴቆች ፣ አራዊትን የገዙ ፣ ፍጥረትን ያዘዙ ሙሴያውያን ታይተዋል ።

የሃይማኖት ብቻ ሳይሆን የኪነ ሕንፃ ፣ የሥነ ጽሑፍ ፣ የንግግር ክህሎት ፣ የባሕል ፣ የሥርዓት ፣ የሕግ መገኛው የእግዚአብሔር ቤት ነው ። ይህም የእውቀትን ከፍታና የጥበብን ዐውድ ያሳየናል ። ከቤተ ክርስቲያን ያልተኮረጀ ኪነ ሕንፃ ፣ ዘማሪ ያልነበረ እውቅ ዘፋኝ ፣ ቅኔ ቤት ያላለፈ ጎበዝ ገጣሚ ፣ ደጀ ሰላም ያልረገጠ ጥሩ አጫዋች ማነው ብለን መጠየቅ ብቻውን በቂ ነው ። የሰሎሞን መቅደስ ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት የዕብራይስጥ ፊደል ፣ በአደባባይ ቆመው ንግግር ያደርጉ የነበሩ ነቢያት ፣ የአገር አንድነትን የጠበቁ ካህናት ፣ አምስት መቶ ዓመታትን ዘመነ ካህናት ብለው ያሰየሙ ፣ መሪ ሲጠፋ መሪ የሆኑ መቅደሳውያን ፤ ዜማውን ከነምልክቱ ያወረሱትን ሃይማኖታውያን ስናስብ የእግዚአብሔር ቤት የእውቀት ራስ መሆኑን ይነግረናል ። ሰው አእምሮው የሚጨልመው ከእግዚአብሔር ቤት ሲርቅ ነው ። ከእግዚአብሔር ቤት የራቁ ፍልስፍ የሚሉ ሰዎች በሱስ ጉቦ ቀኑን የሚገፉ ፣ መጨረሻቸው የማያምር ምስኪኖች ናቸው ። በዓለም ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫና የፍትሐ ብሔር ሕግ ከዐሥርቱ ትእዛዛት የተቀዳ ነው ። የዚህች ዓለም መሠረት የእግዚአብሔር ቤት ነው ።

ቤተ ክርስቲያን ዓለም ናት ። በዓለም ካለው በላይ በቤተ ክርስቲያን ያለው ይበልጣል ። ሌላ ዓለም የማያምረን ቤተ ክርስቲያን ራስዋ ዓለም ስለሆነች ነው ። የግጥም ምሽት እንዳንፈልግ የከበረ ቅዱስ ቅኔ እንደ ጅረት ይፈስሳል ። ዘፈን እንዳንሻ አዲስ ዜማ በየዕለቱ ይፈልቃል ። ኪነ ሕንፃ እንዳናስስ ዓለም ወደ እኛ የሚመጣበት ብዙ ጥበበኛ መቅደሶች አሉን ። ሌላ ባሕል እንዳያምረን ለሺህ ዓመታት የዘለቀ ሥርዓትና አለባበስ በቤተ ክርስቲያን ይታያል ። ቤተ ክርስቲያን በማውገዝ ሳይሆን ሁሉን በማቅረብ ትውልድን ከዓለም የመነጠል አሠራር አላት ። ይህን አውቀው የሚያሳውቁ ከሌሉ ግን ትውልድ የቤተ ክርስቲያን ጠላት ይሆናል ።

እውቀት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሃይማኖት ያምናል ። ዛሬ በዓለማችን ላይ የታወቁ ዩኒቨርሲቲዎች ትላንት ገዳም የነበሩ ናቸው ። ገዳማውያን ገዳማቸውን ለተማሪዎች መልቀቃቸው ፣ ተማሪዎቹ ሲመረቁ የሚለብሱት ልብስም የመነኮሳት ልብስ መሆኑ ቤተ ክርስቲያን ለእውቀት ያላትን ዋጋ ያሳያል ። የመድኃኒት ቅመማውን ሥር መማስ ፣ ቅጠል መበጠስ በማለት አቃለልነው ፣ የሥነ ከዋክብት ምርምሩን ኮከብ ቆጠራ ፣ ጥንቆላ ፣ የዜማውን ጥበብ ጩኸት ፣ የቃል ትምህርቱን ድግምት አልነው ። ያልተማረ ሁሉን ያረክስ እንዲሉ ። የገዛ ስልክ ቍጥሩን በቃሉ የማያውቅ ትውልድ ብሉይና ሐዲስን በቃላቸው የሚያውቁ አባቶችን ሲንቅ ማየት በጣም ይገርማል ። የራሳችንን እንድንጠላ የሚያደርጉን ሃይማኖት የሚመስሉ የባሕል ወረራዎች አያሌ ናቸውና ትውልድ ሆይ ንቃ !!!

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /18

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 1 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ